አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

የኢንተርኔት ሞክሼዎቼ

የኢንተርኔት ሞክሼዎቼ
የኢንተርኔት ሞክሼዎቼ

በመኩሪያ መካሻ – በዓለም ላይ 145 መኩሪያ መካሻዎች አሉ። ይህን ያወቅኩት በአንድ ዝናባማ የሐምሌ ወር ጉግልን ስጐለጉል ነው። እነዚህ ሰዎች እንደ ጨው ዘር በመላው ዓለም ተበትነው ይኖራሉ። ከሞስኮ እስከ ገልፍ ኦፍ ሜክሲኮ፣ ከኖርዌይ እስከ ፖርት ኤልዛቤት። በጣም የሚገርመው በቻይናዋ ቹን ከተማም አንድ ሞክሽዬ መኖሩ ነው። በአጠቃላይ ከ20 አገራት በላይ መኩሪያ መካሻዎች ይኖራሉ። ሌላም አስደማሚ ነገር አለ። አብዛኛዎቹ ሞክሼዎቼ በሴቶች ስም በተሰየመ ጐዳና አካባቢ መኖራቸውም ያስገርማል፡፡ በአሌክሳንድራ ፣በላውራ፣ በሾሴ ፣በአንድሬቭና ጐዳናዎች አፓርታማ ተከራይተው ይኖራሉ፡፡

ሞክሼዎቼ በባህርያቸው በጣም ይለያያሉ። አንዳንዶቹ ገና ወጠምሻ ጐረምሶች በመሆናቸው በየፓርቲው መደነስ ይወዳሉ፡፡ የሴት ሽንጥና ገላ ታቅፈው ጨዋታ ነፍሳቸው የሆነና በየመንደራቸውም የታወቁ ግብ ጠባቂዎች ሞልተዋል፡፡

ከሁሉም ግን የገረመኝ አንዳቸውም አጥቂ ሳይሆኑ የኳስ በር ጠባቂዎች መሆናቸው ነው። እንደተረዳሁት ከሆነ ብዙዎቹ አልኮልና ሐሺሽ ይደፍራሉ። ከ145ቱ ውስጥ ሁለቱ ብቻ ናቸው የሥነ መለኮት ትምህርታቸውን ተከታትለው ሰባኪ የሆኑት። አንደኛው ሰባኪ በቅርቡ ሴት ልጅ እንደምትኖረው እየተጠባበቀ ይገኛል። ሌላኛው ሰባኪ ግን ለመውለድ አልታደለም ሚስቱ ሾተላይ ዞረባትና ጨነገፈች።

አንዳንድ ቆፍጣና ሞክሼዎቼ ከእናት ሀገራቸው አልፈው በሶማሊያ አል-ሸባብን እየተዋጉ ነው።
«እስቲ ስለ ራሳችሁ ንገሩኝ» ብዬ ለሞክሼዎቼ አንዲት ማስታወሻ በኢ-ሜይል ሰደድኩ።
«ስማችሁን ማን አወጣላችሁ? ምን እየሠራችሁ ትኖራላችሁ? ምንድንነው ሆቢያችሁ? የሥራ ኃላፊነታችሁስ? የት ተወለዳችሁ? የትምህርታችሁስ ሁኔታ እንዴት ነው? የሚስቶቻችሁ ስምስ ማን ይባላል?» ነበር ጥያቄዬ።

