አርእስተ ዜና
Fri. Apr 26th, 2024

ኦሮሚያ፡ የሞት እና አካል ጉዳት አደጋ በተቃውሞ ሰልፎች

Aug20,2020
ኦሮሚያ፡ የሞት እና አካል ጉዳት አደጋ በተቃውሞ ሰልፎች

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ለተቃውሞ በተጠሩ ሰልፎች ምክንያት የሚከሰተው የሰዎች ህይወት መጥፋት በእጅጉ እንደሚያሳስበው እየገለፀ የፀጥታ ሀይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ሀይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በተለይም በአሳሳ፣ አሰቦት፣ አወዳይ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጭሮ፣ ደንገጎ፣ ድሬ ጠያራ፣ ዶዶላ፣ ገለምሶ፣ ጊኒር፣ ሀሮማያ፣ ሂርና እና ሻሸመኔ የሞት ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ ደርሶታል፡፡

የሞት ጉዳቶቹ የደረሱት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ በተጠሩ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹የመንግስት አካላት የዜጎችን በሰላማዊ መልኩ ተቃውሞ የማሰማት መብት ማረጋገጥ እንዳለባቸው እና ሕግ የማስከበር ስራ ተመጣጣኝነት እንዲጠብቅ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው›› የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ እና ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ ገልፀዋል፡፡

‹‹የኦሮሚያ ክልል በዚህ አመት የተከሰቱ አሳዛኝ ግድያዎች ከፈጠሩት ሰቆቃ አሁንም ፈጽሞ አላገገመም፡፡ እነዚህ ከፍተኛ የመብት ጥሰት አዝማሚያዎች እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡

እስካሁን በአንዳንድ ሚዲያዎች የወጡ ሪፖርቶች እና በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ መረጃዎች የሞቱ ሰዎችን ቁጥር በሚመለከት የተለያየ አሀዝ አስቀምጠዋል፡፡ ኢሰመኮ የደረሰውን ሞትና ጉዳት መጠን ለማረጋገጥ ከየአካባቢው ነዋሪዎች፣ ምስክሮች፣ ሆስፒታሎች እና የአስተዳደር አካላት መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛል፡፡

ኢሰመኮ የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ጉዳዩን ለማጣራት በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀምሩ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Related Post