አርእስተ ዜና
Mon. Jan 27th, 2025

መንግስት የወረሰዉን 2 ሚሊየን ጀሪካን የምግብ ዘይት ለሸማች ማህበራት ሠጠ

መንግስት የወረሰዉን 2 ሚሊየን ጀሪካን የምግብ ዘይት ለሸማች ማህበራት ሠጠ
መንግስት የወረሰዉን 2 ሚሊየን ጀሪካን የምግብ ዘይት ለሸማች ማህበራት ሠጠ

ከሰሞኑ በግለሰብ መጋዘን በሕገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘው 2 ሚሊየን ጀሪካን ፓልም የምግብ ዘይት በየክፍለ ከተማው ለሚገኙ ሸማች ማህበራት እየተሰራጨ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጀሞ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ልዩ ስሙ አንበሳ ጋራዥ ጎን በአንድ ግለሰብ መጋዘን ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 2 ሚሊየን ጀሪካን የፓልም የምግብ ዘይት በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋሉ የሚታወስ ነው።

ይህ በቁጥጥር ስር የዋለው የምግብ ዘይት በክፍለ ከተሞች በሚገኙ የሸማች ማህበራት አማካኝነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ በወሰነው መሠረት በዛሬው ዕለት የማሰራጨት ስራው ተጀምሯል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ነጻነት ዳባ በሕገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተያዘው የዚህ ዘይት መሰራጨት በከተማዋ የሚስተዋለውን እጥረት ያቃልለዋል ብለዋል።

በቀጣይም በክፍለ ከተማው መሰል የፍጆታ እቃዎችን በመጋዘን የሚያከማቹ ግለሰቦችንና ተቋማትን ለመቆጣጠር የተደራጀው ልዩ ግብረሀይል መንግስት በድጎማ የሚያስገባቸውን መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በሕገ ወጥ መንገድ በማከማቸት እና የአቅርቦት እጥረት በመፍጠር የንግድ ስርዓቱን ለማዛባት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

ህብረተሰቡ በየትኛውም አካባቢ የፍጆታ ሸቀጦችን የሚያከማቹ አካላትን እና ግለሰቦችን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥ ወ/ሮ ነጻነት ጥሪ ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬተሪ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

(ምንጭ – ንኢሚ)

Related Post