አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ከየት አመጡት?

ከየት አመጡት
ከየት አመጡት

በመላኩ ብርሃኑ ብዙዎች ጋር ገንዘብ ቆሎ ሆኗል።እንደቀላል የሚዘገን እንደቀላል የሚበተን። ዕድሜያቸው ሰርቶ ለመበልጸግና ለአቅመ ሃብታም ለመድረስ ብዙ የሚቀራቸው ወጣቶች እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ህጋዊ ስራ ሰርተው (ለዚያውም ከቀናቸው) ከመጠለያ እና ከጡረታ ውጪ ምንም ገቢ ካልተረፋቸው አዛውንቶች በላይ እጅግ ሃብታሞች ናቸው።

ሳይበደሩ…ሳይሰሩ ነገር ግን ቆጥረው የማይጨርሱት፣ በትነው የማይረኩበት ገንዘብ አላቸው። አንዳንዶች ጭራሽ በአደባባይ ወጥተው ምን ያስጨንቅሃል ሲባሉ “ቁርስ በልቼ ምሳ ደግሞ የት ልብላ ብሎ ማሰብ ነው የሚያስጨንቀኝ” አይነት መልስ እየሰጡ በሚገባ ያላግጡብናል።

አንዳንዶችም “ሰዓቴ ምናምን ሺህ ዶላር ያወጣል” እያሉ እንደማህበረሰብ እንዴት እንደተራራቅን በደንብ እየነገሩ ‘RICH POOR GAP’ ያለማምዱናል።እነዚህ The tip of the iceberg ናቸው እንጂ ራሱ ግዙፉ የበረዶ ግግር ከስር ነው ያለው። አይታይም። ሚዲያም የማያውቃቸው ፣ በ’ሳይለንት ሙድ’ የሚንቀሳቀሱ ፣ ለአንድ ውስኪ 300ሺህ ብር ሲከፍሉ ‘ቅም’ የማይላቸው እልፎች ከተማዋን ሞልተዋታል። ሚዛናችን በጥሩ ሁኔታ ተዛብቷል።

በመሰረቱ ሰው ሃብታም መሆኑ መልካም ነው። የሁላችንም ምኞት ሃብታም መሆን ነው እኮ! ። ሰርቶ ያለፈለት፣ በላቡ በወዙ ሃብት ያፈራ የብር ፍራሽ ሰርቶ ላዩ ላይ ቢተኛበትም እሱን ከተመቸው ነውር የለውም። ሃቂቃው ነው። ለአንድ ሰው በዘነበ ቁጥር ለሌላ አንድ ሰው ማካፋቱ ስለማይቀር ሰው ያግኝ እንጂ ይጣ አይባልም።በተለይ ሰርቶ ሲያተፍር ካለው ለሚያካፍል ሰው ጨምሮ ጨማምሮ ይስጠው ነው የምንል !!

ችግሩ ሳይሰሩ፣ ምን እንደሚሰሩ ሳይታወቁ ፣ የገቢ ምንጫቸው ምን እንደሆነ ሁሌም ጥያቄ ሆነው የሚዘልቁ ሰዎች ከተማዋን መሙላታቸው፣ ሚዲያውም እነርሱን ማንቆለጳጰስ ማብዛቱ፣ በዚህም ማህበረሰቡ እና ወጣቶች አቋራጭ ሃብት ፍለጋ ላይ አይናቸውን ማማተር መጀመራቸው፣ ልጆች ገና ብቅ ሳይሉ ቶሎ በአቋራጭ ሃብታም የመሆን ህልም ውስጥ መዘፈቃቸው ነው።

አንድ ሰው ሳይሰራ ሃብታም ከሆነ ” ከየት አምጥቶ? ፣ እንዴት?” ብሎ መጠየቅ ምቀኝነት አይደለም። እንዲያውም የዜግነት ግዴታ ነው። ለተዘረፈ የህዝብ ሃብት መቆርቆር የጤነኛ እና የሰለጠነ ዜጋ ተግባር ነው። በርግጥ ሃብቱ ተዘርፎ ከሆነ እኮ ያ የህዝብ ሃብት የሁላችን ነው። ከዚያች ካለችን ጥቂት ሃብት ላይ አንዱ በኩንታል ፣ አንዱ በፌስታል ሌላው በእፍኝ ከሆነ የምንካፈለው እዚህ ላይ ነው ሚዛናችን ተዛብቶ እንዳንጠገን ሆነን የምንወድቀው።

