አርእስተ ዜና
Tue. Apr 23rd, 2024

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋዜጣዊ መግለጫ

Feb11,2021
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋዜጣዊ መግለጫየኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋዜጣዊ መግለጫ

ትግራይ ክልል፡ የመሰረታዊ ልማት፣ የማኅበራዊ እና የአስተዳደራዊ አገልግሎቶችን በአፋጣኝ የመመለሱ ተግባር ልዩ ትኩረት ይሻል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ከሦስት ወራት ላለፈ ጊዜ የዘለቀው እና በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች አሁንም ገና በተሟላ መልኩ ወደ መደበኛ ስራ ያልተመለሰው የመሰረት ልማት፣ የማኅበራዊ እና የአስተዳደር አገልግሎት የአካባቢውን ነዋሪዎችና እና ተፈናቃዮች ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እያጋለጠ እንደሆነ ገለጸ።

ኮሚሽኑ ከጥር 2 ቀን እስከ ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ እና በደቡባዊው የትግራይ ዞን አላማጣ፣ መሆኒ እና ኩኩፍቶ ከተሞች ክትትል እና ምርመራ በማድረግ፣ በተለይም በመቀሌ የሚገኙ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ሲቪል አመራሮችን፣ የጤና ዘርፍ ሰራተኞችን፣ ነዋሪዎችን፣ ተጎጂዎችን እና ተፈናቃዮችን አነጋግሯል።

በሪፖርቱ እንደተመለከተው ኮሚሽኑ ገና በአካል ተገኝቶ ክትትል ለማድረግ ባልቻለባቸው በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎችም ጭምር የሰው ሕይወት ማለፉን፣ የአካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት መድረሱን፣ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ዘረፋ እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው መረጃዎች ደርሰውታል። በብዙ አካባቢዎች የባንክ አገልግሎትን ጨምሮ የትራንስፖርት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች ገና ተሟልቶ አለመመለስ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶችን ዝውውር አስቸጋሪ አድርጓል፤ በተለይም የፍትሕ እና የጤና ተቋማት ወደ መደበኛ ስራቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኗል።

ከመቀሌ፣ ከአይደር፣ ከአዲግራት እንዲሁም ከውቅሮ ሆስፒታሎች በተገኘ መረጃ መሰረት ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 108 (አንድ መቶ ስምንት) የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

እንዲሁም በመቀሌ እና የኢሰመኮ ክትትል ቡድን በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ በማዳረስ ረገድ አበረታች እርምጃዎች ቢኖሩም፣ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቱ አሁንም አልተሟላም። ከሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወደ መቀሌ ከተማ የተፈናቀሉ ሰዎች የምግብ፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ እና የጤና አገልግሎት አቅርቦት እጥረት አለባቸው። በተለይም በሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ እና የጤና ተቋማት አገልግሎት መቋረጥ፣ ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች የህክምና እርዳታ ለማግኘት ረዥም የእግር መንገድ እንዲያደርጉ አስገድዷል።

ኢሰመኮ በአይደር ሆስፒታል የሕፃናት ተኝቶ መታከሚያ ከፍልን በጎበኘበት ወቅት፣ ተኝተው በመታከም ላይ ከነበሩት 20 ከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀት እና ድንጋጤ (trauma) ታካሚ ሕፃናት መካከል 16ቱ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። ከሕፃናቱ መካከል እጃቸውን፣ እግራቸውንና እና አይናቸውን ጨምሮ የአካላቸውን ክፍል ያጡ ወይም የተለያየ አይነት የአካል ጉዳት የደረሱባቸው የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይ በሕፃናት ላይ ለደረሱት ጉዳቶች አንዱ ምክንያት በመሬት ውስጥ “የተቀበሩ እና በሜዳ ላይ የተጣሉ ፈንጂዎች” የሚደርስ ጉዳት ነው።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት፣ “በትግራይ ክልል እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መጠን የሚያመላክቱ በርካታ ጥቆማዎች እና መረጃዎች ቢኖሩም፤ የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ ገና ያልተረጋገጠ በመሆኑ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ገና በተሟላ መንገድ ለማወቅ አልተቻለም። ሆኖም ኮሚሽኑ የማጣራትና የመመርመር ስራውን ይቀጥላል” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ ኢሰመኮ ጦርነቱ ያስከተለውን የሞትና የመፈናቀል አደጋ በተመለከተ ኢሰመኮ ያቀረባቸውን ጥሪዎች አስታውሰው ‹‹እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጾታዊ ጥቃትና በሕጻናት ላይ የደረሰው ጥቃትና ጉዳቱ ከዚህ የበለጠ እንዳይስፋፋ ልዩ ትኩረትና ጥረት ይሻል›› በማለት አበክረው አሳስበዋል።

(ምንጭ – ኢሰመኮ)

Related Post