ሰባኪውና በሥነ መለኮት የዶክትሬት ዲግሪውን የተቀዳጀው ሞክሼዬ ምን አለኝ መሰላችሁ፡-
«የምኖረው አሜሪካ አኒስተን ሲቲ በምትባል ከተማ ነው። አንዳንዴ ብስክሌቴን እየነዳሁ ወደ ቢራ መጥመቂያ ቤቶች ጐራ እላለሁ። ልጆች የሉኝም። እንደ ዕድል ሆኖ ባለቤቴ በሾተላይ ምክንያት መውለድ አልሆነላትም፡፡ ቤተሰቦቼ አሁንም ሱሉልታ ከተማ ውስጥ ወተት እያለቡ ኑሮአቸውን ይገፋሉ። እኔ ግን ሰባኪ ነኝ። እኔና ባለቤቴ ኢየሱስ ጌታ ነው እያልን ሕይወታችንን እየመራን ነው። እሱ የሕይወታችን አልፋና ኦሜጋ ሆኖ ይኖራል» አለኝ።

ሌላኛው ሞክሼዬ በቦስተን ከተማ ይኖራል። ብረት አቅላጭ ነው። «ይኸው ለ23 ዓመታት ብረት እየቀጠቀጥኩ ብረት እያቀለጥኩ እኖራለሁ፡፡ ሁሌም የብረቱን ነበልባልና እቶን እየተመለከትኩ ስለ ሕይወት ነበልባላዊ ስሜት አለኝ።»

ሞክሼዎቼ በየክፍለ ዓለማቱ ስለተዘሩ ይኸኛው ደግሞ የሚኖረው ሊድስ ከተማ ነው፣ ሀገረ- እንግሊዝ። ገና የሊድስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን፣ ይህን ስሙን እንዴት እንዳገኘ አያውቀውም። በአሳዳጊ ነው እንግሊዝ ሀገር የገባው። ታዲያ ስለ ስሜ ጠንቅቄ እንዳውቅ አድርገኸኛል ሲል በጥያቄዬ ተገርሞ መለሰልኝ።

መኩሪያ መካሻ የቪተርቦው (ጣሊያን) ደግሞ- «ዕድሜዬ 18 ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለማጠናቀቅ ተቃርቤያለሁ፡፡ ገና የ18 ዓመት ወጣት መሆኔ ያስደስተኛል። ትምህርት ቤታችን ውስጥ 200 ተማሪዎች ብቻ ናቸው ያሉት። ቪተርቦ ከሮማ ከተማ ራቅ ያለች ትንሽ ከተማ ናት። የከተማው ሰዎች እንተዋወቃለን። እኔን በመልኬ ብቻ ሳይሆን በስሜም ያውቁኛል። አንዳንዶቹ ስሜን አሳስተው ሜሪኩሪ ይሉኛል። ግድ የለኝም። ስቄ አልፋቸዋለሁ። አንድ የሊሞናራ ፋብሪካ ውስጥ በትርፍ ጊዜዬ ስለምሠራ የመዝናኛ ሳንቲም አላጣም። ብዙም ባይሆን ሕይወቴን አጣጥምበታለሁ። ገና 18 ዓመቴ ነው ብዬሃለሁ ስለዚህ አላገባሁም።

ግን ታዲያ በአንድ ክፍል አብረን ከምንማር ሊያና ፍቅር ይዞኛል። ሆቢዬ እግር ኳስ መጫወት ነው። እንዲያው በደፈናው የጐል በር ጠባቂ ነኝ።»
ኖርዌይ የሚኖር ሞክሼም አገኘሁ።

