አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

የገበያ መንፈስ ምን ተወግቶ ነው ግን እንዲህ የቀዠበው ?

የገበያ መንፈስ ምን ተወግቶ ነው ግን እንዲህ የቀዠበው
የገበያ መንፈስ ምን ተወግቶ ነው ግን እንዲህ የቀዠበው

በመላኩ ብርሃኑ

መንግስት መኪና አሽከርካሪዎችን የራሳችሁ ጉዳይ ሊል ጫፍ ላይ ደርሷል። በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት መንግስት ለድጎማ በማወጣው ወጪ 10 ቢሊዮን ብር ከስሬያለሁ እያለ ነው። ይህ መረጃ በርግጥም እውነት ከሆነ ከባድ ነው።ነዳጅ አምራች ሃገራት እንኳን የኢትዮጵያን ያህል በረከሰ ዋጋ ነዳጅ እንደማያቀርቡ ሲነገር ሰምተን እናውቃለን። በዚህ መጠን ኪሳራ ማስተናገድ ከጀመርን ግን የሆነ ቦታ ቆም ማለት ይኖርብናል።

በርግጥ ከድጡ ወደማጡ እየተንደረደረ ባለው ኢኖሚያችን ላይ ይህ ሲደመር ኑሯችንን ከባድ ያደርገዋል። አዳዲስና ብዙሃኑን የማይጎዱ መንገዶችን አጥብቆ ማሰብ ይጠይቅ ይሆናል።መፍትሄ ማመንጨት በመንግስት ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሰዎች ስራ ነው። ይህንን ካልሰሩ ታዲያ የማንን ጎፈሬ ያበጥራሉ?

እኔን የሚያሳስበኝ ግን በከፋ መልኩ ወደኛ እየመጣ ያለው ከባድ የኑሮ ጫና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚያሳስብ ነገር ሆኖ አለመገኘቱ ነው። የሆነ ክፍል ቋጥኝ ቢወድቅበት እንኳን ቅም የማይለው ‘ኪሱ ጢቅ ብሎ የሞላ’ አይነት ነው። ብዙሃኑ ደግሞ ኪሱ ጭራሽ ሳንቲም ለመያዝ እንኳን ጥንካሬ አጥቶ የሳሳ ሆኗል።
ሃብታሙ የበለጠ ሃብታም እየሆነ ሲሄድ ደሃው የበለጠ ደሃ እየሆነ ነው።

መንግስት በቅርብ ቀን የነዳጅ ዋጋን ምናልባት በሊትር ከ47 እስከ 52 ብር ሊያደርሰው ይችላል።አንድ ሊትር በአንድ ዶላር ከሆነ ነው እሱም። በጥቁር ገበያ እንዳታሰሉት። እንዲያ ከሆነ ‘ኦልሬዲ’ 70 ብር ገብቷል።

የኛ ገበያ ‘ክሬዚነት’ እዚህ ላይ ፍጥጥ ብሏል። የአዲስ አበባ መንገዶች በመኪኖች እየሞሉ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ‘መንገድ ላይ የመኖር’ ያህል አሰልቺ ሆኗል። በተለይ ጠዋት እስከ 3 ተኩል ፣ ከሰዓት ከ 9 ሰዓት ጀምሮ እና ማታ ከ2 ሰዓት ጀምሮ መንገዶቻችን ‘በመኪና ጢቅ’ ይላሉ። ነዳጅ የሚያልቀው ጉዳይ በመሙላት ሳይሆን መንገድ ላይ በመንፏቀቅ ነው።አንዱ ብክነት እዚህ ላይ ነው።

የመኪና መብዛት ብቻ ሳይሆን ዋጋውስ ምን እየሆነ ነው?.
..በዓለም አቀፍ ደረጃ ነዳጅ ዋጋው ሲጨምር በብዙ ሃገራት የመኪና ዋጋ ቀንሷል። በተቃራኒው ግን በኢትዮጵያ የመኪና ዋጋ በየቀኑ ሊባል በሚችል መልኩ እየጨመረ ነው። መንግስት መኪና መግባትን ላለማበረታታት ብሎ ቀረጡን ከፍ ቢያደርገውም ሰዉ ግን አሁንም ነዳጅ በተወደደበት ጊዜ እንኳን ዋጋው ጣራ የወጣ ነዳጅ በሊታ ባለከባድ ሞተር መኪና እንደቆሎ መሸመቱን አልተወም።

ለምን እንደሆነ ይገባችኋል ግን ? ….እኔ ግራ ገብቶኛል። ለነገሩ መንግስትም የመኪና ማቆሚያ ሰርቶ መሸቀሉን ነው እንደትልቅ ስኬት እየቆጠረ ያለው መሰለኝ።
እዚህ ሃገር ግን ስኳር ሲጠፋ የሻይ ቅጠል ዋጋ የሚወደደው ነገር…በግ ሲረክስ የቀይ ወጥ ዋጋ የሚጨምረው ነገር ምስጢሩ ምንድነው?
ገበያውን የሚመራው መንፈስ ግን ምንድነው የተወጋው?

Related Post