አርእስተ ዜና
Tue. Nov 26th, 2024

የቁርአን ቤት (የአሽር ቤት) ትዝታዎች – ፎርፌና ክርስቲያን ጓደኞች

የቁርአን ቤት (የአሽር ቤት) ትዝታዎች - ፎርፌና ክርስቲያን ጓደኞች
የቁርአን ቤት (የአሽር ቤት) ትዝታዎች - ፎርፌና ክርስቲያን ጓደኞች

በሃውለት አህመድ

በቁርዓን መቅራት ሕይወት ውስጥ ክርስቲያን ጓደኞቻችን የራሳቸው ቦታ አላቸው። እኛም በጓደኞቻችን የቄስ ትምህርት ሕይወት ተሳትፎ እንዳለን ሁሉ።

አሽር ቤት (ቁርዓን ቤት) የሚዘጋው አርብ አርብ (ጁሙዓ) ቀን ብቻ ነው። በተረፈ ስድስቱንም ቀን ሙሉ ቀን እንቀራለን። ጠዋት ከ 2 – 6 ከሰዓት ከ7 – 11። ያኔ ትምህርት በፈረቃ ስለነበር የጠዋት ተማሪ ከሰዓት ቁርዓን ቤት ይገኛል። የከሰዓቱም ጠዋት። በትምህርት አመካኝቶ ማርፈድም ሆነ መፎረፍ ለአለንጋ ሲሳይነት ይዳርጋል።

እና በአንድ ወቅት ሐሙስ ከሰዓት ክርስቲያን ጓደኞቻችን ወደ ቁርዓን ቤት እየሸኙን ሳለ (በግምት 10 እንሆናለን። አንድ ሰባቱ ወንዶች) ‘ለምን አንፎርፍም?’ የሚል ሃሳብ መጣልን። ‘መፎረፍ’ በርግጥ ያኔ የሚታወቅ ቃል አይደለም። (ለጽሁፌ እንዲመቸኝ ነው። ) ጓደኞቻችን እጅግ ተደሰቱ። በቃ ነገ ጁሙዓ ነው። ቅዳሜ ጠዋት ስንገባ አሽር ጌታ ስለሚረሱት ግርፊያ የለም። በቃ ወደ ጨዋታ… የተሰረቀ ጊዜ እንዴት ይጣፍጣል? ተራገጥን አይገልጸውም። ‘አፈርፋሮ’ እስክንመስል ተጫውተን ከቁርዓን ቤት የመውጫ ሰዓት ጠብቀን ዘና ብለን ወደ ቤት ስንደርስ በድንጋጤ አፋችንን ከፍተን ቀረን። አሽር ጌታችን ያቺን የሸረፈዲ ጎማ እያወዛወዙ ቆመዋል። ወላሒ እግራችን ከመሬት አልነቀል ብሎ አስቸገረ። አያቴም ከአሽር ጌታ እኩል እሳት ጎርሳለች። (በአያት ዕጅ ነው ያደግኩት )

‘ኸውለት’ ብለው አሽር ጌታ ሲጮሁ ተፈናጥሬ አጠገባቸው የደረስኩበት ፍጥነት በውነቱ እስካሁን አልተገለጠልኝም። ምክንያት መጠየቅ ሳያስፈልግ አንድ ባንድ ተለጠለጥን። ግርፊያ ለኛ አዲስ ባይሆንም የአካባቢው ሰው ተሰብስቦ ‘ይበሏቸው፣ የታባታቸው፣ ቁራን ሄደናል ብለው ሲንዘላዘሉ ተገኝተው እኮ ነው፣ ጨምሩላቸው አዎ…’ እያሉ ሲያባብሱና የኛ friend ያልሆኑና ሌላ ቁርዓን ቤት የሚቀሩ ልጆት ተሰባስበው ሲስቁብን … በዕውነት ለኛ ትልቅ ውርደት ነው። ክብራችን ተነክቷል።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እስከዛሬም ሳስበው ዓይኔ እንዲረጥብ የሚያደርግ ነገር ተከሰተ። ‘እነ ሐውለት እየተገረፉ ነው’ መባልን ሰምተው ያኔ በፎርፌው የተሳተፉም ያልተሳተፉም ክርስቲያን ፍሬንዶች አጎንብሰው ጸጉራቸውን እያሻሹ መጡ።