«እንደዚህ ብዙ ስመ ሞክሼዎች መኖራችንን አላወቅሁም ነበር። 49 ዓመቴ ነው። በ1990 ዓ.ም ኤርትራ ገዛ-ገረስላሴ ስዋጋ ግራ እግሬን ቆስያለሁ። ከዚያም እዚህ ኖርዌይ በስደት ከመጣሁ በኋላ ከሞተር ብስክሌት ወድቄ ግራ -ጐኔን (ሟይቴ አካባቢ) ተጐድቼያለሁ። ኖርዌይ- ትሮንዲሄም ከተማ የባቡር ጣቢያ የጥበቃ ምክትል ኃላፊ ሆኜ ለ10 ዓመታት ሠራሁ። የማስተዳድረው ቤተሰብ ስለሌለብኝና የሚያለቅስ ልጅም ስለማላሳድግ የገንዘብ ችግር የለብኝም። ክረምት ሲሆን ሰፊ ዕረፍት ወስጄ ወደ ኢትዮጵያ ላንጋኖ ሄጄ አርፋለሁ። መላ ሕይወቴ ግን ዛሬ ከትሮንድሄም ከተማ ጋር ተጣብቋል። ባለቤቴ ሸርሊያ በተፈጥሮ ዓይነ-ሥውር ስትሆን መልከ ቀና ናት። ከነፍሷ ትወደኛለች። ማታ ማታ ወጣ ብለን «አይሪሽ ባር» ከሚባለው ቡና ቤት ቢራ እንጐነጫለን። እኔም በዚያው የአውሮፓን የእግር ኳስ ጨዋታ እከታተላለሁ። ዕድሜዬን የሊቨርፑል ደጋፊ እንደሆንኩ ፀጉሬ ተመለጠ። በተረፈ ፈጣሪ ይክበር ይመስገን ደህና ነኝ። ስለ አንተ ባውቅ ደስ ይለኛል።»

እኔም ይህ ማስታወሻው እንደደረሰኝ ወደ ኖርዌይ መልዕክት ላክሁ። ስለ ላክልኝ ደብዳቤ አመሰግንሃለሁ አልኩት። ስለ እሱ አሰብሁ። በጦር ሜዳ ስላሳለፈው መራራ ህይወትና ከዓይነ ሥውር ሚስቱ ጋር እንዴት በመኖር ላይ እንደሚገኝ በዕዝነ-ልቡናዬ ቃኘሁ። አሁን የእንቅልፌ ሰዓት ደርሷል። ማሸለቤ ነው። የነገውን አንድዬ ያውቃል…
የሞስኮው ሞክሼዬ ደሞ አጠር ያለች ማስታወሻ ላከ። «አራት ሴት ልጆች አሉኝ። ናታሻ፣ ካትሪና፣ መነንና ለጋ-ወርቅ። ወንዶች? የምን ወንዶች?…። መኩሪያ የወንድ ስም አይደል። እሱ ይበቃል።»

የሞስኮው መኩሪያ ስለ ስማችን ታሪካዊነት አንድ ነገር አከለበት። «የመመካት፣ የኩራት፣ የአንበሳነት ተምሳሌት የሆነ ስም ነው፤ ስለዚህ በስማችን መኩራት አለብን» አለኝ። «በታሪካችን ብዙ አርበኞች ስማቸው መኩሪያ እንደሆነ ታውቃለህ? የቤተመንግሥቱ የአፄ ኃይለስላሴ አንበሳ እንኳ ስሙ መኩሪያ ነበር» ሲል ታሪክ አስታወሰ። አክሎም « በኡክሬይን ኪቭ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሞክሼዎችን አውቃለሁ» አለኝ። «አንዱ የራሱ የግል የቼኮላት ባር አለው። ሌላኛው ደግሞ የአንድ ፋብሪካ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ ይሠራል፣ ግን አንዳቸውንም አግኝቼ አላውቅም። አዝናለሁ።»

የካናዳው ደግሞ በይቅርታ ደብዳቤውን ጀመረ። «በፍጥነት ኢ-ሜይል ስላላደረኩልህ በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ። በመሠረቱ ሥራዬ እሥረኞች ከእሥር እንዲፈቱ ይቅርታ ማስጠየቅና የይቅርታ ፎርም ማስሞላት ነው። እዚያ አዲስ አበባ ይህ ሙያ የሚታወቅ አይመስለኝም። በትርፍ ጊዜዬ በቶሮንቶ የሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኜ ተመርጬልሃለሁ። ባለቤቴ እዚህ ካናዳ የተወለዱ ህፃናትን መዝሙር ታስተምራለች። ስሜ ሳፊ የአማራ ስም እንደሆነ አውቃለሁ። አያቶቼ ሲያወሩ እንደሰማሁት ሩብ፣ ሩብ ከትግሬው፣ ከኦሮሞው፣ ከወላይታው እንዳለኝ ነግረውኛል።

