አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

የቁርአን ቤት (የአሽር ቤት) ትዝታዎች – 2

የቁርአን ቤት (የአሽር ቤት) ትዝታዎች - 2
የቁርአን ቤት (የአሽር ቤት) ትዝታዎች - 2

በሃውለት አህመድ – አለንጋ – አለንጋ ክብሯን ካጣች ሰንብታለች። የኔ ልጆች በጣም ያበሳጩኝ ጊዜ በዕድሜያቸው ምናልባት 3 ወይ አራት ጊዜ ገርፌያቸው ይሆናል። ለዚያውም ሁለቴ ወይ ሶስቴ ሾጥ ባደርጋቸው ነው።

ይቺም ግርፊያ ሆና አንዴ ተቀጥተው ዓመቱን ሙሉ ሲያለቃቅሱበት ማየቴ ይገርመኛል። ይባስ ብለው እንደ ምልክት ሁሉ ይጠቀሙበታል። ‘መቼ ነው ይሄ የሆነው? ያኔ ከተገረፍን በኋላ ነው በፊት? ያኔ ከመገረፋችን በፊት ትዝ ይልሻል? እናቴ የገረፈችኝ ቀን እንትን የሚባል ፊልም አምልጦን እንደነበር አታስታውስም?’ ወዘተ እየተባባሉ ሊያሸማቅቁኝ መሞከራቸው አስቂኝ ነው። በልጅነቴ ዓመቱን ሙሉ እየተገረፍኩ ቆዳዬ ለደነደነ ለኔ ዓይነቷ በዕውነቱ የልጆቼ complain እጅግ አስቂኝ ነው። 😂

አሽር ቤት የምንገረፍበት አለንጋ የተሰራው ለበረባሶ/ሸረፈዲ ጫማ መሥሪያ ከሚያገለግለው ጎማ ነው። ጎማው ብቻውን ቢሆን ደግ ነበር። ውስጡ ጠንካራ ክሮች ስላሉት የጎማው ጥብቀት ለኛ ቆዳ ጠር ነበር። እርግጥ ነው ቁርአን ቤትና አለንጋን የሚነጣጥል ኃይል የለም። ልትቀራም ልትገረፍም ነው የምትሄደው።

አለንጋው ተገርፈንበት እየሳሳ ሲሄድ የበለጠ ስለሚያም በአዲስ ጎማ እስኪተካ በናፍቆት እንጠብቃለን። ምክንያቱም መሳሳቱ ሁለት ወይ ሶስት ቦታ ስለሚሰነጥቀው በአንድ ስንዝር ሶስቴ እንደመገረፍ ስለሚቆጠር ነው። በነፍስ ወከፍ እንደጥፋታችን የምንገረፈው እንዳለ ሆኖ በጅምላ ከምንገረፍባቸው ‘ምክንያቶች’ መካከል

– አንድ ልጅ ሲረብሽ ሁላችንም እንገረፋለን።
– ጮክ እያልን መቅራት ስለሚጠበቅብን የጥቂት ልጆች ድምጽ ደከም ካለ ሁላችንም እንገረፋለን።
– አሽር ጌታ በሌላ ጉዳይ ተበሳጭተው ከመጡ እንገረፋለን።
– ውሃ የምንጠጣው ከአንድ በርሜል ነበር። መጠጫዋ አንድ ጣሳ ነች። ትጠጣለህ፤ ጣሳዋን በርሜሉ ውስጥ ትጨምራለህ። ሌላውም ይመጣል እንደዚያው። ማን እንደተዋት ሳይታወቅ ጣሳዋ ከበርሜሉ ውጪ ከተገኘች እንገረፋለን።

– አሽር ጌታችን አለንጋውን የት እንዳስቀመጡት ከጠፋ በኋላ ሲገኝ እንገረፋለን። (ደብቃችሁ ነው ስለሚባል)
– ቁርዓን አስተካክሎ የማይቀራ አንድ ልጅ ከተገኘ ለሁላችንም ይተርፋል። ሌላም ሌላም…

ግርፊያ ከመልመዳችን ብዛት ልንገረፍ ስንል ምንም አንሸማቅቅም። በቃ መገረፍ ነው። ጭራሽ የግርፊያውን ሰንበር ለቤተሰብ ስታሳይ ‘የአሽር ጌታ አለንጋ መድኃኒት ነው። ቁርአንም ትምህርትም እንዲገባህ ነው። ጥፋ ከዚህ’ ትባላለህ። ከተነጫነጭክ ከቤተሰብ ተጨማሪ ቁንጥጫ ይጠብቅሃል። ስለዚህ ሕመምና ሰንበር ከአዕምሮ ንቃት ጋር ስላላቸው ግንኙነት እያሰላሰልክ ወደ ጉዳይህ ትሄዳለህ።

በዕውነት አብዛኞቻችን ያኔ መቀጣታችን ለኋለኛው ሕይወታችን የጠቀመን ይመስለኛል።
ጽሁፉ ስለረዘመብኝ የሳማውን አሳድሬዋለሁ።
…. በቀጣይ ሸሪካና ዋስ ….
ጁምዓ ሙባረክ። 😊

Related Post