‘እኛንም ግረፉን’ አሉ። አንድም ቤተሰብ አልተቃወመም። እንዲያውም አንደኛዋ እናት የሷም ልጅ ቄስ ት/ት ቤት ፎርፎ ከእኛ ጋር ሲራገጥ በመዋሉ ቆማ ደህና አድርጋ አስገረፈች። እስኪበቃን ተገርፈን ወደየቤታችን። ሆኖም ሁለት ፍሬንዶች ፈርተው ለመገረፍ ስላልመጡ በማግሥቱ አፍረው ከኛ ጋር ሳይጫወቱ ቀሩ። ቀኑን ሙሉ ሌላ ሰፈር ከሴቶች ጋር ‘ሱዚ’ ሲጫወቱ መዋላቸው በራሱ በቂ ቅጣት ስለነበር ይሄው እንደ ‘ቅጣት ማቅለያ’ ተይዞላቸው አመሻሽ ላይ እንዲቀላቀሉን ፈቀድንላቸው።

ለውህ/ሉህ የማስመለስ ዘመቻ ከክርስቲያን ጓደኞች ጋር
ለውህ/ሉህ ከጣውላ ለስልሶ የተዘጋጀ ትንሽ ሰሌዳ ነው። በሉሁ እየተከተበ ከዚያም ከሃከምን (ለአሽር ጌታ ካሰማን) በኋላ ይታጠባል። ለሚቀጥለው ክትብ ዝግጁ ይሆናል። ወደቤታችን ስንሄድም ለሉሁ የተዘጋጀለት ቦታ አስቀምጠን እንሄዳለን። በተለይ በደ/ብርሃን ከተማ በቀላሉ አዘጋጅቶ የሚሠጠን ስለሌለ ሉሃችንን እንደ ዓይን ብሌናችን ነው የምናያት።

እናም በአንድ ወቅት የመጀመሪያው አሽር ጌታችን አገር ሲቀይሩ ሌላ አስቀሪ እስኪመጣልን ድረስ ቢያንስ 1 ወር አካባቢ ቦዝነን ነበር። የኛ መቦዘን ሳያንስ የሌላ ቁርአን ቤት ልጆች አሳቻ ቀንና ሰዓት ጠብቀው መስጊድ የሚገኘውን የኛ ቁርአን ቤት ገብተው ደህና ደህናዎቹን ሉሆች መርጠው ወሰዱብን። የእነዚህ ልጆች አሽር ጌታ በመኖሪያ ቤታቸው ስለሚያቀሩና የሉህ ማስቀመጫ ቦታ ስለሌላቸው ልጆቹ ወደየቤታቸው ይዘውት ይሄዳሉ። ልጆቹ ሉሃችንን መዝረፋቸው ሳያንስ ልክ እኛን ሲያዩ በኩራት ተወጣጥረው ለመንሳፈፍ ሲከጅሉ ማየት ምን ያህል አሳማሚ እንደነበር መገመት ይቻላል። እንዲች እንዳሳረሩንማ አይቀሩም!

አልሃምዱሊላህ አሽር ጌታ ተገኘልን። ለጊዜው በአንድ ሉህ ለሶስት እየቀራን ለማሳለፍ ተገደድን። ስለዘረፋው ለአሽር ጌታችን ብንናገርም ገና አዲስ በመሆናቸው መተነኳኮስ አልፈለጉም። ስለዚህ ሉሃችንን በጉልበት ለማስመለስ ወሰንን። የተለያዩ ልጆች ተሰባስበን ለመንጠቅ ብንሞክርም እነዚያም ‘ነቄ’ በመሆናቸው አልተሳካም። ስለዚህ የአሽር ቤታችን ልጆች ተስፋ ቆረጡና ተውት።

ለጥቂት ጊዜ አስቤ ክርስቲያን ጓደኞቼን ሰበሰብኩ። አብዛኛው ከኔ ጋር ሲራገጡ የሚውሉ ስለሆኑ እኔ ላሰብኩት ‘ንብረት የማስመለስ ህጋዊ ዘመቻ’ ፍቃደኞች ነበሩ። ነገር ግን ቁጥራችን አስተማማኝ ‘ወረራ’ ለማካሄድ በቂ ስላልነበር የ’ኮስታራ’ ጓደኞች እገዛ አስፈለገ። ኮስታሮቹ ስላቅማሙ ቀጣዮቹ ማስፈራሪያ ተሰጣቸው።

