አርእስተ ዜና
Sat. Apr 27th, 2024

ቡና የአገራችን መለያ መሆን አለበት

Sep11,2023
ቡና የአገራችን መለያ መሆን አለበትቡና የአገራችን መለያ መሆን አለበት

በስንታየሁ ግርማ አይታገድ – ዓለም በምርትና በገበያ በጥብቅ በተሳሰረችበት በዘመነ ግሎባላይዜሽን አገሮች ሁሉ አንፃራዊ ብልጫቸውን በመለየትና 
በማስተዋወቅ ይወዳደራሉ። አገሮች ራሳቸውን ለመሸጥ ከባድ ውድድር ያደርጋሉ፡፡ 

በውድድሩ አሸናፊ በመሆን ልዩ መለያቸውን (ብራንድ) በመለየት በቅንጅት ይንቀሳቀሳሉ፡ የተለየ መለያቸውን የማያስተዋውቁ አገሮች ደግሞ ሌሎች እነሱን  በአሉታዊ መልኩ እንዲገልጹላቸው መፍቀድ ነው፡፡

ታዋቂው የዓለም ሦስተኛ ቢሊየነር ዋረን ቡፌት ስለመለያ ጠቀሜታን ሲያስረዱ ልዩ መለያህን ለመገንባት ሃያ ዓመታት ይፈጃል። ለማፍረስ ደግሞ አምስት ሰከንድ 
ይበቃል፡፡ ስለዚህ በድርጅታችን የሚያደርስ የገንዘብ ጉዳት በጣም ከፍተኛም ቢሆን እታገሳለሁ፡፡ 

በድርጅቱ ገጽታ ላይ በሚደርስ ጉዳት ግን ምሕረት ሊኖረን አይገባም ይላሉ፡፡ ዋረን ቡፌት የድ ርጅታቸውን መለያ ይበልጥ ለመገንባት የዓለም ኢኮኖሚ  ቀውስንም እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመውበታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 የተፈጠረው የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ አንዱ ምክንያት ፍትሐዊ ያልሆነ የግብር አከፋፈል 
ነው የሚል እምነት አላቸው፣ ለዚህም ራሳቸውን እንደ ምሳሌ ያቀርባሉ፡፡

ዋረን ቡፌት የአሜሪካ የግብር ምጣኔ ገቢ በጨመረ ቁጥር የግብር ምጣኔው እየቀነሰ መሄድ (Regrerssieve Tax Rate) በሀብታምና በደሃ መካከል  ያለውልዩነት እየሰፋ የመጣው ይላሉ፡፡ ቡፌት እሳቸው 15 በሆነ የግብር ምጣኔ ታክስ ሲከፍሉ ጸሐፊያቸው 35 በመቶ የሆነ የታክስ ምጣኔ መክፈላቸው 
ፍትሐዊነት የጎደለው ነው በማለት ይተቻሉ፡፡ 

ብልህ የሆኑ ሰዎች፣ ኩባንያዎችና አገሮች ቀውስን ሳይቀር የድርጅታቸውን ተቀባይነት ለማሳደግ ይጠቀሙበታል። አገሮች ምሕረት በሌለው የዘመነ ሉላዊነት
(ግሎባላይዜሽን) ተወዳዳሪና አሸናፊ ለመሆን የተለያዩ መለያዎችን የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ በአገር ደረጃ ከሁሉም የተሻለ ተቀባይነት 
ያለው ምርትን (አገልግሎትን) በመለየት በቅንጅት ይሠራሉ፡፡ መንግሥት የግል ባለሀብትና ሲቪል ማኅበራቱ በጋራ የሚሠሩበትን ሥርዓት ይዘረጋሉ፡፡ 

መለያቸውን በየጊዜው የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ይገመግማሉ፡፡ የብራንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት የተለያዩ መለያዎችን መጠቀም የአገሮችን መለያ በቀላሉ 
ሸማቹ እንዳይረዳው ያደርጋል፡፡ ቱሪዝም የሴክተሩ መለያ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የአገር መለያ ማድረጉ አዋጭነቱ አመርቂ አይደለም ይላሉ፡፡ 

