አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

በዋርካው ሥር እንጠለል

በዋርካው ሥር እንጠለል
በዋርካው ሥር እንጠለል

ከመኩሪያ መካሻ – ዋርካ መልቲሚዲያ ለማቋቋም ስንሰበሰብ ይህ የዛሬው አብሮነታችን ቶልስቶይን ያስታወሰኛል፡፡ አንድ የሊዮ ቶልስቶይ ገጽ ባህርይ “ከመሞትህ በፊት፣ አትሙት! (Don’t die before you are dead) ይላል፡፡ ምን ለማለት ፈልጎ ነው? አዎን እኛ ዝም ለማለት ፈልገን ዝም በማለታችን ለመሞት ተቃርበን ነበር፡፡

እኛ የሚዲያ ባለሙያዎች የለማ አእምሮ፣ ዕውቀትና ክህሎት በእጃችን ነው፡፡ ይህን በእጃችን ያለውን ሀብት አልተጠቀምንም፣ ለምን? ራስን መጠየቅ ነው፡፡ ዛሬ የተሰበሰብነው ከመሞታችን በፊት ላለመሞት ነው፡፡ ዋርካ የሚጠቅመን ለዚህ ይመስለኛል፡፡ መሰብሰቢያችን፣ አድባራችንና የወደፊቱን ርዕይ ዕውን የምናደርግበት የጋራ ቤታችን ነውና በዋርካ ሥር እንጠለል፡፡

ዳር ቆመን በመመልከታችን፣ የበይ ተመልካች በመሆናችንና ሚዲያው ሲደናቆር ውስጣችን ተክኗል፡፡ ዳር ቆሞ እሳት መሞቅ ይቁም! ይህ ዋጋ የለውም፡፡ በሚዲያው ኢንዱስትሪ ውስጥ ተሰብስበን ብንሠራ ተአምር እናመጣለን፡፡

ዛሬ አንዳንድ የኢትዮጵያ ሰዎች ታመዋል፡፡ በጎሰኝነት፣ በዘረኝነት፣ በበታችነት ስሜትና በመኮፈስ አባዜ (megalomania) ተለክፈዋል፡፡ በዚች ሀገር እስከሬን ላይ ለመጨፈር አሰፍስፈዋል፡፡ ሚዲያው ከዚህ ወረርሽኝ ያመለጠ አይደለም፡፡ ይህን ጉዳይ እጃችንን አገጫችን ላይ አድረግን በትዝብት መመልከት የለብንም፤ ሙያችንና ሚዲያው ወደ ትክክለኛውና ዕውነተኛ ሥፍራው እንዲመለስ ማረቅ ይኖርብናል፡፡ ትላንት የነበሩት ተምሣሌቶቻችን ሀዲስ ዓለማየሁ፡ ፀጋዬ ገ/መድህን፣ በዓሉ ግርማ፣ በርሃኑ ዘርይሁን፣ ከበደ አኒሳ፣ ማዕረጉ በዛብህ ዘራቸው ምንድነው? የዘር ቁስል አከው ያውቃሉን? ዘረኝነትና ጐሠኝነት የወስላቶችና የአፈጮሌዎች መሣሪያ ነው፡፡ ሰብረን እንጣለው፡፡

የኢትዬጵያ ሁኔታ ዛሬ ከባብኤል ማማ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ የባብኤል ማማ በወደቀ ጊዜ ብዙዎች በፍርስራሹ ቆስለዋል፡፡ ተደፍጥጠዋል፣ ብዙ ተስፋዎች፣ ምኞቶችና ሀሳቦች በፍራስራሹ ውስጥ ተቀብረዋል፡፡ እኛስ እንደዚያ ሁነን እንድንቀር ትፈልጋላችሁን? ይህ አይደረግም! እኛ ይህን ሁሉ ዕውቀት ክህሎትና ልምድ ይዘን ተቆራምደን አንቀርም፡፡ ሆሌም በፍርስራሹ ውስጥ ተስፋ እንዳለ እናስብ፡፡ እንደምታውቁት በእነዚያ አስፈሪ የመቃብር ሥፍራዎች እንኳ እጅግ ውብ አበባዎች ይበቅላሉ፡፡ የእኛ ዋርካም እንደዚያ ሊታይ ይገባል፡፡

አሁን የምንነጋገርባቸው የዋርካ ሀሳቦች የተተከሉት በትላንቱ ምኞት ውስጥ ነው፡፡ በትላንቱ የእኛ መብሰልሰል ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ መብሰልሰሉ እዚህ ላይ ይቁምና በዋርካችን ሥር እንጠለል፡፡ ሙያዊ ጨለምተኝነት ወደ ጠበበ ጉድጓድ ያመራናል፡፡ ከዚህ የጠበበ ጉድጓድ እንውጣና ትልቅ ነገር እናስብ፡፡ ወደፊት የምናልመውን የሚዲያ ግሩፕ(ተቋም )እናቁም፡፡

እኛ የምናቋቁመው ሚዲያ በዩኔስኮ የሚዲያ ዕድገት ማሳያዎች የሚለካ ይሆናል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሚዲያ ብዝሃነት አለው ይሉናል፡፡ እርግጥ ነው የግል፣ የመንግሥት፣ የማህበረሰብ፣ የሃይማኖት ድርጅቶች፣ የፖርቲ፣ በዘር ላይ የተመሠረተ ሚዲያ እየተባለ ቅርንጫፉን አብዝቷል፡፡ የታለ የሀሳብ ብዝሃነት? የታለ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን የመታደግ ዓላማ? በአንድ ፈረስ የሚጋልብ፣ በአንድ ቦይ የሚፈስ አሰልቺ ሚዲያ ነው ያለው፡፡