ይህንን ለማስቀረት ሰዎች ‘ሾው ሲያበዙ’ ፣ ሃብታቸውን ካላያችሁልኝ፣ ካልጎበኛችሁልኝ ሲሉ “እሰይ እንኳን አገኘህ! እንኳን አለፈልህ! ግን ከየት አመጣህ” ብሎ መጠየቅ ለሰለጠነ ማህበረሰብ ጤነኝነት እንጂ ምቀኝነት አይደለም። እንዲህ ያሉ ሰዎች አደባባይ እንውጣ ካሉ በዚያው ልክ የሚተማመኑበትን፣ ቢመረመር የማያፍሩበትን የገቢ ምንጫቸውን ማሳወቅ ግዴታቸው ሊሆን ይገባል።ምክንያቱ ካላችሁም ባይከበርም ቅሉ ህጉ ገና ድሮ ይህንኑ እንድናደርግ አዝዞናል።

በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ ቁጥር 419 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብን በተመለከተ ያሰፈረው ድንጋጌ ሲብራራ እንዲህ ነው

“አንድ ሰው የኑሮ ደረጃው አሁን ከአለበት ወይም አስቀድሞ በነበረበት የመንግስት ስራ ወይም በሌላ መንገድ ከሚያገኘው ወይም ሲያገኝ ከነበረው ህጋዊ ገቢ የበለጠ እንደሆነ ወይም፣ 2. ያለው ንብረት ወይም የገንዘብ ምንጭ አሁን ከሚያገኘው ወይም አስቀድሞ በነበረበት ስራ ወይም በሌላ መንገድ ሲያገኝ ከነበረው ህጋዊ ገቢ ጋር የማይመጣጠን እንደሆነ፣እና 3. የዚህ አይነት የኑሮ ደረጃው እንዴት እንደኖረው ወይም ንብረቱ በእጁ እንዴት ሊገባ እንደቻለ ለፍርድ ቤት ካላስረዳ በስተቀር የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ እስከ አምስት አመት ሊደርስ በሚችል እስራት ይቀጣል፡፡” ይላል።

መቼም ይህ ህግ ለመንግስት ሰራተኞች ብቻ ነው የወጣው ብላችሁ ተስፋ እንዳታስቆርጡኝ እንጂ እንደአንድ ዜጋ ማንም ሰው ቢሆን ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ከያዘ (ህግ እስኪቀጣው ድረስ) ማፈርና መደበቅ፣ አርፎም መቀመጥ ሲገባው ሌብነቱ ሳያንሰው በየሚዲያው እየወጣ እንዲያላግጥ ሊፈቀድለት አይገባም ባይ ነኝ።

በተለይ አንዳንድ የሚያቀርቡት ወሬ ከሽቀላቸው ባለፈ ትውልዱን እንዴት እያጣመመ እንደሆነ የማይገባቸው ደናቁርት ለነዚህ አይነት ሰዎች መድረክ እየሰጡ ማንገስና ማህበረሰቡን ሙስናና ወንጀልን እንደጀግንነት እንዲለማመደው ማድረግ ማቆም አለባቸው።ማግኘት በስራና በስራ ብቻ መሆኑን ዛሬ ካላስተማርን ነገ የምናፈራው ትውልድ በሞታችን የሚነግድ ፣ በረሃባችን የሚሳለቅ፣ በችግራችን ኪሱን የሚሞላ ነው የሚሆነው። ሃይማኖቱም እኮ ” በላብህ በወዝህ ጥረህ ግረህ…” ይል የለ?

ምን ያደርጋል …ህግ አስከባሪውም፣ ህግ ተርጓሚውም፣ ህግ አስፈጻሚውም …ሁሉም ሌባ በሆነበት ሃገር ሌብነትን ማውገዝ ምቀኝነት እና ቅናት ሆኖ እየተወሰደ ነውና ወዴትም ፈቅ ሳንል ስንንፏቀቅ ልንኖር ነው። ምን አገባህ እንዳትሉኝ … ይህ ነገር ለነገአችን መልካምነት ጸር ነውና በጣም ያሰጋኛል ! የዘቀጥነው ህጋችን ከወረቀት የማይዘል ፉከራ ሆኖብን እኮ ነው ።
ሜርድ!!

Related Post