– አንድ ሶስቱ ልጆች ብቸኛ ሂሳብ አስጠኚያቸው እኔና እህቴ ስለነበርን ካልተባበሩ ‘ሂሳብ’ ብለው ቢመጡ ቅልጥማቸውን ሰብረን እንደምናባርር ተናገርን። እንዲያውም የአንደኛው እናት ‘ልጄን አላስጠናችልኝም’ ብላ አያቴ ፊት ቆንጥጣኝ ስለነበር ‘ከፈለግህ ለእናትህም ንገራቸው። ማንንም አልፈራም’ ብዬ ደነፋሁ።

– አንድ ሁለት ሴት ፍሬንዶች ሰንበት ት/ቤት መዝሙር አጥንተው ሲመጡ ዜማውን የምይዝላቸው እኔ ስለነበርኩና ሲረሱ ስለማስታውሳቸው ‘ከዚህ በኋላ ለገደል ማሚቱ ንገሩ። አጠገቤ ድርሽ እንዳትሉ’ ብዬ ተቆጣሁ።

ዓመት በዓል ሲደርስ አበባ የምስልላቸው ልጆች፣ ቤታችን በር ላይ ካለው ስልክ እንጨት ላይ ‘ቴዘር’ ለመጫወት የሚመጡ ልጆች ወዘተ ላይ ማዕቀብ ጣልኩ። ማዕቀቡ ህልውናቸውን የሚፈታተን ሆኖ ስላገኙት ተስማሙና ለዘመቻው ተዘጋጁ። የቁርአን ቤቱ ልጆች ሉሃቸውን ታቅፈው ከአሽር ቤቱ ራቅ ሲሉልን የተሳካ ወረራ አከናውነን በርካታ ሉሆችን ከዕጃችን አስገባን። ከዚያም ሰብስበን ከአንድ የጉሎ ዛፍ ከሚገኝበት ሥፍራ የጉሎ ቅጠል ሸፍነን ደበቅናቸው። (የጉሎ ቅጠል ሰፊ ነው)
በማግሥቱ ምን እንደሚደርስብኝ አውቄያለሁ።

የነዚያንኞቹ አሽር ጌታና የተወሰኑ ‘ተዘረፍን’ ባይ ደፋሮች ቁርዓን ቤታችን መጡ። ‘ኸውለት’ የአሽር ጌታችን ድምጽ ቤቷን አናጋት። ሁሉም ስለ ሉህ ዘመቻው አውቋል። ‘የልጆቹን ሉህ ቀምታችኋል?’ ቀምተናል ሆነ አልቀማንም ቅጣቱ ያው ነው። ‘አልቀማንም።’ ሽምጥጥ። ምሥክር ቢጠራም ብቸኛዋ ከ 1 ለ 3 ሉህ ‘ነፃ አውጪያቸው’ እኔ ስለነበርኩ ‘ዓይኔን ግንባር ያድርገው’ ብለው ካዱ። ምንም ማድረግ አልተቻለም። እናም ሳናስፎግር ሉሆቹን ቀስ እያልን ወደ አሽር ቤታችን አስርገን አስገባን። በክርስቲያን ጓደኞቼ ትብብር በየራሳችን ሉህ የመቅራት ነፃነታችንንም አገኘን።

በራሳ/ቦረቅ
እነዚያ በእርግዝናቸው ወቅት ‘አፈር አማረኝ’ የሚሉ ሴቶች ግን አሁንም አሉ? የአፈር አምሮት ያሰቃያቸው የነበሩ ነፍሰ-ጡሮች አንዳንዱ እንደቀበጥ ሲያያቸው እንዴት እንደማዝንላቸው። ስለማውቀው ነዋ! ከእኛ ከአሽር ቤት ልጆች ምግብነት ተርፎ ለሌላ አገልግሎት የሚውል አፈር መገኘቱም በኛ ቸርነት ነው። በትክክል አንብባችኋል። አፈርን በፍቅር የምንበላ ልጆች ነበርን።

ስንጀምር በራሳ/ቦረቅን እናገኛለን። አማርኛ ይሁን/አረብኛ ወይ አርጎብኛ ቃሉ ምን እንደሆነ አላውቅም። በራሳ ከምን ዓይነት አፈር፣ ቀለምና ውሁድ እንደሚሠራ አናውቅም። ምንነቱን ለመግለጽ ያህል አሁን ካሉት የገላ ሳሙናዎች ቅርጹ ተመሳሳይ ሆኖ ትንሽ ከፍ የሚል፣ ከለሩ ውሃ አረንጓዴ የሆነ እና የአፈርነት ሽታው ደስ የሚል ጠጣር የሆነና የሬክታንግል ቅርጽ ያለው ነው። አገልግሎቱም የቁርአን መቅሪያ ሉህ ከታጠበ በኋላ በማሸት ሉሁን ወደ አረንጓዴ ሰሌዳነት መቀየር ነው። በአረንጓዴ ሰሌዳ ሲከተብ ጽሁፉ ስለሚያምር ከከሰል ዓመድ ይልቅ በራሳ ምርጫችን ነው። ያኔ የነበረው ዋጋ 0.50 ሳንቲም ሲሆን ለአንድ ለሚቀራ ልጅ ከ6 ወር በላይ ያገለግላል።

