አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ፖርላማው ያወጣውን አዋጅ ያውቀዋል ወይ?

ፖርላማው ያወጣውን አዋጅ ያውቀዋል ወይ
ፖርላማው ያወጣውን አዋጅ ያውቀዋል ወይ

በታምራት ሃይሉ – ዛሬ ሃሙስ ቀን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ መገናኛና ብዙሃን ባለስጣንን የዘጠኝ የቦርድ አባላትን ሹመት አፅድቋል፤የቦርድ አባላቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት የተሾሙ ስለመሆኑ ተገልፃል፤ ነገር ግን እነዚህን የባለስጣኑን የቦርድ አባላት አሻሷም በተመለከተ ይኸው ምክር ቤት ያወጣው አዋጅ ቁጥር 1238/2ዐ13 ምን ይላል? ከሚለውን ጋር ሲተያይ የተሾሙት በየትኛው የህግ አግባብ ነው ያሰኛል፤

በመጀመሪያ ደረጃ ለዓመታት ክርክር ሲደረግበት የቆየው የሚዲያ አዋጅ በቦርድ አባልነት ብቻ ሳይሆን በዳይሬክተርነት የሚሾሙ ሰዎች ከማንኛውም ተፅእኖ /የፖለቲካ፤ የሀይማኖት/ነፃ ካልሆኑ በቀር ሚዲያውን በገለልተኝነት ሊመሩ አይችሉም ሲባል የነበረ ሙግት ነበር፤ ሙግቱ በተወሰነ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ በባለስልጣኑ ማቋቋያ አዋጅ ላይ ይኸው ገብቷል፤ ዛሬ የተሾሙት ሰዎችን ማንነትን ስንመለከት ግን ፖርላማው ያወጣውን አዋጅ ያውቀዋል ወይ? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፤

በመጀመሪያ ደረጃ የባለስልጣኑ የቦርድ አባላት ከመሰየማቸው በፊት ምልመላው የሚካሄደው ‹ግልጽ በሆነ የህዝብ ጥቆማ እና በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፍ ማስታወቂያ ነው› ይላል በአዋጁ አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ፡-

፪/ የቦርዱ አባላት እጩዎችን የመመልመልና የማፅደቁ ሂደት ሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ መከናወን ያለበት ሲሆን፤ በሂደቱም፡-
ሀ) ሕዝቡ እጩ ግለሰቦችን በመጠቆምና በእጩዎች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ እድል እንዲሰጣቸው ይደረጋል፤
ለ) የዚህን አዋጅ ዓላማዎችና መርሆች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የእጩዎች አመራረጥ ሂደትና የተመረጡ እጩዎች ዝርዝር በመገናኛ ብዙሃን ወይም በሌሎች ኤሌክትሮኒክ ማሰራጫዎች ታትሞ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል፤
ሐ) የእጩዎች ምልመላ የኢትዮጵያን ብዝሃነት ያማከለ ፌደራላዊ ውክልና እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ይላል፡፡
፤ ይህ አልተደረገም፤ በመገናኛ ብዙሃንም ህዝቡ እንዲጠቁም ዕድል አልተሰጠውም፤አስተያየትም አልተሰጠም፤/አንዳንዶቹ ከቀናት በፊት በስልክ ተደውሎ እጩ ስለመሆናቸው እንደተነገራቸው ተናግረዋል፤/

በሁለተኛ ደረጃ የቦርዱ አባላት የሚመረጡበትን መስፈርት በተመለከተ በአንቀፅ 11 ላይ 7 ያህል መስፈርቶችን አስቀምጧል፤ ከእነዚህ መስፈርቶች መሀከል በ6ኛ ደረጃ ላይ፡-

፮/ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ ያልሆነ፤› ይላል፤
ነገር ግን በዛሬው ዕለት የተሾሙ ግለሰቦችን ስንመለከት ሰብሳቢው አቶ ሬድዋን ሁሴን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ከመሆናቸውም በላይ የብልጽግና ፖርቲ አባልና ከፍተኛ አመራር ናቸው፤ ባለፈው ኣመት በተካሄደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይም ብልጽግናን ወክለው ተመርጠው ምክር ቤት የገቡ ሰው ናቸው፤

ሌላው ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊም የብልፅግና አባል ስለመሆናቸው ይነገራል፤ ሌላው አባል አቶ ሀሰን አብዱል ቃድርም የብልጽግና ፖርቲ አባል ናቸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ተመራጭ የሆኑት ዶ/ር አጋረደች ጀማነህም ምንም እንኳ የብልጽግና አባል ባይሆኑም በምርጫው የ ብልፅግና እጩ ሆነው የተመረጡና ምክር ቤት የገቡ ናቸው፡፡

ለሌላው የቦርዱ አባት ስብጥርን በተመለከተ በአንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ቢያንስ ሁለት የቦርድ አባላት ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንዲሆኑ ይደነግጋል፤

፭/ ከቦርድ አባላት መካከል፡-
ሀ) ሁለቱ ከሲቪል ማኅበረሰብ፣ ሁለቱ ከመገናኛ ብዙሃን እና ሁለቱ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ጠቀሜታና አግባብነት ካላቸው የተለያዩ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች፤

ለ) ሦስቱ አግባብነት ካላቸው የመንግሥት አካላት፤ የተውጣጡ ይሆናሉ፡፡ ይላል፤
ከተሾሙት ግለሰቦች መሀከል ግን አንድም የመገናኛ ብዙሃን ሰው የለም፤ በንዑስ አንቀፅ (ለ) ላይ የተመለከተው አግባብት ካላቸው የመንግስት አካላት የሚለውም ቢሆን የፖለቲካ ፖርቲ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች እንዳይሆኑ አዋጁ በግልጽ ከልክሏል፤

ሌላው ፖርላማው ያወጣውን አዋጅ አያውቀውምወይ የሚያሰኘው ከፈረሱ ጋሪው የቀደመበትን የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዳይሬክተር ሹመት እንዳላየ እንዳልሰማ ማለፉ ነው፤ ይኸውም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የሚሾመው በአዋጁ አንቀፅ 17 ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት ቦርዱ ከተሰየመ በኋላ በቦርዱ አቅራቢነት እንጂ ከቦርዱ በፊት መሆን የለበትም፤

፲፯. የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሥልጣንና ተግባራት
፩/ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በቦርዱ ተመልምል በመንግሥት አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማል፡፡ይላል፡፡
ነገር ግን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመው ፖርላማው ሹመታቸውን ያፀደቀው አዋጁን ሳይመለክት ከ ወራት በፊት ነው፡፡ እንደ አዋጁ ከሆነ ቦርዱ ስራ ሲጀምር ሌላ ዋና ዳይሬክተር /አዲስ/ መልምሎ ሊያፀድቅ ይገባል ማለት ነው፡፡ ለመሆኑ ፖርላማው ያወጣውን አዋጅ አገላብጦ የስራ ሀላፊ የሚሾመው መቼ ነው?

Related Post