አርእስተ ዜና
Wed. Nov 13th, 2024

ይድረስ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ

ይድረስ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ
ይድረስ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ

በጅብሪል ላሞ – ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ለሚጀምረው የማስተርስ ፈተናዬ ለሳምንታት በትጋት ሳጠና ቆየሁ፡፡ በእለቱ ወደ ፈተናው አዳራሽ በሰዓቱ ለመድረስ ከታክሲ ይልቅ ባቡር እንደሚፈጥን በማመኔ ሰባተኛ ወደሚገኘው የባቡር ጣቢያ አመራሁ፡፡ በስፍራው በርካታ ሕዝብ ባቡር እየጠበቀ ደረስኩ፡፡ ይህም የፊተኛው ባቡር ካለፈ በርካታ ደቂቃ እንዳለፈው ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ባቡሩ በሁለት ደቂቃ ውስጥ እንደሚደርስ በመገመቴ በፍጥነት ትኬት ገዝቼ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቀልኩ፡፡

ሰዓቱ ለሰባት ሃያ ጉዳይ ነበር፡፡ ፈተናዬ ግሎባል ሆቴል አቅራቢያ በመሆኑ ባቡሩ ከሁለት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይደርሳል፣ ለፈተናዬም በአስተማማኝ ያደርሰኛል የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡ ይሁንና ሰዓቱ እየነጎደ ሄደ፡፡ ከባቡር ጣቢያው ወጥቼ በታክሲ ልሂድ ብል እንኳን ጊዜውን በባቡር ጥበቃ ያቃጠልኩት በመሆኑ የመድረስ ተስፋ አልነበረኝም፡፡ በመሆኑም ልቤ በፍርሃት መራድ ጀመረ፡፡

ከብዙ እልህ አስጨራሽ ቆይታ በኋላ 7፡20 አካባቢ ከአውቶቡስ ተራ የሚመጣ ባቡር ተመለከትኩ፡፡ ፈተናው ከተጀመረ 20 ደቂቃ እንዳለፈው ሳስብ ፍርሃት ተሰማኝ፡፡ ይሁንና ከባቡሩ የሚፈጥን ትራንስፖርት ባለመኖሩ ዘልዬ ገባሁ፡፡ እንደዚያ እለት ባቡር ሲንቀራፈፍ አይቼ አላውቅም፡፡ ልቤ በጭንቀት ሊፈነዳ ደረሰ፡፡
ግሎባል አካባቢ እንደደረስኩ ኮቴ እንደ ባንዲራ እየተውለበለበ በሩጫ ወደ ትምህርት ቤቴ አመራሁ፡፡

አራተኛው ፎቅ ላይ የሚገኘው የፈተናው ክፍል ስደርስ 7፡38 ሆኖ ነበር! ፈታኙ በንዝህላልነቴ በመደነቅ ፣ኮምጨጭ ባለ ፊት ዓይኖቼን እያየ ፈተናው ከተጀመረ ግማሽ ሰዓት ስላለፈ መግባት አትችልም! ሲል ቁርጤን አረዳኝ፡፡

ከ475 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የወጣበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራስፖርት መስከረም 9 ቀን 2008 ሥራ ሲጀምር የከተማይቱን የትራንስፖርት ችግር እንደሚቀርፍ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ በየስድስት ደቂቃ ልዩነት ተሳፋሪዎችን ከየፌርማታው በማንሳት በሰዓት እስከ 15 ሺህ ተሳፋሪዎችን ከቦታ ቦታ ያጓጉዛል ፣ተብሎ ነበር፡፡

ከሰባት ዓመታት አገልግሎት በኋላ የድርጅቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ሊሻሻል ፣ ሽፋኑ ሊጨምር እና በየስድስት ደቂቃው ይደርሳል ተብሎ የነበረው ባቡርም በሂደት በየሁለት ወይም ሦስት ደቂቃ ሊደርስ በተገባው ነበር፡፡