እንኳን 6 ወር 20 ቀንም መሻገሩን እንጃ። በልተን ነዋ የምንጨርሰው። በራሳው የተሰራበት አፈር ወይ ድንጋይ ወይ ሌላ የተጨመረው ነገር ስለሚጥምና እኛም አጣጥመን ወደጉሮሮአችን ስለምንልከው ሁሌ 0.50 ሳንቲም መክሰር የሚፈልግ ቤተሰብ አይገኝም። አንዳንዴ ሉሁን ለመቀባት ቾክ ልንጠቀም እንችላለን። ወደባሰ ‘የበራሳ ድህነት’ ከዘለቅንም የከሰል ዓመድ ሌላው አማራጫችን ነው።

በሚያሳዝን ሁኔታ በራሳ ያመጡ የነበሩት ሰውዬ መሸጥ ስላቆሙ የአፈር አምሮት ማስታገሻ ያስፈልግ ነበር። (ግነት የለውም።) ስለዚህ የአሽር ቤቱን ግድግዳ አፈር መቅመስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ጥቂቶች አፈሩን ስንቀምስ ለክፉ እንደማይሰጥ ስላረጋግጥን አዘውትረን ግድግዳውን እየፈነቀልን መብላት ጀመርን። አሽር ጌታ አፈሩን ስንበላ አይተውን አያውቁም። ተደብቀን ነው የምንፈነቅለው። በተለይ በጓሮ በኩል ያለው ግድግዳ አጽሙ እየወጣ ሲመጣ አሽር ጌታ ጠጋ ብለው መመርመር ጀመሩ። ጋሽ መሐመድ ኑር ይባሉ የነበሩ የመስጊዳችን ምክትል ዒማም ጋር ሰፊ ምክር ያዙበት። በኋላ ላይ አንዳች ብል እየበላው ሊሆን ይችላል ብለው ደምድመው ትንሽ ይብላውና እናስመርገዋለን ተባባሉ። ይሄ ለኛ ትልቅ እፎይታ ነበር።

ሆኖም ከበራሳ ወደ አመድ መውረድ ለኛ ‘ክብረ-ነክ’ በመሆኑ ሌላ መላ ፈለግን። ችግር ብልሃትን እንደሚወልድ አፈር በምንበላበት ዘመን ነው የተማርነው። ስለዚህ የራሳችንን በራሳ/ቦረቅ ለመስራት ኖራ ድንጋይ ፈጭተንና ጢባጢቤ የምንጫወትበትን ቅጠል አቀላቅለን ጭፍጭፍ አድርገን እንጠፈጥፈውና ጸሃይ ላይ እናሰጣዋለን። ለዚህም የሚያገለግለን ጎድጓዳ ድንጋይ አዘጋጅተናል። በራሳን ባይተካም ከአመድ በጣም ስለሚሻል በሥራችን በመኩራት በአረንጓዴ ሰሌዳ ልንቀራ ችለናል። (የፈጠራ ክህሎታችንን ማነው የሰረቀብን?)

አንድ ቀን በብዛት ‘ግድግዳ በልተን’ ቤት ስንገባ አያቴ አንድ ከአዲስ አበባ ከመጣች ጓደኛዋ ጋር እያወራች ነበር። ልክ የኔን ጥርስ ስታይ ‘ኧረ ለአላህ ብለሽ አንቺ ልጅ ይህን አፈር ተይ’ ስትል ሴትዮዋ ግራ ተጋብታ ‘በአፈር መጫወቷ ምንድነው ሽግሩ?’ ስትል አያቴ ቀበል አድርጋ ‘ሽግሩማ ጨዋታው አይደለም። ቀለቧ መሆኑ ነው፤ አፈር ስትበላ ነው የምትውለው’ ስትላት ‘አበስኩ ገበርኩ’ ብላ የጮኸችው እስካሁን ጆሮዬ ላይ ያቃጭላል። እና ምን ለማለት ነው ኮረት ድንጋይ ሲቀር ያልበላነው ነገር የለም።

Related Post