አርእስተ ዜና
Fri. Apr 19th, 2024

አንገቴን አልደፋም!!

Mar1,2022
አንገቴን አልደፋም!!
ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ውድ ነው። ነገር ግን ባለመሬቱ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነው። ሂድ ኬኒያ፣ ዛምቢያ፣ታንዛኒያ ….ቁጠር ሃምሳ ሃገር። ከቦሌ አብዮት አደባባይ የሚደርስ አጥር ታያለህ። “ይህ መስሪያቤት ምን ይባላል?” ትላለህ። አገሬዎቹ በግርምት ያዩሃል። “ይኼማ የሰር ሪቻርድ ማንትሴ መሬት ነው ይሉሃል። ጭንቅላትህን ይዘህ ትጮሃለህ።

“የሱ እንደውም ትንሹ ነው…ሰር እከሌና ቤተሰቡ ደግሞ …” ይሉና በኪሎሜትር ሲጠሩት ከአዲስ አበባ ቢሾፍቱ የሚደርስ መሬት ባለቤት መሆኑን ይነግሩሃል። በዚህ ሁሉ መሃል አንድ ጥያቄ ትጠይቃለህ።
“እናንተስ ምን ያህል መሬት አላችሁ?”
….ተያይተው ይሳሳቃሉ።

“ማ ብራዛ ! …እዚህ ሃገር ሃብታም ነጭ ብቻ ነው። እኛ የነርሱን ሃብት ተጠግተን እንጀራችንን እንጋግራለን እንጂ ሃብትና መሬት ብርቃችን ነው” ይሉሃል። በሳቃቸውና በፌዛቸው ውስጥ ግን ከባድ ቁጭት ታያለህ።

ያኔ የሆነ ነገር ውርር ያደርግሃል…ኩራት ኩራት ይልሃል…ኢትዮጵያዊነትን ከነትርጉሙ መናገር ያምርሃል።
” አንድ ነገር ልንገራችሁ?…እኔ ሃገር ብትመጡ ነጭ እንኳን መሬት ሊኖረው በስሙ አንድ ክፍል ቤት መግዛት አይችልም። እኛ በጣም ድሆች ብንሆንም በሃገራችን ውስጥ ሃብታሞቹም እኛው ራሳችን ብቻ ነን። ህንጻውም መሬቱም ጠቅላላ ሃብቱም የኛው የኢትዮጵያውያን ብቻ ነው”

ይህንን ሰምተው “ዩ ማስት ቢ ፍሮም ኢቶቢያ” ሲሉህ ያለምንም ማጋነን የደምህ ሙቀት በአንዴ አናትህ ወጥቶ በደስታ ሲያሰክርህ ይሰማሃል። አባቶችህ በሰው ፊት አንገትህን ቀና አድርገህ አንድትሄድ ስላደረጉህ …በኩራት የምትናገረው ታሪክ ባለቤት ስላደረጉህ የምታመሰግናቸው ያኔ ነው።

ወጣ በል ከሃገርህ…እዚሁ ጎረቤት ሃገር ሂድ። አፍሪካውያኑ አማራ ሁን ኦሮሞ፣ ከንባታ ሁን ሃዲያ፣ ትግሬ ሁን ምንትስ የሚያውቁልህ ነገር የለም። ከኢትዮጵያ መምጣትህንና ኢትዮጵያዊ መሆንህን ብቻ እንጂ ።

ደስ ብሏቸውም…ሳይወዱ በግድም ብቻ በምንም ስሜት ውስጥ ሆነው የነጻነትህንም፣ የጀግንነትህንም፣ የጥቁር ህዝቦች ነጻነት ቀንዲልንትህንም ታሪክ ሃገርህን ጠርተው የሚያወርሱህ ኢትዮጵያዊ ስለሆንክ ብቻ ነው።

ስለሃገርህ ስታወራቸው አፋቸውን ከፍተው የሚያዳምጡህ ስለሆቴልህ፣ ስለፋብሪካህ…ስለመንገድህ…ስለመንግስትህ፣ ስለትምህርትህ ስትናገር አይደለም…ስልጣኔ ወይም ዘመናዊነት ለነርሱ ባዶ ቅል ነው። ካንተ ይበልጥ ያዩት ነገር ግን እየኖሩ የማይኖሩበት፣ እየጎመጁ የማይበሉት ስልጣኔ ነው ሃገራቸው ያለው። እነርሱ እህ! ብለው አይናቸውን ተክለው የሚያደምጡህ በሃገርህ አንተ ጥቁሩ ሰው እና መጤው ነጭ ነዋሪ ያላችሁን ልዩነት ስትነግራቸው ብቻ ነው።