ይሁንና ድርጅቱ ገና የሙሽርነት ዘመኑ ሳያበቃ እርጅና ተጭኖታል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱ እያሽቆለቆለ ዋጋው ብቻ ጨምሯል፡፡ የባቡር አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደመሆኔ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያስተዋልኳቸውን አንዳንድ ችግሮች እንደሚከተለው አነሳለሁ፡፡

የአገልግሎት ሰዓት መቀነስ፡- የባቡር አገልግሎቱ ከሰባት ዓመት በፊት ሥራ ሲጀምር ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ የባቡር አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ የባቡር አገልግሎቱን ወደ 24 ሰዓት በማሳደግ የከተማይቱን እንቅስቃሴ ይበልጥ ያሳልጣል፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ከተሟላም የንግድ እንቅስቃሴ ይጨምራል የሚል እምነት ነበር፡፡ ይሁንና ቀስ በቀስ የአገልግሎት ሰዓቱ በ120 ደቂቃ እንዲቀንስ ተደረገ፡፡

ይህ ማለት ደግሞ አብዛኞቹ የምሽት ትምህርት ቤቶች የሚዘጉት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በመሆኑ ፣ እንዲሁም በርካታ የመሃል ከተማ መደብሮችና መዝናኛ ካፌዎች የሚዘጉት ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በመሆኑ ተጠቃሚዎች ወደ አካባቢያቸው ለመሄድ የባቡር አገልግሎት እንዳያገኙ አግዷቸዋል፡፡
ተደጋጋሚ የባቡር ብልሽት፡- በበርካታ አገራት – አዳዲስ ባቡሮች በአማካኝ ለ28 ዓመታት ያለ ብልሽት ያገለግላሉ ተብሎ ይነገራል፡፡

ይሁንና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት በተደጋጋሚ ተሳፋሪዎችን እንደያዘ በብልሽት ሳቢያ በየፌርማታው ይቆማል፡፡ በዚያ የተነሳ ተሳፋሪዎች ብዙ ፌርማታ እየቀራቸው የከፈሉበት ትኬት ዋጋ ሳይመለስ ለመውረድ ይገደዳሉ፡፡ የተበላሸውን ባቡር ድርጅቱ ፈጥኖ ስለማያነሳው በብልሽት ሳቢያ ቢያንስ አንድ ቀን የባቡር አገልግሎት ይቋረጣል፡፡

ፀሐፊው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ በባቡር ብልሽት ሳቢያ ለትራንስፖርት የማይመች አጉል ቦታ ለመውረድ ተገዶ ያውቃል፡፡
የባቡር ትኬት መሸጫ ሱቆች መዘጋት፡- የባቡር አገልግሎትን ለማግኘት ደንበኛው ትኬት መግዛቱ ግድ ነው፡፡ ይሁንና ባቡሩ በሥራ ላይ እንዳለ ሠራተኞቹ የቲኬት መሸጫዎቹን በጊዜ ዘጋግተው – ወደቤት ወይም ወደጉዳያቸው የሚሄዱበት ጊዜ አለ፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ቢያንስ ሁለት ቀን ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ባቡሩ እየሠራ ሚኒሊክ አደባባይ የሚገኘው የባቡር ትኬት መሸጫ በጊዜ በመዘጋቱ በጥበቃ ላይ የነበሩት መልካም ፖሊሶቹ ተሳፋሪዎች ያለ ክፍያ እንዲገቡ ሲፈቅዱ ተመልክቻለሁ፡፡

አላስፈላጊ የአገልግሎት ማቋረጥ፡- የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፎች ሲኖሩ ምናልባት በዚያ ሰዓት የባቡር አገልግሎት ማቋረጡ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ማለዳ የሚካሄዱ ሰልፎች ወይም የኃይማኖት ስርዓቶችን አስታኮ የሚቋረጠው የባቡር አገልግሎት እስከሚቀጥለው ቀን ማለዳ ሲቀጥል ይስተዋላል፡፡ በእኔ አስተሳሰብ የባቡር መስመሩ ከዋናው መንገድ የተለየ በመሆኑ ምንም አይነት ሰልፍ ወይም የኃይማኖት በዓል ቢኖር የባቡር አገልግሎት ሊቋረጥ አይገባውም፡፡ ምክንያቱም ሰልፈኛውም የባቡር አገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናልና፡፡