ለመሆኑ ስምን መልአክ-ያወጣዋል የሚባለው አባባል እውነት ይሆን?
የፍራንክፈርቱ መኩሪያ መካሻ ቢራ ይወዳል። ቀዝቃዛ ቢራ ያላበው ቢራ ከተፈለፈለ ኦቾሎኒ ጋር። እንዲህ ሲል ፃፈልኝ « ባለፈው ሳምንት በፖስታ ቤት የላክልኝ ደብዳቤ ደርሶኛል። እንደነገርከኝ ከሆነ አዲስ አበባ ኢንተርኔት ይቆራረጣል፣መብራት ይቆራረጣል፣ውሃ ይቆራረጣል፣ደመወዝ ይቆራረጣል- ምንድነው የማይቆራረጠው?» ሲል ጠየቀኝ ።ደ’ሞ መልሶ ለዚህ መልስ አልፈልግም ይገባኛል። ተወው» አለኝ።«አፃፃፍህ ግን ንፁህ ነው። የፌደል አጣጣልህ የቄስ ተማሪ እንደነበርክ ያሳብቃል። የእኔም የመጀመሪያ መምህሬ አባተ ገላው ይባሉ ነበር። የጐጃም ሰው ናቸው። መቼም ወንዝ ወርጄ የተሸከምኩላቸው እንሥራና ጭራሮ ይታወሰኛል። ታዲያ ምሥጋና ይግባቸውና የእኔም የእጅ ጽሑፍ በጣም ያምራል። እዚህ ፍራንክፈርት ከተማ ከሁሉም ምግብ የምወደው ሶሴጃቸውን ነው። አንዲት ሴት ልጅ አለችኝ። መካሸች ብያታለሁ። የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ ነው። በል ሌላ ጊዜ ጨምርልኝ» ብሎ ተሰናበተኝ።

ዛሬ ለየት ያለ ዕለት ነው ደንግጬያለሁ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ነው ያስደነገጠኝ። አንድ የሀዘን ማስታወቂያ በድንገት አነበብኩ እንዲህ ይላል« የሶማሊያው ጀግና መኩሪያ መካሻ በ38 ዓመቱ ከዚህ ዓለም ተለየ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ ለ15 ዓመታት አገልግሏል። ሁለት ሜዳሊያዎች ተሸልሟል። አንድ የምሥጋና ወረቀት ከመከላከያ ሚኒስትሩ በቀጥታ የተላከለት ምስጉን ወታደር ነበር። ነፍሱን በገነት ያኑረው» ይላል።

