አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

ትኩረት ለስነ-ምግባራዊ መሪዎች እና ድርጅቶች ግንባታ!

ትኩረት ለስነ-ምግባራዊ መሪዎች እና ድርጅቶች ግንባታ!

በስንታየሁ ግርማ አይታገድ- ታዋቂው የስራ አመራር ምሁር ፒተር ድሩከር ‘በእድገት ወደኃላ ከቀሩ ሀገራት ይልቅ በስራ-አመራር የተበደሉ ይበዛሉ’ በሚለዉ አባባሉ በብዛት ይታወሳል፡፡አባባሉ ለሀገር ወይንም ለድርጅት እድገትም ሆነ ውድቀት ወሳኙ የሰው ሀይል በተለይም መሪዎች ወሳኝ መሆናቸውንያሳያል፡፡

አስሞለጉ እና ሮቢንሰን why nations fail በሚል መፅሃፋቸዉ አንዳንድ ሀገራትመበልፀግ የቻሉት፤ ሌሎች ደግሞ በድህነት አረንቋየተዘፈቁት በተፈጥሮ፣ በአየር ንብረት፣ በባህል ልዩነቶች ሳይሆን አካታች ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስርአት በመሪዎቻቸዉ መገንባት በመቻል ወይም ባለመቻላቸው ነዉ ይላሉ፡፡ በተፈጥሮሀብት፣ በአየር ንብረት፣ በባህል መመሳሰል ቢሆን ኖሮ ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ በተመሳሳይ እድገት ላይ በተገኙ ነበር፡፡



ለልዩነቱ መንስኤ በደቡብ ኮሪያ ፈጠራን የሚያበረታታ ኢኮኖሚ እና የባለስልጣን ሳይሆን የህግ የበላይነት የሰፈነበት አካታች የፖለቲካ ስርአት በመገንባቱ እና በአስተማማኝ ሁኔታ ተግባራዊ በመደረጉ ነዉ፡፡ የዚህን አይነት አካታች ስርአት ለመገንባት ደግሞ መሪዎች በተለይም ስነ-ምግባራዊ መሪዎች መኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለዉ፡፡ በስነ-ምግባር አርአያ የሆኑ መሪዎች አካታች ስርአት ይገነባሉ፡፡ በስነ-ምግባር የዘቀጡ ባለስልጣናት ደግሞ አግላይ ስርአት በመገንባት ሙስናን ባህል በማድረግ ማህበራዊ ካፒታልን በመሸርሸር ሀገርን ወደ ውድቀት አዙሪት ይከታሉ፡፡

በዚህ አለም እንደ ሥነ-ምግባር በመጥፎም ሆነ በጥሩ ለሀገርም ሆነ ለተቋማት ወሳኝ ነገር የለም፡፡ በአለም ላይ ያደጉ እና የለሙ ሀገራት መሠረታቸው ስነ-ምግባር ነው፡፡ ለምሣሌ የምዕራቡ አለም እድገት “ከፕሮቴስታንት ስነ-ምግባር” ጋር ሲያያዝ በ3ዐ አመታት ውስጥ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ህዝብ ከድህነነት ወለል በማውጣት የምትታወቀው ቻይና እድገት አንዳአንድ ኋላ ቀሪ የኮንፈሲየስ ባህላዊ እሴቶች ከመለወጥ ጋር ይያያዛል፡፡

በአለም በከፍተኛ ፍጥነት እድገት ያስመዘገቡ የሩቅ ምሥራቅ ኤስያ ሀገራት ደግሞ እድገታቸው ከህዝብ ብሔራዊ መግባባት ጋር ይያያዛል፡፡ እንደ ኮሪያ የመሳሰሉት ሀገራት ሌባ እንኳን ለክቶ የሚሠርቅበት ሀገር ነበሩ፡፡ ለምሣሌ ለኤክስፖርት በተዘጋጀ ምርት እና አገልግሎት ላይ የጉምሩክ ሠራተኞች ስርቆት አይፈፅሙም ነበር፡፡

