አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ወርቃማዉ የቡና ዓመት

ወርቃማዉ የቡና ዓመት
ወርቃማዉ የቡና ዓመት

በስንታየሁ ግርማ – ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተችው እንቁ ስጦታዎች መካከል ቡና ዋነኛው እና የመጀመሪያው ነው፡፡ ቡና ዛሬ በዓለም ላይ በየቀኑ ከ3 ቢሊዮን በላይ ስኒ ይጠጣል፡፡ በ50 በላይ ሀገሮች ይመረታል፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ የዓለም ህዝብ ኑሮው በቡና ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ጥናቶች እንደሚያሣዩት የቡና የጤና ጠቀሜታዎች ብዙ ናቸው፡፡ ለመጥቀስ ያህል
• “የስኳር በሽታን በ50% ይቀንሣል፣
• የአልዛይመር በሽታ ስጋትን ይቀንሣል፣
• በቆዳ እና በጡት ካንሰር የመያዝ እድሎችን ይቀንሣል፣
• ብጉርን በመከላከል የቆዳ ጤንነትን ይጨምራል፣
• የሰው ልጅ ፀጉር እድገትን ይጨምራል፣
• የፋይበር አወሳሰዶችን ይጨምራል፣
• ሲርሆሲስ የተባለ ጉበት በሽታን ይከላከላል፣
• ድብርትን/የመደበት ስሜትን ይቀንሣል፣
• የሰውነት መጉረብረብ ወይም መመረዝን /ኢንፍላሜሽንን/ ይቀንሣል፣
• በፓርኪንሰንስ በሽታ የመያዝ እድላችንን ይቀንሳል
• የእድሜ ጣሪያንይጨምራል ”(/ኢትዮ ጤናን)
በማህበራዊ ፋይዳ በኩል ቡና በሀዘንም በደስታም ወቅት የሚቀርብ ነው፡፡ ለእኛ ቡና የኩራት ምንጫችን ነው፡፡ ከ3ዐ ሚሊዮን በላይ ዜጐች ህይወታቸው የተመሠረተው በቡና ላይ ነው፡፡

ከኢኮኖሚያዊ እና ከማህበራዊ ፋይዳው የበለጠ ቡና ለአለምም ባለ ዉለታ ነዉ፡፡ በዓለም ዲሞክራሲ ለመበልፀግ ያደረገው አስተዋጽኦ መነሣት ያለበት ነው፡፡ ጀርገን ሀቨርማስ የተባለው የጀርመን ሶሽዮሎጂስት እና የፖለቲካል ሣይንስ ምሁር የ18ኛው ክፍለ ዘመን የዲሞክራሲ ወርቃማው ዘመን ነበር ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ Public Sphere በሚለው ፅንሰ ሀሣቡ በወቅቱ ሠዎች በቡና ካፌዎች በመሰባሰብ ስለህይወታቸው፣ ስለየጋራ ጉዳያቸው ስለተለያዩ ሀሳቦች ያለምንም ገደብ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ በምክንያት ይከራከራሉ፡፡

መግባባት የተደረሰበት ስምምነትን በተግባር ያውሉታል፡፡ ሠዎች በቡና ካፌዎች ተሠብስበው ሲወያዩ የገንዘብ፣ የትምህርት፣ የመደብ እና የመሣሠሉት ልዩነቶች ግምት ውስጥ አይገቡም ነበር ይላል ሀቨርማስ፡፡ እሱ እንደሚለው መንግስታትም ተቀባይነት ለማግኘት ዜጐች በቡና ካፍቴሪያዎች ተሰባስበው የተወያዩበትን እና ስምምነት የደረሱበትን ሀሳብ ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጉት ነበር ይላል፡፡

በሂደት ግን የመገናኛ ብዙሃን እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች እና ተቋማት Public Sphere በግለሰቦች ሉዐላዊነት/private sphere) ተተካ ይላል፡፡ እንደሀቨርማስ አረዳድ የህዝብ ወሳኝነት የበላይነት በነበረበት ዘመን ቡና እና የቡና ካፌዎች አስተዋፅኦ አድርገዋል ማለት ነው፡፡
ለመንደርደሪያ ያህል ይህንን ካልኩ ወደ ዋናው ጉዳይ ልግባ፡፡ በ2014በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ብዙ ስኬቶችን እና ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች፡፡

