አርእስተ ዜና
Fri. Apr 26th, 2024

በመሰረተ ልማት እጦት የተፈተነው የጨው ማዕድን ክምችት በሶማሌ ክልል

Feb10,2022
በመሰረተ ልማት እጦት የተፈተነው የጨው ማዕድን ክምችት በሶማሌ ክልልበመሰረተ ልማት እጦት የተፈተነው የጨው ማዕድን ክምችት በሶማሌ ክልል

በወር ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የሚያስገኘው በሶማሌ ክልል የሚገኘው የጨው ክምችት በመሰረተ ልማት እጦት ተፈትኗል።

ከሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ ከ750 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት በሐርጌሌ ወረዳ የሚገኘው የጨው ማዕድን፤ ስሙ እምብዛም አይታወቅም።
ማዕድኑ በአካባቢው ስለመኖሩ በብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ባይታወቅም፤ በምርት አቅሙ ከፍተኛ ሀብት ያዘለ፤ 30 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚያካልልና ለሐርጌሌ እና አካባቢ ነዋሪዎች የኑሮ አማራጭ ነው።

ከጎዴ ወደ ሐርጌሌ በሚወስደው መንገድ ላይ ‘ጨው ቤት’ ከተሰኘች ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ይህ ጨው የሚመረትበት መንገድ ከሌሎች የጨው ማምረቻ አካባቢዎች የተለየ ነው።

ይሄውም ሶማሌዎች ‘ኤላ’ የሚሉት ከ10 ሜትር ያላነሰ ጉድጓድ ከተቆፈረ በኋላ በጉድጓዱ የሚያጠራቅመውን ውሃ እየቀዱ በማትነን ጨውን የማምረት ዘዴ ነው።
በዚህ ባህላዊ ዘዴ ጨው ማምረት ከተጀመረ ረጅም ዘመናት ቢያስቆጥርም የአካባቢው ነዋሪዎች ተደራጅተው ማምረት የጀመሩበት ጊዜ ግን ከ10 ዓመት በላይ አይርቅም።

የሐርጌሌ ጨው ማዕድን በወር ከግማሽ ሚሊየን ኩንታል በላይ ጨው የማምረት አቅም አለው። ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ ያነጋጋራቸው ጨው አምራቾች እንዳሉት በ2004 ዓ.ም ከ5 ሺህ በላይ አባላትን ያቀፈ ማህበር መስርተው ወደ ስራ ገብተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ በፊት ከዚህ ጨው ማዕድን ለመጠቀም ዕድል እንዳልነበራቸው ገልጸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የሐርጌሌ ነዋሪዎች የኑሮ መሰረት እንደሆነ ይገልጻሉ።

የሐርጌሌ ጨው ከእነርሱ አልፎ አገርን ለመጥቀም ከፍተኛ አቅም ቢኖረውም የመሰረተ ልማት ባለመኖሩ በሙሉ አቅም ተጠቅሞ ለማምረት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
አንድ የጨው ማዕድን ሰራተኛ ከስራ በኋላ ለመታጠብ በቀን የሚያስፈልገው 10 ሊትር ውሃ ቢሆንም በአካባቢው ውሃ ባለመኖሩ በሊትር 5 ብር ለመግዛት ይገደዳል።

የመብራት መሰረተ ልማት ባለመኖሩም ውሃውን ከጉድጓድ ጠልቆ ለማውጣት ለጀኔሬተር ወጪ ከመዳረጋቸው ባሻገር ሌሊት ሌሊት ስራቸውን እንዳያከናውኑም እንቅፋት ሆኗል።

በተመሳሳይ ወደ ማዕድኑ አካባቢ ያለው መንገድ ባለመሰራቱ የጉልበት ሰራተኞች የተመረተውን ጨው ወደ መኪና ለመጫን ተሸክመው ረጅም ርቀት ለመጓዝ እንደሚገደዱና ለተሽከርካሪም ምቹ መንገድ እንደሌለ ይገልጻሉ።

በተለይም የመንገድ፣ መብራትና ውሃ መሰረተ ልማቶች ቢዘረጉ ይህን ሰፊ ፀጋ ተጠቅሞ ለመለወጥ እና እንደ አገርም አስተማማኝ የጨው ምርት ለማቅረብ ዕድል እንዳላችው ጠቅሰዋል።

በቅርቡም ማህበሩ በጨው ምርት እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ አይዎዳይዝድ ጨው ማምረቻ ፋብሪካ ቢገነባም መብራት ባለመኖሩ በጀኔሬተር ለመስራት እንደተገደደ ገልጸዋል።

መንግስት ይህን ችግር ተገንዝቦ ጥያቄያቸውን እንዲመለስም ጠይቀዋል። የሐርጌሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አብዱራህማን እንዳሉት ወረዳው ካለው እምቅ ጸጋ መካከል የጨው ማዕድን ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

ይህ ጸጋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ቢያደርግም የመሰረተ ልማት ባለመሟላቱ ግን ሙሉ አቅሙን ለመጠቀም እንዳልተቻለ ይናገራሉ።

ወረዳው በተደጋጋሚ የመሰረተ ልማት ጥያቄ እንዲመለስለት ለበላይ መንግስታዊ መዋቅሩ ቢጠይቅም ከጎዴ ወደ ሐርጌሌ ከሚወስደው አስፓልት መንገድ ግንባታ ጅማሮ በስተቀር ምላሽ አላገኘም።

ወረዳው ከጨው ማዕድን በተጨማሪ በዕጣን እና ከርቤ ሀብቶችም የከበረ እንደሆነም ገልጸዋል። የሶማሌ ክልል ርዕስ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ መሀመድ የሱፍ በበኩላቸው አብዛኛው የክልሉ አካባቢ ላለፉት አስርት ዓመታት በመሰረተ ልማት እንዲጎዳ ይልቁኑም የግጭት ቀጣና እንዲሆን ተደርጓል ይላሉ።

በዚህም በአብዛኛው የክልሉ አካበቢዎች መንገድን ጨምሮ የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ግን ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሐርጌሌ ጨው ማዕድን እስካሁን በአግባቡ መጠቀም ያልተቻለውም በመሰረተ ልማት ችግር እንደሆነ ገልፀው፤ ከጎዴ ወደ ሐርጌሌ የሚወስደው አስፓልት መንገድ ስራ መጀመሩን አንስተዋል።

የክልሉ መንግስት ቀሪ መሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይ ሐርጌሌ ጨው ክምርን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ መላክ በሚያስችል ደረጃ አቅሙን ለማሳደግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ምንጭ – ኢዜአ

Related Post