አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024
ጠጠው በል!!

በሠላኩ ብርሃኑየዛሬ 29 ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማኋት ቃል ናት። ኢህአዴግ የገባ ሰሞን ሰፈራችን በታጋይ ተጨናንቆ ነበር። አንዳንድ የሰፈራችን ሰዎችም የውስጥ ታጋዮች ሆነው በራችን ላይ ለመቆም ሁሉ ከልክለውን ነበር። እናም አንድ “መሬ” ብለን የምንጠራውን ባለቁምጣ እና ባለጠመንጃ ታጋይ ግንቦት ሃያ በመጣ ቁጥር አስታውሰዋለሁ።

አንድ ቀን ሰብሰብ ብለን በቆምንበት ሲመጣ አየነውና “ሳናስጠጣ” መበተን ጀመርን። ትከሻዬን ከበድ ሲለኝ ዞር ብዬ ሳይ ከሱው ጋ አይን ለዓይን ተገጣጠምን።
የዚያን ቀን የቆመልኝ እግዚአብሄር ከዛሬ የሙት አመት ቆጠራ አዳነኝ።

ስላየሁት ብቻ ሲያፈጥብኝ ሩጫዬን ጀመርኩ። ክላሹን ከትከሻው አውርዶ …ጠጠው በል!! እያለ ….እየሮጠ ሲያቀባበል የጠመንጃው ድምጽ ተሰማኝ። ሩጫዬን አላቆምኩም። ከኋላ ብዙ የሰፈሬ ሰዎች እንዲተወኝ እየለመኑት በሩጫ ይከተሉናል።ምክንያቱን ሳላውቅ የዚያ ታጋይ ክላሽ መጋዚን (ጥይት መያዣ) ተፈትቶ መሬት ወደቀ። እሱን ለማንሳት ሲቆም እኔም ሰው ግቢ ዘልዬ ገባሁ።

የገባሁበት ገብቶ ማጅራቴን ጨምድዶ አወጣና አንበረከከኝ። ጠመንጃውን በድጋሚ ወደኔ ወደረው። በዙሪያችን የተሰበሰቡት የሰፈር ሰዎች ምልጃ…የእናቴ ለቅሶ ፣ መሬት ለመሬት መንከባለልና የሚያሳዝን ልመና…… በድንጋጤ ደርቄ በተንበረከክኩበት ህልም ህልም ያህል ይሰማኛል። ብሞትም የምረሳው አይመስለኝም። ለእግዜር እግዜር ይስጠውና የዚያን በሰፈሩ የታወቀ ጨካኝ ታጋይ ልብ አራራልኝ።

በያዘው የሸንበቆ ዱላ ወገቤን ለምጦኝና ጭንቅላቴን በኩርኩም ቆግቶኝ በማላውቀው ቋንቋ ሰድቦኝ ሰዳድቦኝ ጠመንጃውን እያነገተ ጥሎኝ ሄደ።
እናም ያኔ የደነገጥኩ ይኸው አሁን ድረስ “ጠጠው” እንዳልኩ ነኝ…

አንተ ታጋይ… አሁንም ድረስ ሰራዊቱ ውስጥ ካለህ……(ሃብታም ሆነህም ይሆናል….ሞተህም ይሆናል…ባለስልጣን ሆነህም ይሆናል…) ብቻ እንኳዕ ለጉንበት 20 ብሰላም እብፅሃኩም
ከፈቀድክልኝ አሁን ልሩጥ?
ቂቂቂቂቂ
*ጠጠው በል (ቁም! ማለት ነው )
በዚህች ቃል ሌላም ትውስታ አለኝ! በኋላ እፖስተዋለሁ

Related Post