ግብፅ ለምሳሌ ራሷን በቱሪዝም ለማስተዋወቅ በምታደርገው ጥረት የግብፅ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በማቅረብ እጥረት ያለበት በመሆኑ ቱሪስቶች ምሬታቸውን 
እንደሚገልጹ ተዘግቧል፡፡ ስለዚህ ለአገሮች ዋነኛ መለያ መሆን ያለበት አንፃራዊ ብልጫ በያዙበት ልዩ ምርት (አገልግሎት) መሆን እንዳለበት ባለሙያዎች 
ይመክራሉ፡፡ 

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መለያ መሆን ያለበት ቡና፣ ጤፍ፣ አትሌቲክስ ወዘተ. የሚለው በቂ ትንታኔ ተሠርቶበት ወደ ሥራ ቢገባ አገሪቱን በዓለም አቀፍ ገበያ 
ተወዳዳሪ አድርጎ የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡

በጸሐፊው እምነት የኢትዮጵያ መለያ መሆን ያለበት ቡና ነው፡፡ ምክንያቶች ደግሞ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር ናት፡ ቡና የሚለውም ሆነ Coffee የሚለው 
የእንግሊዝኛ ቋንቋ በቀላሉ ሊያያዝ የሚችል ነው፡፡ 

በዓለም ላይ በየቀኑ 2.25 ሚሊዮን ስኒ ቡና ይጠጣል፡፡ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር የቢዝነስ ልውውጥ ይካሄድበታል፡፡ ከነዳጅ ቀጥሎ ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ 
ቡና አነቃቂና በቀላሉ በሌሎች ምርቶች ሊተካ የማይችል በመሆኑ ሸማቹን የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ከሌሎች የግብርና ምርቶች በአንፃራዊ መልኩ 
የሚያጋጥመው የመዋዠቅ ምጣኔ አነስተኛ ነው፡፡ 

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ከሆኑ አሜሪካኖች መካከል 5ዐ በመቶ በየቀኑ ቡና ይጠጣሉ፡፡ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ አገሮች 
መካከል የቻይና ሕዝብ አሥር በመቶ በየቀኑ ቡና የመጠጣት ሱስ ቢይዘው ተጨማሪ ገበያ ማለት ነው፡፡ 

ለዚህ ደግሞ በአገራችን ያሉ ቻይናውያን ቡናን እንዲለምዱ ማድረግ ይቻላል፡፡ የተለያዩ የቡና ቀኖችን በመሰየም በሲምፖዚየሙ፣ በየወርክሾኘ በየጉባዔዎች ወዘተ. 
ቡናን ማስተዋወቅ ይረዳል፡፡ ታዋቂ አትሌቶችና ሰዎች ቡናን እንዲያስተዋውቁ በማድረግ የኢትዮጵያ መለያ (ብራንድ) ማድረግ ይቻላል፡፡ የሚተዋወቀው ምርት/አገልግሎት/ አዋጭ እንዲሆን ከተፈለገ ምርት (አገልግሎት) በዓለም ኅብረተሰብ ተቀባይነት ያለው መሆን አለበት፡፡ ቡና በቢሊዮን የሚቆጠር የዓለም ሕዝብ 
ተቀባይነት ያለው በመሆኑ የአገር መለያ ከመሆን አኳያ ተወዳዳሪ የለውም፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ልዩ ጣዕም ያለው መሆኑ በዓለም አቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ ብዙ ጥናቶች የቡናን ጠቀሜታዎች አስቀምጠዋል። ሲጠቃለል በዓለም 
አቀፍ ደረጃ ቡናን ለማስተዋወቅ የሚከተሉትን የሕዝብ ግንኙነት መሣሪያዎች መጠቀም ጥሩ ነው፡፡