መሀንዲሶች በሚገነባው ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ መንገድ የራሳቸውን 1ዐ በመቶ ኮሚሽን በመጨመር በጥራቱ፣ በጊዜውናበመጠኑ ላይ አይደራደሩም ነበር፡፡ ይህንን እስቲ ከእኛ አገር ሌቦች ጋር አወዳድሩት? ከዚህ በመነሣት ሥነ-ምግባር ሙስናን ለመከላከል ወይም ለመከሠት ዓይነተኛ ሚና እንዳለው መረዳት እንችላለን፡፡ማህበረሰቡ ከማንኛውም የመንግሥት ተቋም ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ትክክለኛ አገልግሎት ይጠብቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ “ደንበኛ ሁልጊዜ ትክከል ነው፣ ሉዕላዊ” ነው የሚሉት አባባሎች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ይሁንታ እያገኙ ነው፡፡

ደንበኛ ለማርካት የማይጥር ድርጅት፣ ተቋምና ሀገር እራሱን በገመድ አንቆ እንደ መግደል በሚታይበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡፡ ምክንያቱም ደንበኛ/ተገልጋይ/የሚያማልሉ አገልግሎት ሰጪዎች እንደ አሸን እየፈሉ እና ድንበር የለሽ እየሆኑ በመምጣታቸው ነው፡፡

ምንም እንኳን ለማህበረሰቡ ፍትሀዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግ ቢጠበቅም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ግን ሥነ-ምግባራዊ እሴቶች በመንግሥት አገልግሎት አሠጣጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸረሸሩ ነው፡፡ ይህ የመንግሥት አገልግሎት አሠጣጥ መላሸቅ በዋነኝነት የሚገለፀው በሙስና መልክ ነው፡፡ ሙስና የህዝብ ስልጣን ለግል ጥቅም ወይም ትርፍ ማዋል ነው፡፡ ጉዳቱ ግን ዘርፈ ብዙ ነው፡፡

ሙስና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ተፅዕኖዎች አሉት፡፡ በፖለቲካው መስክ ሙስና የህግ የበላይነት መሸርሸርእና ለዲሞክራሲ ማበብ ትልቁ እንቅፋት ነው፡፡ ሙስና በተንሠራፋበት እና የሰዎች እንጂ የህግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ተቋማት አይገነቡም፡፡ ተቋማት ባልተገነቡበት ሁኔታ ደግሞ አካታች ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሥርዓት አይመሠረትም፡፡ በተቋማት ያልታገዘ እድገት እና ልማት ዘላቂነት አይኖረውም፡፡

የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል ባላቸው ሀገራት ሣይቀር ሙስና የመንግሥት ቢሮዎች፣ ተቋማት፣ መርሆዎች ላይ እምነት በማሣጣት የቅቡልነት ቀውስ ውስጥ ይከታል፡፡በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ደግሞ የበለጠ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ሙስና በተንሠራፋበት ሁኔታ እና ቦታ ተጠያቂነት እና ልጓም ያለው የፖለቲካ አመራር ማስፈን አይቻልም፡፡

በኢኮኖሚው መስክ ሙስና የሀገር ሀብት እንዲወድም ያደርጋል፡፡ በአብዛኛው ውስን የሆነው የህዝብ ሀብት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው/ለድሆች/ ከፍተኛ ባልሆኑ ኘሮጀክቶች ማለትም እንደ ግድቦች፣ የሃይል ማመንጫዎች፣ የቧንቧ መስመሮች፣ አስደናቂ ግን መሠረታዊ ያልሆኑ አገልግሎቶች(ለከፍተኛሙስና በር ስለሚከፍቱ) ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድና ውሃ ወደ ገጠር አካባቢ እንዳይስፋፋ ያደርጋል፡፡ ከሁሉም የከፋው ደግሞ ውድድሩን በመገደብ የነፃ ገበያ እንዳይስፋፋ ያደርጋል፡፡ ኢንቨስትመንትም ያቀጭጫል፡፡

