አርእስተ ዜና
Mon. May 6th, 2024

የቁርዓን ቤት ትዝታዎች – 1

Apr7,2022
የቁርዓን ቤት ትዝታዎች - 1
የቁርዓን ቤት ትዝታዎች - 1

በሃውለት አህመድ – አልሃምዱሊላህ 8 ዓመት ያለማቋረጥ ቁርዓን ቤት ተመላልሼ ቀርቻለሁ። ሕፃናት እያለን (1980ዎቹ መጀመሪያ) ደብረ ብርሃን ከተማ የሙስሊሞች ቁጥር በጣም ጥቂት ነበር።

ከአጠቃላይ ነዋሪው 5 በመቶ ቢሆን ነበር። ይሁንና 3 ቁርዓን ቤቶች ነበሩ። በሌላ ችግር ካልሆነ በቁርዓን ቤት ዕጥረት ያልቀራ አይገኝም። ሶስቱ አሽር ጌቶች አባዬ ሸህ ማህሙድ, ሸህ ዓሊ ሞጆ, አባባ ሸሆቹ ይሰኙ ነበር (ሁሉም ወደ አኼራ ሄደዋል፤ አላህ ጀነተልፊርደውስን ይወፍቃቸው)።

ክፍያ በወር 1 ብር ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ኑሮ ተወደደ ተብሎ 50 ሳንቲም ተጨመረ። የመጨረሻ ቁርዓን አጠናቅቄ ስወጣ ክፍያዋ ያቺው 1.50 ነበረች። ቁርዓን ከመቅራቱ በላይ ከባዱ ብርዱ ነበር። አሁን ላይ ደ/ብርሃን ‘በረደኝ’ የሚል ሰው ስሰማ በመጠኑ እገረማለሁ። ያለ ማጋነን ቁርዓን ለመቅራት ስንሄድ ጠዋት ላይ የነበረው ብርድ እግር በስለት የተቆረጠ ያህል ይሰማ ነበር። አሁን ጭራሽ ብርድ አለ እንዴ? 😁

የኔ ልጆች በእኛ የሕፃንነት ዘመን ስማርት ስልክ፣ ታብሌት ምናምን ይቅርና ቴሌቪዥንም እንደማናውቅ ሬድዮም በጣም ጥቂቶች ቤት የሚገኝ ብርቅ ዕቃ እንደነበር ነግሬአቸው እንዴት በዚያ ‘ጨለማ’ ዘመን በህይወት እንደቆየሁ እያሰላሰሉ ቆዘሙ።
ሬድዮ ራሱ ምን እንደሆነ ለማስረዳት ብደክምም የገባቸው አልመሠለኝም። ከሁሉም የገረማቸው በአንድ ወቅት ፊልም ስንመለከት በቀሰም ቀለም እየነከረ ሳስቶ በለሰለሰ ቆዳ ላይ የሚጽፈውን ሰውዬ እያሳየኋቸው ‘እኛም በተላገ ጣውላ ላይ እንደዚህ ቀለም ነክረን እየከተብን/እየፃፍን ነው ቁርአን የቀራነው ስላቸው ፊልሙን ትተው በድንጋጤ እኔ ላይ አፈጠጡ። የሆነ ከ18ኛው ክ/ዘመን የመጣሁ ዓይነት ተሰምቷቸው መሠለኝ። 😂
እኛ አሽር ቤት (የታተመ) ቁርአን የነበረው በጣም በቁጥር ነው። በቁርአን ለመቅራት ቢያንስ 5 ጁዝዕ መድረስ ያስፈልጋል። ከቤት ቁርአን ቢኖርም እንኳን እስከ 5 ጁዝዕ ድረስ በለውህ መቅራት ግዴታ ነበር።
አምስት ጁዝዕ ለመድረስ ቢያንስ ከ2-3 ዓመት ይፈልግ ነበር። መድ (ቀለም) የምናዘጋጀው ከብረት ምጣድ ጥላሸት ነው። እንዲያጣብቅና እንዲያብረቀርቅ ስኳር እንጨምርበታለን። አብዛኛውን መድ ጠጥተን ነው የምንጨርሰው። (ወይ ልጅነት! ጥላሸት በስኳር የምንጠጣ ጀግኖች) ቀሰም መጻፊያውን ማዘጋጀት በጣም ቀላል ነበር። ምክንያቱም ደ/ብርሃን መቃ (ሸምበቆ) በየቦታው የሚያድግ ተክል ስለነበር።
ያኔ የምንቀራው ልጆች ከ50 – 70 እንደርስ ስለነበር አሽር ጌታው ለሁሉም መክተብ ስለማይችሉ ትንሽ ከፍ ያሉት (በተለይ በቁርአን የሚቀሩት) ዝቅ ላልነው የመክተብ ግዴታ አለባቸው። ሁሉም ወንዶች ነበሩ። እናም ለነርሱ የካልሲ ኳስ ሰፍተን ማቅረብ ግዴታ ነበር። አለዚያ አይከትቡልንም፤ ‘አልከትብም አለኝ’ ብለህ ለአሽር ጌታ መናገር ያስገርፋል። ስለዚህ የታላላቅ ወንድሞቻችንን ካልሲ እነዚህ ከታቢዎች ጨርሰውብናል (በያላችሁበት ሰላም ብያለሁ እናንተ ጸረ-ካልሲዎች 😁)።
ወቅቱ ሲደርስ እኔም ከታቢ ሆንኩ። ብቸኛ ሴት ከታቢ። የኔ ለዚህ መድረስ ለወንዶቹ የምሥራች ነበር። ለኔ እየጣሉ እነሱ ወደ ኳስ። demand and supply gap ተፈጠረ። ስለዚህ እኔም ‘ክፍያ’ መጠየቅ ጀመርኩ። በመጀመሪያ አዝራር (የልብስ ቁልፍ) ከዚያ ጸጉር ማስያዣ እና የመጨረሻው ደግሞ ጠጠር ከረሜላ። አሁን ሳስበው በየቀኑ የኔን ‘ክፍያ’ ለማምጣት ቤተሰቦቻቸውን ምን ብለው አስቸግረው ይሆን? (በያላችሁበት ይቅር በሉኝ) 😊
… በቀጣይ አለንጋና ሳማ …

Related Post