ባቡሮችን ቀጣጥሎ ያለመጠቀም፡- ተሳፋሪ በሚበዛባቸው ሰዓታት ከተጠቃሚው ብዛት የተነሳ ባቡር ቶሎ ቶሎ ቢመጣ እንኳን በአንድ ፌርማታ ሕዝብ ነው የሚሞላው፡፡ በተለይም ተሳፋሪ በሚበዛባቸው እንደ አውቶቡስ ተራ እና ስታዲዮም ያሉ የባቡር ጣቢያዎች የሚገባው ተሳፋሪ በራሱ አንድ ባቡር የሚሞላ ነው፡፡ በመሆኑም ቢያንስ ተሳፋሪ በሚበዛባቸው የሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት ባቡሮችን ቀጣጥሎ በአንድ ጊዜ በርካታ ተሳፋሪዎችን ማንሳት እንዲችሉ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይሁንና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አልፎ አልፎ ብቻ የሚስተዋለውን ባቡሮችን ቀጣጥሎ አገልግሎት የመስጠት ሥራ በስፋት አጠናክሮ ሊሄድበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡

የባቡሮች ተመሳሳይ ቀለም መቀባት፡- በመላው ዓለም የሚገኙ የከተማ ቀላል ባቡሮች በማያሳስት ሁኔታ የጉዞ አቅጣጫቸው በተቀቡት ቀለም ይለያል፡፡ በመሆኑም ተሳፋሪ በስህተት ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚሄድ ባቡር ውስጥ መግባት የተለመደ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ሲጀመር የባቡሮቹ ቀለም በማያሳስት ደረጃ ከርቀት የሚለይ ነበር፡፡ አረንጓዴና ሰማያዊ !

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ባቡሮቹ በላያቸው ላይ ማስታወቂያ ተለጥፎባቸው አንዳቸውን ከአንዳቸው ለመለየት አዳጋች ሆኗል፡፡ ለአብነትም ከሚኒሊክ አደባባይ ወደ ቃሊቲ የሚሄደው ሰማያዊ ባቡር ላይ ከጦር ኃይሎች እስከ አያት ከሚሄደው ባቡር ቀለም ጋር በሚመሳሰል የሳፋሪኮም ማስታወቂያ በመሸፈኑ በቀለሙ የባቡሩን አቅጣጫ ለመለየት አዳጋች ሆኗል፡፡ በተለይም ከልደታ መገንጠያ እስከ እስታዲዮም በሚገኙት ጣቢያዎች የሚሳፈሩ ሰዎች የሚሳፈሩበትን ባቡር በጥንቃቄ ሊመርጡ ይገባል፡፡

የንጽሕና ችግር፡- የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የሚጠቀምባቸው ዋሻዎች በንጽህና ሊያዙ ፣ በቂ ጥበቃም ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ይሁንና ሰዎች በማይጠቀምባቸው ሰዓታት ምናልባት በሌሊት ወደ ዋሻዎቹ የሚገቡ ሰዎች አልፎ አልፎ የሚፀዳዱባቸው በመሆኑ ደስ የማይል ጠረን አላቸው፡፡

ባቡሮቹም ቢሆን ንጽሕና እንደሚጎድላቸው እንደሆኑ ማየት ይችላል፡፡ በሀገሪቱ ውሃ የሌለ ይመስል ባቡሮቹ በጣም ቆሽሸው ነው የሚታዩት፡፡ በመሆኑም ለሕዝብ ጤና ሲባል ድርጅቱ የንጽህናውን ጉዳይ ሊያስብበት ይገባል፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች አግጠው የሚታዩ እንጂ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ሌሎችም በርካታ ጥቃቅን ችግሮች አሉ፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አስተዳደር ችግሮቹን በተለይም የአስተዳደር ቸልተኝነትን ለመፍታት የበኩሉን ለመፍታት እንደሚጥር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

Related Post