ሙስና በህብረተሰቡ ማህበራዊ ትስስር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከሁሉም በላይ ነው፡፡ ህብረተሰቡ በፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ ያለውን እምነት ያቀጭጫል፡፡ በተቋማት እና በፖለቲካ መርሆዎች ላይ ያለውን ተስፋ ያጨልማል፡፡ ይህ ደግሞ በዲሞክራሲ በተመረጡ መሪዎዎች ሳይቀር ህሊና-ቢስ በማድረግ የህዝቡን ሀብት ወደ ውጭ ሀገር እንዲያሸሹ ይረዳቸዋል፡፡ ጉቦ መጠየቅ እና መስጠት አፀያፊ ስነ-ምግባር መሆኑ ቀርቶ የተለመደ እና ቅቡልነት ያለው መጥፎ ባህርይ ያደርገዋል፡፡

ስነ-ምግባራዊ መሪ መገንባት ኢትዮጵያ አሁን ለተዘፈቀችበት ብልሹ አሰራር እና የሙስና ማእበል ዋነኛውመፍትሄውነው፡፡ መሪዎች ስነ-ምግባራዊ ሲሆኑ ተከታዮቻቸዉ ስነ-ምግባራዊ ይሆናሉ፡፡ መሪዎቹ እና ተከታዮቻቸው ስነ-ምግባራዊ ባህል ይገነባሉ፡፡ እስቲ በቀጣይ ስነ-ምግባራዊ መሪ ምን እንደሆነ፣ የስነ-ምግባራዊ መሪ መርሆች፣ ስነ-ምግባራዊ ባህል እንዴትእንደሚገነባ እንይ፡



ስነ-ምግባራዊ (ግብረ-ገብ) መሪ
• መሪ ማለት ተከታይ ያለው እና መደበኛ ስልጣን ይኑረውም አይኑረውም ተከታይ ካለው መሪ ነው፡፡
• ስነ-ምግባራዊ (ግብረ-ገብ) መሪ የሚመራበት መርህ ያለው ለመርሁ የታመነ ትክክል ያልሆነውን እየተወ ትክክል የሆነውን ለመተግበር የሚተጋ እውነተኛና ፍትሀዊ የሆነውን ነገር በመስራት ለተከታዮቹ አርአያ የሚሆን ማለት ነው፡፡
• አመራር ሆኖ ግለሰቡ የጋራ ጥቅም የሆነውን የሚያራምድ እና የሚተገብር ሆኖ በማንኛውም የህይወት መመዘኛ ተቀባይነት ያለውንና ተገቢ የሆነውን ነገር የሚፈፅምነው፡፡
• በማንኛውም ጊዜ ድርጊቱ እና አመራሩ ሥነ-ምግባር የተላበሰ ሲሆን ሥነ-ምግባራዊ አመራር ይባላል፡፡
የስነ-ምግባራዊ መሪዎች መርሆዎች
የስነ-ምግባራዊ መሪዎች መርሆዎች ከአርስቶትል ጀምሮ ያሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ መርሆዎች ጠቀሜታቸው በተለያዩ ዲስፒሊን ውስጥ መወያያ ናቸው፡፡ሥነ-ምግባራዊ መሪ ለመፍጠር መሠረቶች ናቸው፡፡
ሀ.ሥነ-ምግባራዊ መሪዎች ሌሎችን /ተከታዮቻቸውን/ያከብራሉ፡፡ሌሎችን ያገለግላሉ (The servant-leader is servant first)
“መሪ ማለት ተከታይ ያለው ማለት ነው፡፡ተከታይ ሳይኖር መሪ መሆን አይቻልም፡፡ እውነተኛ ተከታይ ለማፍራት ደግሞ እውነተኛ አገልጋይ መሆንን ይጠይቃል”
ለ.ትክክለኛውን ውሳኔ ይወስናሉ ይተገብራሉ
ሐ. ሐቀኝነትን (honesty) እዉነትን መናገርን በተግባር ያስመሰክራሉ
መ.ማህበረሰብ ይገነባሉ፣ ማህበራዊ ካፒታል ይገነባሉ
ሰ. መሪዎች በቃላቸዉም ሆነ በድርጊታቸዉም አርአያ ይሆናሉ፡፡

