አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

የሻይ ሳይሆን የቡና ዕረፍት ነዉ መባል ያለበት

የሻይ ሳይሆን የቡና ዕረፍት ነዉ መባል ያለበት
የሻይ ሳይሆን የቡና ዕረፍት ነዉ መባል ያለበት

በስንታየሁ ግርማ – በአለምአቀፍ ደረጃ ቡና ከ50 ሀገሮች በላይ የሚመረት ሲሆን ከ120 ሚሊዮን በላይ የአለም ህዝብም ኑሮው ተመሰረተው በቡና ላይ መሆኑን መረጃወች ያሳያሉ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ተወዳጅ የሆነዉ አረቢካ ቡና መገኛና ቡናን ለዓለም ያበረከተች ሀገር መሆኗን ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከ5 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ቡናን የሚያመርቱ ሲሆን በአጠቃላይ ከ25 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኑሮው በቡና ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ቡና 5 ከመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ብሄራዊ ምርት የሚሸፍንና ከ 25-30 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ነው፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር አቦል፣ ቶና በረካ በሚል በየቀኑ በመላው ኢትዮጵያ በመጠጣት ዜጎች ሀሳባቸውን በመለዋወጥ የኢትዮጵያን ማህበራዊ ካፒታል/ Social Capital/ ከመገንባቱም በላይ ሀገራችንን ለአለም በማስተዋወቅ ረገድ የኢትዮጵያ ብራንድ እየሆነ ይገኛል፡፡ ሰለዚህ የሻይ ሳይሖን የቡና እረፍት መባል አለበት ፡፡

የዕረፍት ሰዓታችን የሻይ ከሚባል የቡና ቢባል የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቶቹም፡-
1. ለአለም ዲሞክራሲ እውቀት ፍልስፍና መስፋፋት ካደረገው አስተዋፅኦ አንፃር
እ.ኤ.አ. በ1964 በአሜሪካ የላብአደሩ ተደራዳሪዎች “እርስዎ የቡና እረፍት ይስጡና የሚሠጡትን ሁሉ ያግኙ” በሚል መሪቃል ከባለሀብቱ ጋር እልህ አስጨራሽ ድርድር በማድረግ “የቡና ዕረፍት” ተግባራዊ ሆኖ የላብአደሩን አካላዊ እና አዕምሮአዊ ብቃት በቡና ዕረፍት ምክንያት በመጨመሩ የባለሀብቱ ምርትና ምርታማነት ማደግ ጀመረ፡፡

ቡና በተለይም የእውቀት የምክንያት እና የፍልስፍና ዘመን ለሚባለው የ18ተኛ ክ/ዘመን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በ18ተኛ ክ/ዘመን የነበሩት እውቅ ፊላስፋዎች እንደ ቨልተር ሩሶ ወዘተ በቡና ካፌ ውስጥ በመሠብሠብ የሃሳብ ፍጭት ያደረጉ ነበር፡፡ አዳዲስ ሃሳቦችንም ያፈልቁ ነበር፡፡ ፈላስፋዎቹም ቡናን ፉት ማለት ያዘወትሩ ነበር፡፡ ይህ “የእውቀት የፍልስፍና፣ የብርሃን” ዘመን ተብሎ የሚጠራው የ18ተኛው ክፍለዘመን የሥልጣን ምንጭ መሆን ያለበት ምክንያታዊነት ነው የሚል አቋም ተቀባይነት ያገኘበት ዘመን ነበር፡፡ ስለዚህ ቡና ለዲሞክራሲ ማደግ እና መስፋፋት ላደረገው አስተዋፅኦ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡

ቡና በዓለም ዲሞክራሲ ለመበልፀግ ያደረገው አስተዋጽኦ መነሣት ያለበት ነው፡፡ ጀርገን ሀቨርማስ የተባለው የጀርመን ሶሽዮሎጂስት እና የፖለቲካል ሣይንስ ምሁር የ18ኛው ክፍለ ዘመን የዲሞክራሲ ወርቃማው ዘመን ነበር ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ Public Sphere በሚለው ፅንሰ ሀሣቡ በወቅቱ ሠዎች በቡና ካፌዎች እና በመሣሠሉት ቦታዎች በመሰባሰብ ስለህይወታቸው፣ ስለየጋራ ጉዳያቸው ስለተለያዩ ሀሳቦች ያለምንም ገደብ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ በምክንያት ይከራከራሉ፡፡

መግባባት የተደረሰበት ስምምነትን በተግባር ያውሉታል፡፡ ሠዎች በቡና ካፌዎች ተሠብስበው ሲወያዩ የገንዘብ፣ የትምህርት፣ የመደብ እና የመሣሠሉት ልዩነቶች ግምት ውስጥ አይገቡም ነበር ይላል ሀቨርማስ፡፡ እሱ እንደሚለው መንግስታትም ተቀባይነት ለማግኘት ዜጐች በቡና ካፍቴሪያዎች ተሰባስበው የተወያዩበትን እና ስምምነት የደረሱበትን ሀሳብ ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጉት ነበር ይላል፡፡ በኋላ ግን ሚዲይ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጥናት በሚል ሰበብ ወካይ ያልሆነ የጥናት ውጤት በማቅረብ ለህዝብ መወገን ትተው ለባለሀብት በመወገን Public Sphareን በግለኝነት ተኩት ይላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ቡና ሀሣብ ለማፍለቅ በምክንያታዊነት በመከራከር እና በማመን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህም እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡

