አርእስተ ዜና
Fri. Nov 22nd, 2024

የኢኮኖሚያዊ ሁኔታችን ከሞላ ጎደል ይህንን ይመስላል

የኢኮኖሚያዊ ሁኔታችን ከሞላ ጎደል ይህንን ይመስላል
የኢኮኖሚያዊ ሁኔታችን ከሞላ ጎደል ይህንን ይመስላል

በሙሼ ሰሙ – የቀድሞ የኢ.ዴ.ፓ መሪ እና የኢኮኖሚ ባለሙያ የቀረበ – የኢኮኖሚ መረጃ ተወደደም ተጠላ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች፣ በአፍሪካ ልማት ባንክና በአበዳሪ ተቋማት ምዘና የሀገራችን የ2021/22 ኢኮኖሚያዊ ሁኔታችን ከሞላ ጎደል ይህንን ይመስላል!

ከጠንካራ ጎኑ ልጀምር።
የወጭ ንግድ 12 % አድጓል፣ ገቢ ንግድ በ 8.1 % ቀንሷል በዚህም ምክንያት የከረንት አካውንት ጉድለት ከ5.3 ወደ 4.4 % ወርዷል። መንግስት ከቀረጥ የሚያገኘው ገቢ በ16% ያደገ ሲሆን ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ ግን 0.8 ቀንሷል። 20/21 የስንዴ ምርት በ1.6 በመቶ በማደግ 5.18 ሚሊየን ቶን እንደሚደርስ ተገምቷል። በፈታኝ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ኢኮኖሚያችን 6% እድገት አሳይቷል።



ወደ አሳሳቢው ጉዳይ እንምጣ
አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት በ2020 ከ6 እስከ 8% የሚደርስ እድገት ያሳያል ቢባልም በአማካይ ከ2.1% እንደማይዘል እየተገመተ ነው። ግሽበቱን ወደ አንድ ዲጅት የማውረድ ምኞት ቢኖርም የግሽበት ምጣኔውን በኢምፖርትድ ግሽበት ልክ እንኳን መግታት ስላልተቻለ ግሽበቱ ወደ 34.5 በመቶ አሻቅቧል። ግሽበቱ በቀጣይም በታወቁ ምክንያቶች እንደሚባባስ ይጠበቃል።

በድህነት ወለል ላይ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ከ24 በመቶ ወደ 27 በመቶ ያደገ ሲሆን ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጎች ወደ ድህነት ወለል እንዳሽቆለቆሉ ይገመታል። ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ገቢያቸው እድገት ባለማሰየቱ፣ ግሽበቱን የሚቋቋም ጭማሪ ስላላገኙ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም በመዳከሙ፣ በነዳጅና መብራት ጭማሪ፣ በስራ አጥነትና በዋጋ ንረት ስለዳሸቀ ገቢያቸውን ሙሉ በሙሉ አጥተውታል ወይም በግማሽ ያህል ቀንሷል።

ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት (FDI) ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት( GDP) ላይ ከነበረው የ20 በመቶ ድርሻ ወደ 2.2 በመቶ አሽቆልቁሏል። ሃዋላ (Remittances) ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ከነበረው የ10 በመቶ ድርሻ ወደ 5.3 በመቶ አሽቆልቁሏል።

እዳ የመከፍል አቅማችን ሪስትራክቸር ቢደረግም በ2024 አንድ ቢሊየን ዮሮ እዳ መክፈያው ጊዜ ስለሚደርስ ብድር የመክፈልና ተጨማሪ የመበደር አቅማችን ጥያቄ ላይ ወድቋል። እዳ የመክፈል ምዘናችን በአማካይ CCC ላይ ወድቋል። መንግስታዊ እዳችን ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት( GDP) አንጻር ሲታይ 55.43 % የደረሰ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት አንጻር 467 ዶላር ድርሻ ይኖረዋል።



በሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ መሰረት ጥረቶች ቢኖሩም ኑሮ ተወዷል፣ ገቢ አላድግ ብሏል፣ ግሽበቱ ናላ የሚያዞር ነው፣ አቅርቦቱ በሚፈለገው ፍጥነት እየሰፋ አይደለም። የውጭ ምንዛሪው ተመናምኗል። እዳ የመክፈል አቅማችን ሳስቷል። ይህም ሆኖ በ2020 የሀገራችን ኢኮኖሚ 6.1% ያደገ ሲሆን ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ 2.3 ቀንሷል። ይህ እድገት የትና ወደ ማን ኪስ ገባ ?! መሰረታዊ ጥያቄ ነው።

– ምን ይሻላል?
የብዙዎች ጥያቄ እንደሚሆን እገምታለሁ። መፍትሔዎችን በሚመለከት በግል በቡድን፣ በስብሰባ በሴሚናር ወዘተ ብዙ ተብሏል። ልብ ካለ ከበቂ በላይ ተብሏል የሚል እምነት አለኝ። በቅርቡ ብልጽግና ጉባኤ ያካሂዳል። በዚህ ጉባኤ ላይ ከፖለቲካዊ ሹኩቻዎች በላይ ፖርቲው በጥልቀት ሊነጋገርበትና መፍትሔ ሊያበጅለት የሚገባው ጉዳይ ኢኮኖሚው ፈተና ነው። ዛሬ በድህነት፣ በኋላ ቀርነት፣ በኑሮ ውድነት፣ በረሀብና በሙስና ላይ ካልተዘመተ ጦርነትና የፖለቲካ ሽኩቻ ያላፈረሳትን ሀገር ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ሊጥላት ይችላል።

ለዚህ ደግሞ አሁንም በተለምዶ በበጀት ስራ በተጠመዱ ሚኒስትር መስርያ ቤቶች፣ አማካሪና ጽ/ቤቶች አማካኝነት ችግሩን ለመፍታት ከመወጣጠር ይልቅ ለችግሩ ስፋትና ጥልቀት የሚመጥኑ በተለይ በኢኮኖሚያዊ ሪፎርም ላይ ብቻ አትኩረው የሚሰሩና አማራጭ መፍትሔ የሚያመነጩ ቋሚና ሙሉ ሀላፊነት የሚወስዱ ተቋማትን ማቋቋም ቢያንስ ችግሩን ለመግታት ወሳኝ እርምጃ ነው።

Related Post