አርእስተ ዜና
Mon. Jan 27th, 2025

“ወንድ ይሙት?…”

ወንድ ይሙት...
ወንድ ይሙት...

በመላኩ ብርሃኑ –  የአመሻሽ ምኞት ድሮ ልጅ እያለን ማርች 8 ሲመጣ ሰሞን ይህ ዘፈን እየተደጋገመ ያደምቀው ነበር (የኔ ዕድሜ ባቾች ብቻ ታስታውሱታላችሁ)

፠ ሴት በሴትነቷ ትከበር
ሴት በሴትነቷ ትከበር
ሴት በሴትነቷ…ትከበር…ትከበር
አይቻልምና ያለ እርሷ ለመኖር
ከወንዶችም ቆራጦች አሉ ( አሉ። )
ከሴቶችም ቆራጦች አሉ (አሉ ።)
ታዲያ ከወንዶቹ (እንጃ )በምን ያንሣሉ (እንጃ)
ይህንን ካልን ዘንዳ (ታግሶ ለሚያነብ አንባቢ ብቻ ) ባለፉት ዓመታት እዚሁ ፌስቡክ ላይ ማርች 8ን በመተገን ሴቶቻችንን ያወደስንበትን ጽሁፍ ደግመን እናስነብባለን።
++++++++++++
እንግዲህ ግድ ከሆነ
ቤት እንዳይፈርስ….ቤተሰብ እንዳይበተን
ወንድ ይሙት!!
———————————-
(In memory of March 8 )
እንደኔ ታዝባችሁ ቤት ያለሴት አይሞቅም።በተለይ እናት የሌለችበት ቤት ደግሞ በቁሙ እያለ የፈረሰ ቤት ነው።
ወንድ ልጅ ትንሽም ሆነ ትልቅ የሴት ጥገኛ ነው። የኑሮ መላ ያለው በሴት እጅ ነው። ብዙ ጊዜ ወንድና ኑሮ የሚተዋወቁት በስም ብቻ ነው። በትዳር ውስጥ ወንድ ምልክት ነው። የህይወት ዘዋሪ ግን ሴት ናት።

የወንድ ልጅ ዕድሜ ጠዋቱ ላይ በእናቱ እጅ ነው። ወደአመሻሹ ሲደርስ ደግሞ የመኖሩ ብቸኛ ጣዕም ሚስቱ ብቻ ናት። ባህሪውን ተረድታ፣ፍላጎቱን አሟልታ ህይወቱን እንዲያጣጥም የምታደርገው ሚስቱ ብቻ ናት። ወንድ ልጅ በልጅነቱ እናቱ ብቻ እንደምታውቀው በዘመን ማምሻውም ሚስቱ ብቻ ናት ማንም ከሚረዳው በላይ የም’ትረዳው።

አይታችሁ እንደሁ እናት ስትሞት ብዙ ቤት ይፈርሳል።ቤተሰብ አንድ የሆነ ቢመስለውም በመንፈስ ይበተናል። የቤቱ ግርማ ፣ ምሰሶው ይናጋል። ምን ግንብ ቢያጥረው፣ ምን ቤተመንግሰት ቢያህል እናት የሌለችበት ቤት ቀትሩ ቀላል ነው።

አንዳንዴ ለቅሶ ስትሄዱ ታዝባችሁ እንደሁ ሚስቱ የሞተችበት ወንድ ቁጭ ብሎ ሲያለቅስ አይታችኋል? ..ያሳዝነኛል። ባል ሚስቱን እሷን እንዳጣበት ቀን ያህል በህይወቱ ቀን አይጎድልበትም ።

ልጆች ራሳቸውን ችለው ከቤት የወጡ ቀን ቤቱ ከነሙሉ ግርማው የሚኖረው እናት እስካለች ድረስ ነው። ልጆችም በየበዓሉ፣ በአዘቦቱ ደስ ብሏቸው የሚሰባሰቡት የቤቱ ዋርካ እናት ስትኖር ብቻ ነው። እናት የሌለችበት ቤት ለባል ቀርቶ ለልጆችም ሰቀቀን ነውና ላለመሳቀቅ የልጆችም እግር ወደዚያ ቤት ለመሄድ ያጥራል። ገና ለወግ ያልበቁ ልጆች ባሉበት ቤት ደግሞ የቤቱ አውራ ስትለይ ህይወት መያዣ መጨበጫ ታጣለች።

አባት ይህንን ልዩ የህይወት ስጦታ አልታደለም። የተበታተነውን የልጆች መንፈስ እና አንድነት አስተካክሎ እንደነበረ ለማቆየት ፍጹም ሃይል የለውም።አባት ብቻውን የሆነ ቀን እንኳን ልጆቹን ሊሰበስብ ራሱ ሰብሳቢ ፈላጊ ነው።

ልጆች በፍቅር የሚዋደዱት፣በደስታና ችግር የሚተሳሰቡት፣በሃሳብ አንድ የሚሆኑት በአብዛኛው እናታቸው ስትኖር ነው።ሲጣሉ እንደአመላቸው ተቆጥታ፣መክራና አስተምራ አንዳንዴም ጡቷን ይዛ ለምና አስታርቃና በእርግማኗም ቢሆን አስፈራርታ ልጆቿን በፍቅር አንድ አድርጋ ታኖራለች። ወንድ ልጅ ከቁጣና ጩ.ት በቀር ይህንን ጥበብ በፍጹም አልተካነውም። ፍጹም !።

የወንድ ልጅ ህይወት ከሴት ውጪ ኦና ቤት እንደማለት ነው።ለዚህም ነው “አዳም ብቻውን አይሆን ዘንድ…” ተብላ ሴት የተፈጠረችለት። ብዙ ጊዜ ታዝባችሁ ከሆነ ሚስቱን ያጣ ወንድ ዘውዱን እንደተነጠቀ ንጉስ ቀልብ ርቆት ፣ ሃሳብ አጉብጦት፣ሃዘን ፊቱን አጠይሞት ደስታ ቢስ ሆኖ ታዩታላችሁ።እድሜው ገፋ ሲል ደግሞ ኮትኳቹ እንደረሳው ተክል እያያችሁት ሲጠወልግ ትታዘባላችሁ። ቀስ ብሎም ወይም ደግሞ ፈጥኖ የዕድሜ ጸሃዩ ትጠልቃለች።

ለዚህም ነው ወንድ ልጅ የሚያሳዝነኝ።ጥገኛ ፍጡር ነው። የህይወቱ ደስታ የተቋጠረበት አቁማዳ ያለው በሚስቱ እጅ ነው። እሷ ሳትኖር ፈገግታው እንኳን የግድ ነው። በምድር ላይ ሚስቱን አጥቶ ቀን የመሽበት ፣ ዘመን ጨለማ የሆንበት በራፍ ላይ ቁጭ ብሎ ወጪ ወራጁን እንደሚያይ ግርማ የራቀው አባት የሚያሳዝነኝ ነገር የለም።

ለዚህም ነው “ግድ ከሆነስ …ቤት እንዳይፈርስ…ቤተሰብ እንዳይበተን ወንድ ይሙት እንጂ ሴትስ ሁሌም ትኑር” ያልኩት። (ቢቻልማ ሁላችንም ..ሁሌም በኖርን )

ሴቶቻችን ሆይ ይህች ጽሁፍ የማርች 8 መታሰቢያችሁ ትሁን! …እንኳን አደረሳችሁ። ማርች 8 በወሬ ሳይሆን በተግባር የምትከብሩበት ይሁን። ደግሞም እኛ እንኖር ዘንድ እናንተ ቀድማችሁ ኑሩልን!!

Related Post