ሥነ-ምግባራዊድርጅትእንዴትይገነባል?
መልካም ስም የአንድ ሀገር ድርጅት ስኬታማነትን እና ውድቀትን ይወስናል፡፡ ለዚህም ነው የአለማችን ቁጥር ሶስት ቢሊየነር ዋረን ቡፌትከምንም በላይ ለመልካም ስም /Reputation/ ከፍተኛ ትኩረት እሰጣለሁ ያሉት፡፡ መልካም ስም ለመገንባት ብዙ አመታት ይፈጃሉ፤ለማፍረስ ግን ሠኮንዶች ይበቃሉ፡፡ ለዚህም ነው ጠንቃቃ ድርጅቶች ለመልካም ስም ከፍተኛ ትኩረት የሚሠጡት፡፡ መልካም ሥነ-ምግባር ጥሩ ስም እንደሚገነባ ሁሉ መጥፎምግባር የሠራተኞችን ሞራል ይጐዳል፣ ወጪን ይጨምራል፡፡ ስለዚህ መልካም ሥነ-ምግባር ለመገንባት ተቋማት ትኩረት እየሰጡ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ስለሥነ-ምግባር ዲዛይን ይሠራሉ፡፡ ሥነ-ምግባራዊ ባህል ለመገንባት ለአራት ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ እነርሱም፡- ግልፅ የሥነ-ምግባር እሴቶችን መቅረፅ እና መተግበር፣ ሚዛናዊ ፍርድ መስጠት፣ ማበረታቻዎችን እና ተቀጣይነት ያላቸውን ባህላዊ ልምዶችን መተግበር ናቸው፡፡ እነዚህ አራት የባህላዊ ልምዶች ምሰሶ በመባል ይታወቀሉ፡፡

1. ግልፅ የሥነ-ምግባር እሴቶች መቅረፅ እና መተግበር
እስትራቴጂዎችንና ተግባራትን በአግባቡ፣ በግልፅ መርሆዎች ላይ ተመስርቶ በመቅረፅ በሁሉምሠራተኞች ዘንድ የጋራ ግንዛቤ ሊይያዝ ይገባል፡፡ ለዚህም ደግሞ በአግባቡ የተቀረፀ ተልዕኮ ያስፈልጋል፡፡ከመርሆዎች ጋር የተጣጠመ ተልዕኮ መቅረፅ ይገባል፡፡ የሚቀረፀው ተልዕኮ አጭር፣ ግልፅ፣ ስሜትን የሚያነሳሳ እና የሚያስተጋባ መሆን አለበት፡፡

ይሁንና የአብዛኛዎቹን ተቋማት ተልዕኮ በምናይበት ጊዜ በጣም ረጅም፣ ከሠራተኞች የዕለት ተዕለት ተግባራት ጋር ያልተቀናጀ እና ሠራተኞች ሊመሩባቸው የሚያስችሉ መነሻ አይደሉም፡፡ የተልዕኮ መግለጫዎች በወረቀት ላይ የሚቀመጡ ቃላቶች መሆን የለባቸውም፡፡ በቅጥር፣ በስንብት፣ በእድገት ወዘተ እንደ ፖሊስ ሆነው ማገልገል አለባቸው፡፡ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም የሆነውን ፔንታጐን ተልዕኮን በምናይበት ወቅት ምን ያህል ግልፅ፣ አጭር እና የሚያነሣሣ መሆኑን መንዘብ ይቻላል፡፡‘’Build the best product, cause no unnecessary harm, use business and implement solutions to the environmental crisis’’.

