አርእስተ ዜና
Mon. May 6th, 2024

የታክስ፤ የጉምሩክ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

Jul9,2022
የታክስ፤ የጉምሩክ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል ስምምነት ተፈረመየታክስ፤ የጉምሩክ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

ከታክስ እና ከጉምሩክ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል፣ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከኢንፎርሚሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርና ከፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በጉምሩክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ቀጥሎም ስምምነቱን የተፈራረሙት የየተቋማቱ አመራሮች መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ስርዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዲዔታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ የመግባቢያ ሰነዱ በዚህ ወቅት መፈረሙ የሀገራችንን ወጪ በሀገራችን ገቢ ለመሸፈን የተያዘውን ዕቅድ እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዋና ዋና ስራዎችን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና የታገዘ ይሆኑ ዘንድ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቅሰው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የማጭበርበር ወንጀል ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ እና ሚኒስቴሩ ብቻውን የሚወጣው እንዳልሆነ በማመን ከወዲሁ ከአጋር አካላት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ከለዉጡ ወዲህ በኢኮኖሚ ሴክተሩ ላይ ተጋርጦ የነበረን አደጋ ለመቀልበስ የፍትህና የፀጥታ አካላት በጋራ በሰሩት ስራ ሊደርሱ የሚችሉ ከባባድ አደጋዎችን ማስቀረት መቻሉን በመጠቆም ወደ ፊትም የበለጠ ተቀናጅቶ በመስራት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ስምምነቱ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅት የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ውጤታማ የታክስ አስተዳደር ለአንድ አገር እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና በጀት በጅቶ ለልማት ማዋል የሚቻለው ገቢ ሲኖር መሆኑን በመግለፅ ይህን ገቢ ለማስገኘትም ግብራቸውን በታማኝነትና በሀቀኝነት የሚከፍሉና ህግ የሚያከብሩ አካላት እንዳሉ ሁሉ የግብር መከፍል ግዴታቸውን በአግባቡ የማይወጡ አካላትን ለህግ ማቅረብ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢንፎርሜሽ መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ በበኩላቸው ሀገራችን በህገ ወጥ ንግድ ከፍተኛ ገቢ ታጣለች ብለዋል። ይህን ኪሳራ ለመቀነስ አንዱ አቅም ስርአቱን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ ነው ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሂደት በተጓዳኝ የሚመጣውን የሳይበር ደህንነት ስጋት ለመቀነስ የኢንፎርሜሽ መረብ ደህንነት አስተዳደር ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

አቶ ቴዎድሮስ በቀለ የፋይናንስ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር በስምምነቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመደገፍን ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር የመረጃ ልውውጥ በማድረግ በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደምመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የፌደራል ፖሊስ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር ቀደም ሲልም የኮንትሮባንድንም ሆነ ታክስ ወንጀሎችን ለመከላከል እስከ ህይወት መስዋዕትነት እንደደረሰ ጠቅሰው አሁን ላይ የተደረገው ስምምነት ከውስጥም ከውጭም የሚስተዋሉ የስነ-ምግባር ችግሮችን ከመታገል ጀምሮ በርካታ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

Related Post