የባለፈው በጀት ዓመት በተለይም የቡና ዓመት ተብሎ ሊገለፅ የሚችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በመጠንም በገቢም ሪከርድ የሆነ ኤክስፖርት የተመዘገበበት ነው፡፡ 300000 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ ከ1.4 ቢሊይን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ከ2013 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 14 በመቶ በገቢ 22% በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ለዚህ አስተዋፅኦ ካደረጉት መካከል ኢትዮጵያ በቡና ዘርፍ ያካሄደችው የሪፎርም ስራ ዋናው ተጠቃሽ ነው፡፡

መንግስት በግሎባላይዜሽን /ሉላዊነት/ መተዳደር የህልውና ጉዳይ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ግሎባላይዜሽን የአማራጭ ጉዳይ ሣይሆን የስርዓት ጉዳይ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ከመወዳደር ውጭ ሌላ አማራጭ የለም ብሎ በማመን በዓለም ገበያ ተወዳድሮ ማሸነፍ የሀገሪቱን ህልውና ማስቀጠል ነው ብሎ በጥብቅ በማመን በገበያው ንቁ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ በመሆን ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ባለፉት ጥቂት አመታት ትኩረት ከተሰጣቸው የኤክስፖርት ምርቶች መካከል ቡና ይገኝበታል፡፡
– በተለያዩ የክልል ከተሞች ባለድርሻ አካላትን በማሣተፍ ማነቆዎችን በመለየት መፍትሄዎችን በጋራ አስቀምጠዋል፡፡ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የባለቤትነት ስሜት በማዳበር በህገ-ወጥ የቡና ንግድ ዝውውርና ቁጥጥር ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

– የቡና ምርታማነትና ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ ታትሟል፡፡ እስከ ወረዳ ድረስ ባለፉት አመታት ሥልጠናም ተሰጥቷል፡፡ ምንም እንኳን ቡናን ለአለም ገበያና ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብናመርትም አሁንም የምርታማነታችን ደረጃ ዝቅተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያሣያሉ፡፡ ለመጥቀስ ያህል ቡናን ከዛሬ 290 ዓመት በፊት ማብቀል የጀመረችው የዓለም የመጀመሪያዋ አምራች እና ሁለተኛዋ ቡና ጠጪ ሀገር ብራዚል ስትሆን በሄክታር የቡና ምርታማነት መጠኗ 1.4 ቶን ነው፡፡

የቬትናም 2.1 ቶን፣ የኮሎምቢያ 0.9 ሲሆን የቡና መገናኛ እና የልዩ ጣዕም ቡናዎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት በቶን 0.3 ብቻ ነው፡፡ ይህንን ዝቅተኛ የምርታማነት መጠን በማሻሻል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እና የቡናን ህልውና ለማስቀጠል የቡና ምርታማነትና ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ እስከ ወረዳ ድረስ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በቀጣይ አርሶ አደሩን ማሰልጠን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ የቡና ምርታማነትንና ጥራት ለማሻሻል ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል በቡና ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ የምርምር ተቋማትን ማስፋፋት ነው፡፡ ብራዚልና ሌሎች ግንባር ቀደም ቡና አምራች ሃገራት በቡና ላይ ብቻ ምርምር የሚያደርጉ ብዛት ያላቸው ተቋማት ባለቤት ናቸው፡፡ ሌላው ሪከርድ ለሆነ የቡና ኤክስፖርት መመዝገብ ምክንያት ደግሞ ቡናችን ከማስተዋወቅ አኳያ የተሠሩ ስራዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ አገራችን 15ኛውን የአፍሪካ ልዩ ቡና አብቃዮች ማህበር ጉባኤ በማስተናገድ ቡናን አስተዋውቃለች፡፡

ሰፊ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ያገኘም ጉባኤና ኤግዚቢሽን ነበር፡፡ በጃፓን፣ በአሜሪካን፣ በዱባይ፣ በሀንጋሪ፣ በሴኔጋል፣ በቻይና፣ በህንድ በኤግዚቢሽን፣ በባዛርና በኤክስፖ በመሣተፍ ቡናን የማስተዋወቅ፣ አዳዲስ ገዥዎችን የማፍራትና ውል የማዋዋል ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የቀጥታ ትስስር አርሶአድሩን በቀጥታ ወደዉጭ ለመላክ አስችሎል፡፡ ዝቅተኛ የኤክስፖርት መሸጫ ዋጋም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረዉ።

ሲጠቃለል ዓመቱ ከኤክስፖርት ምርቶች ሁሉ የቡና ዓመት ተብሎ ሊታወስ የሚችል ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ የተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች እና የተገኘው ውጤት የበለጠ ማስቀጠል ከተቻለ ፋይናንሻል ታይምስ እንዳለው ኢትዮጵያ ከቡና የምታገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሣደግ ትችላለች፡፡

Related Post