1. ታዋቂ ሰዎች በተለይ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቡናን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ፣
2. ታዋቂ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለኢትዮጵያ ቡና የጻፉትን መጠኑንና ጥራቱን ሞኒተር በማድረግ ጥቅም ላይ ማዋል፣ ለምሳሌ ጥሩ የሚዘግቡትን ወደ
ቡና አምራች ቦታዎች በመውሰድ እንዲጎበኙ ማድረግ፣
3. የተለያዩ ትልልቅ ሁነቶችን በማዘጋጀት ቡናን ማስተዋወቅ፣
4.የመንግሥት ባለሥልጣናትና አምባሳደሮች በውጭ አገር ሲንቀሳቀሱ ቡናን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ ለቡና ገበያ
 ሁኔታዎች እንዲመቻቹ 
የማሳመን ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ፣
5. ዋጋቸው ተመጣጣኝ በሆነና ተቀባይነት ባላቸው ሚድያዎች የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት፣
6.የአገር (የመንግሥት) የሚኒስትሮችና የቱሪዝም ድርጅቶች፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የቡናና ሻይ ልማትና ግ
ብይት ባለሥልጣን ድረ ገጾች፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ቡናን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ፣
7.ለቡና አምራቾች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማለትም እንደ ኦክስፋምና የመሳሰሉት
 ጋር አብሮ መሥራት፣
8.ራስን ማስተዋወቅ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ዕድገትንና ብቃትን የሚጠይቅ በመሆኑ ከዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት፣ 

ይህንን ለማድረግ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈና በጥናቱ ላይ የተመሠረተ የአገር መለያ (ብራንድ) መለየትና መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ 

የአገር መለያ (ብራንድ) ለመለየት በአገርአቀፍ ደረጃ ሥራውን የሚመራ ግብረ ኃይል ማቋቋም አስፈላጊ ነው። ዋሊ ኦሊንስ በእንግሊዝ የብራንድ ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸውም እንደሚሉት ከሆነ አገርን ማስተዋወቅ ሰባት ደረጃዎች ማለፍ አለበት፣

1.ከመንግሥት፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከጥበብ፣ ከትምህርትና ከሚዲያ የተፈጠረ ግብረ ኃይል በማቋቋም መርሐ ግብር እንዲቀረፅ ማድረግ፣
2. አገሪቱ በራስ ዜጎችና በውጭ ዓለም ሰዎች እንዴት እንደምትታይ በጥናት መለየት፣
3.የተገኘውን ውጤት ከተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ጋር የምክክር መድረክ በማድረግና በማወዳደር የአገሪቱን ጠንካራና ደካማ ጎን መለየት፣

4.ኘሮፌሽናል ባለሙያዎችና አማካሪዎችን በመጠቀም የብራንድ ስትራቴጂ የሚመራበትን ማዕከላዊ ሐሳብ መፍጠር፣ ማዕከላዊ ሐሳቡ በጣም ጠንካራና በቀላሉ ሊያያዝየሚችል ሐሳብ ሆኖ የአገሪቱን የተለየ ልዩ ገጽታ የያዘ መሆን አለበት፡፡ ሌሎች ፕሮግራሞች በዚሁ የሚመሩ መሆን አለባቸው፡፡

5. ማዕከላዊ ሐሳብ ሎጎን ጨምሮ የሚተላለፍበትን ዘዴዎች መለየት፣
6.የተቀረፀው ማዕከላዊ ሐሳብ ከቱሪዝም፣ ከኢንቨስትመንት ለመሳብና ከኤክስፖርት እንዴት እንደሚቀናጅና ለእያንዳንዱ አድማጭ፣ ተመልካች (ሸማች) ተስማሚ 
የሚሆን መልዕክት መቅረፅና መተግበር፣
7. ከግብረ ኃይሉ ጋር የሚያገናኝ ሥርዓት መዘርጋት ናቸው፡፡

ቡና የአገራችን መለያ (ብራንድ) መሆን አለበት
ስንታየሁ ግርማ አይታገድ
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው SintayehuGirma57@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡

Related Post