2. ቡና የኢትዮጵያ ልዩ መለያ(ብራንድ) መሆን ስላለበት፡፡
የብራንድ ባለሙያዎች ሀገራት 1 ብቻ ምርት( አገልግሎት) ልዩ መለያቸው/ብራንድ/ ቢሆን ከኢንቨስትመንት እና ከቱሪዝም ተጠቃሚ ይሆናሉ ይላል፡፡ በዚህ ውድድር በበዛበት እና የሸማች ዘመን በሚባልበት ወቅት ሸማቹን ለመያዝ አንፃራዊ ብልጫ ባለምርት ላይ ማተኮር አዋጭ ነው፡፡ የሀገራትም ተሞክሮ የሚያሣየው ይኸው ነው፡፡ አሜሪካ ሲባል “የዲሞክራሲ ቁንጮ” መሆኗ፣ እንግሊዝ ሲባል “ኘሪሚየር ሊግ” ፈረንሳይ ሲባል “ወይኗ” ግሪክ ሲባል “ፈላስፋዎቹ” ግብፅ ሲባል “ፒራሚዶቿ” ይታወሳሉ፡፡

ከዚህ በመነሣት ኢትዮጵያ ሲባል ልዩ መለያዋ ቡና መሆን አለበት ከቡና የተሻለ ምርት ወይም አገልግሎት የለም፡፡ በአለም ላይ በየቀኑ ከ4 ቢሊዮን ስኒ ቡና በላይ በየቀኑ ይጠጣል፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠረው የቻይና ህዝብ እንኳን 1ዐ በመቶ የቡና ሱሰኛ ቢሆን የምናገኘውን የገበያ እድል እናስበው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በሀገራችን ያሉ ቻይናውያን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተገኘው አጋጣሚ ስለቡና ማውራት እና ከተቻለም ግብዣ በማድረግ ማለማመድ ይቻላል፡፡ ስለዚህ የዕረፍት ሰዓታችን የሻይ እረፍት ከማለት ይልቅ የቡና ዕረፍት ማለት ያዋጣናል ማለት ነው፡፡

3. ሀገራችን ያላት የዲኘሎማሲ ቦታ
አዲስ አበባ በአለም ላይ በዲኘሎማቲክ መቀመጫነት 3ኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ መረጃዎች ያሣያሉ፡፡ ብዛት ያላቸው አለምአቀፍ ሁነቶች ታስተናግዳለች፡፡ ታዲያ በእነዚህ ሁነቶች ጊዜ መርሃግብሩ “Tea Break” ከሚል ይልቅ “Coffee Break” ብንል ቡናን በነፃ ለማስተዋወቅ ይረዳል፡፡ በየቡና ዕረፍቱ ደግሞ በባህላዊ የቡና አፈላል ስርዓት በመጠቀም እና ቡናውን እንዲጠጡት በማድረግ ቡናን ማስተዋወቅ ይቻላል፡፡

4. ለአኮኖሚ ባለው ፋይዳ
ቡና ለሀገራችን 25-30 ሚሊዮን ህዝብ የህይወት መሠረት ነው፡፡ ከአጠቃላይ ብሔራዊ ምርት 5 በመቶ ይሸፍናል፡፡ ከኤክስፖርት ገቢ 25-30 በመቶ በመሸፈን የአንበሣውን ድርሻ ይይዛል ስለዚህ እውቅና ሊሠጠው ይገባል፡፡ በአለም ገበያ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ከቡና የተሻለ ምርት የለንም፡፡ የእኛ ቡና ጣዕም አለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ነው፡፡

5. ቡናና የአየር ንብረት ለውጥ
ጥናቶች እንደሚያሣዩት ቡና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አደጋ ውስጥ ካሉት ምርቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ቡና ከአለም እንዳይጠፋ እና የ120 ሚሊዮን ቡና ላይ የተመሠረተው የአለም ህዝብ ህይወት አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ኢትዮጵያ ውስጥ በቡና ላይ ኢንቨስት ማድረግ መፍትሄ እንደሆነ ተመራማሪዎች እያሣሠቡ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ፖሊሲ እና አተገባበር ከቀጠለ የቡናን ምርት በ4 እጥፎች በኢትዮጵያ ማሣደግ እንደሚቻል ተመራማሪዎቹ እማኝነታቸውን ሠጥተዋል፡፡

ስለዚህ ይህንን የአለም አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ ማለትም የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢነት ለአለም ማህበረሰብ የበለጠ ለማሣወቅ “የቡና ዕረፍት” በማለት ስለጉዳዩ የበለጠ ግንዛቤ በማስያዝ ለመፍትሄዎቹ የአለም ማህበረሰብ የራሱን ሚና እንዲጫወት ማድረግ ይቻላል፡፡ በአጠቃላ የቡና እረፍት መባሉ ለቡና ልማት ትኩረት ለመስጠት ራሱ አስተዋጽኦ ያደርጋል፤፤

Related Post