አርእስተ ዜና
Tue. May 7th, 2024

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች 271.3 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ አገኙ

Apr4,2022
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች 271.3 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ አገኙ
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች 271.3 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ አገኙ

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ዓመት ብር 263.9 ቢሊዮን ጠቅላላ የምርትና አገልግሎት ሽያጭ ገቢ ለማግኘት አቅደው ብር 271.3 ቢሊዮን ጠቅላላ ገቢ አገኙ።

ይህንን የገለጹት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ናችው፡፡ እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የምርት እና አገልግሎት ሽያጭ ገቢው የዕቅዱን 103 በመቶ ያሳካ እና ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ዕቅድ አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር በ60 በመቶ ወይም የብር 101.6 ቢሊዮን ብልጫ ያለው ነው፡፡

በአስተዳደሩ ሰባት ዘርፎች ከተሰማሩት የልማት ድርጅቶች በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ፣በፋይናንስ እና የኮሙኒኬሽን ዘርፎች የተሰማሩ እንደቅደም ተከተላቸው 56.2፣23.4 እና 10.4 በመቶ በመያዝ ከፍተኛ የሽያጭ ገቢ ያስመዘገቡ ሲሆን፣ በግብርናና አግሮ ኢንዱስትሪ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን እና በንግድና አገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ የልማት ድርጅቶች ደግሞ በጋራ 10 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡

የልማት ድርጅቶቹ ካከናወኑት ጠቅላላ ገቢ ብር 51.9 ቢሊዮን ትርፍ ከታክስ በፊት በማስገኘት ዕቅዳቸውን 142 በመቶ ማከናወን ችለዋል፡፡ የተገኘው ትርፍ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 25.5 ቢሊዮን ወይም 96.7 በመቶ ብልጫ ያሳያል፡፡ ከተገኘው ትርፍ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ፣ በኮሙኒኬሽን እና በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የልማት ድርጅቶች ክንውን 96.2 በመቶውን እንደሚሸፍን ተገልጿል፡፡

ከልማት ድርጅቶች መካከል ምርትና አገልግሎታቸውን በውጭ ምንዛሪ የሚሸጡ ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ የልማት ድርጅቶች በመንፈቅ ዓመቱ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 3.83 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በመገኘቱ ዕቅዱ በ96 በመቶ ስኬታማ ሆኗል፡፡

በአስተዳደሩ ተጠሪነት ሥር ያሉ የልማት ድርጅቶች በየዓመቱ ከሚያገኙት ትርፍ ለመንግሥት በትርፍ ድርሻ መልክ ማስገባት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ በግማሽ በጀት ዓመት ብር 4.7 ቢሊዮን ገቢ ለማድረግ ታቅዶ ብር 4.6 ቢሊዮን ወይም የዕቅዱን 96 በመቶ ተሰብስቦ ለመንግሥት ገቢ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

የልማት ድርጅቶቹ በ2014 በጀት ዓመት መጀመሪያ አጋማሽ ዓመት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ባቀዱት መሠረት የብር 2.38 ቢሊዮን ገንዘብ ወጪ በማድረግ ለማህበረሰቡና ልዩ ልዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ድጋፎችን አበርክተዋል፡፡ በአጋማሽ ዓመቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተያዘ ዕቅድ መሰረት ለ12‚260 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉና የሥራ ዕድል ካገኙትም 22 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

Related Post