ስማኝማ! እኔ እድል ገጥሞኝ ባየኋቸው የአፍርካ ሃገራት የሚገጥመኝ ነገር የነገርኩህን አይነት ታሪክ ነው። ከሁሉ አብልጬ ኬኒያን እወዳታለሁ። አገሪቷ ሰልጥናለች። ኑሮው ይመቻል። እኛ ጋ ብርቅ የሆነ እዚያ የሰለቸ ነገር ነው። ከሞል አቅም እዚህ ስሙ ፣ እዚያ ግን ራሱ አለ። ቀላሉን ልንገርህ ብዬ ነው። ግን ደግሞ ህዝቡን ጠጋ ብለህ አውራው። ያሳዝንሃል። በሃገሩ ላይ የምር ኑሮ እየኖረ አይደለም…

ከብዙ ገጠመኞቼ አንዱን ልምዘዝልህማ! …ባለፈው ናይሮቢ የሄድኩ ጊዜ አንድ መካነ አራዊት ለመጎብኘት ከወዳጆቼ ጋር ወጣሁ። sheldrik elephant orphanage ይሉታል ቦታውን። ስደርስ ለመግባት በር ላይ ወረፋ አስያዙኝ። አንዲት ነጭ አሮጊት ዴስክ ላይ ተቀምጣ ከእያንዳንዱ ጎብኚ 27 ዶላር መግቢያ ትቀበላለች። ቀና ብዬ ሳይ የፓርኩ ባለቤት ሰር ዴቪድ ሼልድሪክ ምናምን የሚባል እንግሊዛዊ ሰውዬ ነው። አስታውስ…ያለሁት ሎንዶን ሳይሆን ናይሮቢ ነው።

በግርምት ይሁን በንዴት አቅሌን የሳትኩም መሰለኝ። ብቻ ገብቼ ወደውስጥ ሳይ የነጭ መዓት ተሰብስቦ የዝሆን አልሞሌዎችን በግዙፍ ጡጦ ወተት የሚያጠጡ የተጎሳቆሉ ጥቁሮችን እንደጉድ ያያል።

የሆነ ነገሬ ሲቃጠል ተሰማኝ።የምሬን ነው። ዝሆን በቁሙ ሳይ የመጀመሪያዬ ቢሆንም አይኔ ያፈጠጠው ግን እነዚያ ከዝሆኑ ጋር ሲታገሉ በጭቃ የተጨማለቁ ጥቁሮች እና ህይወት የሰለቸው የመሰለ ፊታቸው ላይ ነው። በቆሻሻ ቱታ፣ በጭቃ በላቆጠ ቦቲ ጫማ ውስጥ ሆነው አይናቸው ህይወት አልባ ነው። በገዛ ሃገርህ፣ በገዛ የተፈጥሮ ሃብትህ፣ በገዛ መሬትህ ነጭ ሁሉንም ነገርህን ወስዶ ጉልበትህን በቀላሉ ይበዘብዛል። 27 ዶላር ከእያንዳንድህ እየተቀበለ ለነዚህ ሰራተኞች የሚከፍለው ስንት እንደሆነ እግዜር ይወቅ። ሽልንጋቸውንም እንጃ…

አያስጠላም? ይህንን እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ልብህ ፈቅዶ ይቀበለዋል?…አታምጽም…ምቾት ይሰጥሃል ?…አንተ ብትሆን የዚህን ትዕይንት ፈተና ቆመህ መጋፈጥ ትችለዋለህ? እነዚያን ጥቁሮች ረስተህ በዝሆን አልሞሌዎች ትፈነድቃለህ?…ትዝናናለህ?

ትንሽ ወጣ አልኩ መሰለኝ…በፈረንጆቹ መሃል ቆሜያለሁ…ጮክ ብዬ በአማርኛ ሃገሩንም ነጩንም ሙልጭ አድርጌ ተሳደብኩ። (የሰው ሃገር ነጻነት ታጋይ አይደለሁም…ቼ ጉቬራ አይደለሁም…ግን እንዲወጣልኝ ብቻ ነው በቋንቋዬ የተነፈስኩት)

ጓደኞቼ ሳቁ። ያልኩት ያልገባቸው ነጮችም በቋንቋዬ ተገርመው ይሁን እንጃ ብቻ አብረው ሳቁ።ቀይ ድዳቸው አስጠላኝ…ሃገሩን ‘ፎርግራንትድ’ የወሰዱ ናቸውና ደስ አላሉኝም…ግልፍጦች!!

እኔ እንዲህ አልወረድኩም…አልዋረድምም… ኢትዮጵያዊ ነኝ…ለጊዜው ዳቦ ጉዳዬ ቢሆንም ክብር ግን የዘለዓለም እጣ ፈንታዬ ነው።
ዓድዋዬ ለዘለዓለም ኑሪልኝ!!

ምኒሊክ ሁሌም ንጉሴ ነህ።
አንገት በተደፋባት አህጉር የኔ አንገት ብቻ ቀና ያለው በናንተ ነው!! ⁾⁾

Related Post