2. ሚዛናዊ ፍርድ
ብዙ ሰዎች ውሣኔ በሚወስኑበት ወቅት ሥነ-ምግባር ግምት ውስጥ የማስገባት ችግር አለባቸው፡፡ በዚህ የተነሣ ሥነ-ምግባራዊ ጉድለቶች ይከሰታሉ፡፡የትኩረት ምንጭም ይሆናሉ፡፡ ለምሣሌ የቅርብ ዘመዳችንን ወይም ጓደኛችንን ስንቀጥር በሌሎች በማናውቃቸው ሰዎች ላይ የምናደርሰውን ጉዳት ግምት ውስጥ አናስገባም፡፡ አዕምሮአችን ያቀበለንን መልዕክት እንደወረደ ተግባር ላይ ስናውል ሚዛናዊ ፍርድ የመስጠት እድላችንን ያጠበዋል፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ፍርድ ስንሰጥ በምናውቃቻውና በማናውቃቸው መካከል ልዩነት ላለመፍጠር ቢያንስ ሁለት ጊዜ ማሰብ ይገባል፡፡



3. ማበረታቻዎች
ግልፅ ተልዕኮን ከመቅረፅ እና ከመተግበር ሚዛናዊ ፍርድን ከመስጠት ጐን ለጐን መልካም ሥነ-ምግባር የተላበሱ ተቋማትን ለመፍጠር ማበረታቻዎችን ከሥነ-ምግባር ጋር ማያያዝ ይገባል፡፡ ውጤት የተመዘገበው ስነ-ምግባርን ተላብሶ አገልግሎት በመስጠት ወይም ባለመስጠት መሆኑን ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሠራተኞች ሥነ-ምግባራዊ ስለሆኑ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ማበረታቻዎች የተለያዩ ዓይነቶች /ውጫዊ እና ውስጣዊ/ መሆን ይገባቸዋል፡፡

ከገንዘብ ማበረታቻ በተጨማሪ ሠራተኞች የሚያረካቸውን ሥራ በመስራት አወንታዊ ተፅእኖ ማሣደርን፣ ክብር ማግኘት እና መደነቅን ይፈልጋሉ፡፡ ይሁንና የሥነ-ምግባር አመራሮች ከፋይናንስ ውጭ ያሉ ማበረታቻዎችን ትኩረት ሲሰጧቸው አይታይም፡፡ስለእነዚህ ማበረታቻዎች የሚሠጡት ትኩረት አናሣ ነው፡፡

ይሁንና መልካም ሥነ-ምግባር ለተላበሱ ሠራተኞች እውቅና መስጠትናማመስገን ይገባል፡፡ ተሸላሚዎችን የሚሠጣቸውን ሽልማት ለማህበራዊ አገልግሎት እንዲያውሉት ማድረግ የበለጠ ያበረታታቸዋል፡፡ ሥነ-ምግባራዊ ባህሪ ሥነ-ምግባራዊ ሥራ ብቻ እንዲሠሩ የሚያበረታታ ብቻ ሣይሆን ጥሩ ስሜትም እንዲሰማን የሚያደርግ ነው፡፡

4. ባህላዊ ልምዶች
በርካታ ከፍትኛ መሪዎች አስቀድሞ ለተጠቃቀሱት የሥነ-ምግባር ስታንዳርዶች ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ይሁንና ለመካከለኛው አመራር ጥብቅ ሥነ-ምግባራዊ ስታንዳርድ መቅረፅን ችላ ይሉታል፡፡ ይሁንና በመካከለኛው አመራር የሚቀረፅ የሥነ-ምግባር ስታንዳርድ የሠራተኞችን ባህሪ በማነፅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ይታመናል፡፡ ጥሩ መርሆዎች ጥሩ ተከታይ ያፈራሉ፡፡ ይሁንና ሠራተኞች በሚዋሹ በሚያታልሉ በሚሠርቁ መካከለኛ አመራሮች የሚከበቡ ከሆኑ የሚዋሹ፣ የሚያታልሉና የሚሰርቁ የመሆናቸው እድል ከፍተኛ ነው፡፡

መርሆዎች ስነ-ምግባራዊ ባህልንበማበረታታት ጥሩ ሥራዎች ምን ምን እንደሆኑ ያሣውቃሉ፡፡ ስለዚህ የሥነ-ምግባር ምልክቶችን /Ethical beacons/ ተግባራዊ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡በአጠቃላይ ስነ-ምግባራዊ መሪዎችን እና ድርጅቶችን ለመፍጠር ትኩረት በመስጠት ለሁላችንም የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር ይገባናል፡፡

Related Post