አዘንኩ። በምን ምክንያት በሞት እንደተለየ የተጠቀሰ ነገር የለም። ማስታወቂያው እንዴት እንደኖረ ማንን እንዳፈቀረ አይናገርም። ሌላው ቀርቶ ስለዓይኑ ቀለም እንኳ ምን እንደሚመስል አይገልፅም። ሩጫውን ከመጨረሱ በፊት ጉጉቱ፣ ራዕዩ ምን እንደሆነ አይናገርም። ምን ያስብ ነበር? የደስታው ወይም የሀዘኑ ሕብረ-ቀለም ምን እንደሚመስል አናውቅም። አሳሳቁስ እንዴት ነበር? ይህም የለም። ስለ ስሙ የነበረው ኩራት፣ ጉጉት ምን እንደሆነ አናውቅም። እንዴት እንደተማረ ሌላው ቀርቶ ስሙን መጀመሪያ ሲጽፍ እንዴት ባለ የካሊግራፊ አጣጣል እንዳስቀመጠ የምናውቀው ነገር የለም። ትምህርት ቤት ሲቀመጥ እንኳ ከፊት ለፊት ነበር የሚቀመጠው። ቅፅል ስሙ «አንበሴ» እንደነበር ለምን አልተገለፀም? ፊርማ ሲፈርም እንዴት በስሙ እየተደሰተ አጠማዞ እንደሚፈርም እንኳ አላወቅንም።
* * * *
ዛሬ ያልጠበቅኩት ኢ-ሜይል ደረሰኝ። ከቻይና ቹን ሲቲ ነው። ሞክሸዬ ፃፈልኝ። መቼም የእኛ ሞክሼ ቻይና ይኖራል ብዬ አልጠበቅኩም። ለካስ ያልተዘራንበት ክፍለ ዓለም የለም። እንዲህ አለኝ። «የቻይና ኑሮ መጀመሪያ ላይ ከነ ቋንቋው አስቸግሮኝ ነበር። አሁን ይኸው ሰባት ዓመቴን ደፈንኩ። ቻይናዊ ሚስትም አገባሁ። መቼም የቻይና ሴት የተለየች ትመስልህ ይሆናል። ሴት ያው ሴት ናት። ቻይናም ይሁን ካናዳ፣ ሩሲያም ይሁን ደቡብ አፍሪካ ሴቶች አንድ ዓይነት ናቸው። እንደ አፍሪካ ዶሮና ኑሮ ይመሳሰላሉ። እኔ ተመችቶኝ ከሊን ቻይ ጋር እኖራለሁ።

ለመሆኑ ኑሮ እዚያ እንዴት ነው? ሰሞኑን እዚህ ሊሸቅል የመጣ የመርካቶ ልጅ እንደነገረኝ ከሆነ ኑሮውን የምትወጡት አይመስለኝም። የኑሮ መርግ ተጭኖአችኋል። በርበሬ ጣራ ነክቷል። ምስር ኪሎ 60 ብር ገብቷል ሲለኝ ጭንቅላቴን ይዤ ጮህኩ። እዚህ ቻይና ቢልዮን ህዝብ በርካሽ ጠግቦ ያድራል። እኔ እንኳ በዕሮብ-አርብ የውሻ ሾርባና የእንቁራሪት መረቅ እያጣጣምኩ መመገብ ከጀመርኩ ወዲህ ፈርጠምጠም ብያለሁ። መቼም የካህን ዘር ብሆንም ኑሮ ነውና ተለውጫለሁ። መቼም በሆድህ የአቦ ጠበልም ርኩሰትህን አያስለቅቅህም ትለኝ ይሆናል።

አትሳሳት! እናንተ ግን የአመጋገብ ባህላችሁን መለወጥ አለባችሁ። ጤፍ ኩንታል 2000፣ ምስር 60 ብር፣ በርበሬ ኪሎ 200 ብር እየገዛሁ እኖራለሁ ማለት አይቻልም። ጊዜው የግሎባላይዜሽን ነው። የእናንተን መንግሥት እንደሆን ብልጥ ነው። ዶላር ይፈልጋል። ገበሬው ዶላር ከቀመሰ ጉዳችሁ መፍላቱ ነው። እወቁበት።!»

ሞክሼዎቼ ብዙ ቢሆኑም የሁሉንም ደብዳቤና ሀሳብ አላካፈልኳችሁም። እንዲያው ጥቂቶቹን ነው እንድታውቋቸው ያደረግሁት። በአካባቢያችሁ አስቂኝ መኩሪያዎች፣ ነጋዴ መኩሪያዎች፣ እንጨት ፈላጮች፣ ኳስ ተጫዋቾች፣ የጥርስ ሃኪሞች… ወዘተ ብዙ ሞክሼዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እስቲ ስለ እነዚህ ሞክሼዎች ንገሩን። በተራችሁ እናተም የኢንተርኔት ሞክሼዎቻችሁን ፈልጉ።

Related Post