አርእስተ ዜና
Fri. May 3rd, 2024

በሙርሌ ታጣቂዎች የታገቱ ህጻናትን ለማስመለስ እየተሰራ ነው

Feb11,2022
በሙርሌ ታጣቂዎች የታገቱ ህጻናትን ለማስመለስ እየተሰራ ነው

በሙርሌ ታጣቂዎች የታገቱ ህጻናትን ለማስመለስ የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ ሃይል ጋር በመሆን በጋራ እየሰራ ይገኛል በማለት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን ዲማ ወረዳ ኡኩቡ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የካቲት 2/ 2014 ዓ.ም ከለሊቱ በ5 ሰአት ከደቡብ ሱዳን አጎራባች አካባቢ ሰርገው የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች አምስት ህጻናትን አግተው ወስደዋል።  እነዚሁ ታጣቂዎች በስደተኞች ጣቢያው በከፈቱት ተኩስም ሁለት ሴቶችን አቁስለዋል።  በተመሳሳይ በቀጣዩ ቀን ማለትም የካቲት 3/ 2014 ዓ.ም ዳግም ታጣቂዎቹ በጎግ ወረዳ በከፈቱት ጥቃት የአንድ ግለሰብ ህይወት አልፏል።



በስፍራው የተፈጠረውን ክስተት ለማጣራትና ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ እንዲሁም የታገቱ ህጻናትንም ለማስመለስ የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ ሃይል ጋር በመሆን በጋራ እየሰራ ይገኛል። ከዚህ በፊት የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ከአጎራባቹ የሙርሌ ጎሳ ሰርገው በሚገቡ ታጣቂዎች ተመሳሳይ የህጻናት እገታና ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።

የአካባቢውን ጸጥታ ለማስጠበቅ የሁለቱ ሃገራት አጎራባች ክልሎች አስተዳደርና የፌደራል ፖሊስ ችግሮችን ለመፍታት ባደረጉት ጥረት በአካባቢው በታጣቂዎች ይፈጸሙ የነበሩ የሰረጎ ገብ ታጣቂዎችን እንቅስቃሴ ለመቀነስ ተችሎ ነበር።



አሁን የተፈጠረውን ክስተት በተመለከተም የታገቱትን አምስት ህጻናት ለማስመለስ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር በሁለቱም ሃገራት አጎራባች አካባቢዎች የሚኖሩ የሃገር ሸማግሌዎችንና የማህበረሰቦቹን ተወካዩች ባሳተፈ መልኩ ዘላቂ ሰላምን በአካባቢው የማስፈን ጥረት ይቀጥላል።

Related Post