በዚህ መቀጠል አይቻለንም፡፡
እስቲ የሚዲያ ባለቤቶችን ጉደይ እንመልከት፡፡ ባለቤቱ እንደፈለገው ጋዜጠኛውን አፋዳሽ አጎንባሽ እያደረገው ነው፡፡ አሁን በቅርቡ በአንድ ሚዲያ የተፈጠረውን ያስታውሷል፡፡ ጋዜጠኛው ተባራሪ ጩሎ፣ የሚሸጥ ባሪያ ሁኗል፡፡ የሚዲያው ባለቤቶችና አመራሮች እንማን ናቸው? ከዚህ ከተሰበሰብነው ይበልጣሉን? ፍጹም የሚወዳደሩ አይደሉም፡፡ በዋርካ ሥር የሚፈጠሩት ሚዲያዎች ለውይይት፣ ለዲሞክራሲና ለሀሳብ መንሸራሸር መድረክ ይፈጥራሉ፡፡ እኛ በክልል፣ በጐሳ፣ በዕምነት፣ በፓርቲ ወዘተ. ተቀይደን መያዝ የለብንም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ሚዲያ የሚታየው ክልልነት ነው፡፡ አለመነጋገር ነው፡፡

የየራሱን ጎጆ መስርቶ የዚያች ጎጆ ንጉሥ መሆን ነው፡፡ እኛ ቱቦ ሳንሆን የብርሃን ሰርቅ የምንፈነጥቅ ሚዲያ እንሆናለን፡፡በአከራካሪ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንነጋገራለን፡፡ እስቲ የደያስፖራውን ሚዲያ እንኳ ተመልከቱ፣ ምን አመጣ? ዕውቀት፣ ልምድ፣ ወይስ የተሻለ ቴክኖሎጂ አመጣልን ? ያመጣልን ነገር ቢኖር አክቲቪዚምንና ጋዜጠኝነትን ባንድ ላይ መደወር ነው፡፡ ድወራው እኛ ስንጠናከር የግራ ፈትል ይሆናል፡፡ ለዚህ መሥራት የግድ ይሆናል፡፡

ዋርካ አገልግሎቱ ብዙ ነው፡፡ ዛሬ የሚዲያ ኢንፍራስትራክቸር ችግር አለብን፤ በከፍተኛ የትራንስሚተሮችና የህትመት ዋጋ ችግሮች ሚዲያው ተጠፍሯል፡፡ የኢንተርኔት ግንኙነታችን ከ15 በመቶ በታች ነው፡፡ ትልቁ ማነቆ ፋይናንስ እንጂ ሳንሱር አይደለም፡፡ በፋይናንስ አቅም ጠንክረን ስንወጣ ሚዲያው ይጠነክራል፡፡ ጋዜጠኛው የተሻለ ተከፋይ ይሆናል፡፡ ዋርካ ለዚህ ጥንካሬ ይሠራል፡፡ ያኔ በተሻለ ሥነ ምግባር ታንጾ ዕውነተኛ የሙያው ባለቤት ይሆናል፡፡

የልምድ አዋላጅነት በሚዲያ አሠራር ውስጥ እንዳይኖር ተግተን መሥራት ይኖርብናል፡፡ ማንም ከመንገድ ዘው ብሎ የሚጨፍርበት የጨረባ ተስካርነት ያቆማል፡፡ ዛሬ በሚዲያው ውስጥ እየሰለጠነ ያለው ባዶ ነፍስ ሀገሪቱን ወደ መቀመቅ ይከታታል፡፡ ኢትዮጵያን አይጠቅማትም፡፡ እዚህ ያለው ጋዜጠኛ ምሉዕ ነፍስ ያለው ነው፡፡ ባዶ ነፍስ ያለው ጋዜጠኛ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ባዶ ነብስ ያለው ጋዜጠኛ ከባዶ ኪሱ ጋዜጠኛ ይበልጥ አደገኛ መሆኑን እንገንዘብ፡፡

ሙያና የመሥራት ፍላጎት ያለን ጋዜጠኞች ባዶ ኪሶች አይደለንም፡፡ እኛ ራሳችን በዋጋ የማይተመን የሀብት ምንጮች ነን፡፡ ባዶ ኪስ ነን አንበል፤ እኛ ምሉዕ ነፍስ ነንና፡፡

የወደፊቱ ሚዲያችን ሁሉን አሳታፊ ነው፡፡ ነፃ ሆኖ መንግሥትንና ፖርቲዎችን የሚቆጣጠር ተቋም ይሆናል፡፡ይሞግታል፡፡ ጥራትና ብቃት ያለው መረጃ ለህብረተሰቡ ያቀርባል፡፡ በዘውጌ ፖለቲካ ታውሮ ጮቤ አይረግጥም፡፡ ለመንግሥት አጎብድዶ አያቋሽርም፡፡ ዕውቀት አለን፣ ልምድ አለን፣ ክህሎት አለን፣ ከሁሉ በላይ ለኢትዮጵያ ቀና መንፈስ አለን፡፡ በትልቅ ሀገራዊ ሚዲያ ዙሪያ ከተሰበሰብን ሀገራችንን ከገባችበት አዘቅት እናወጣታለን፡፡ “ከመሞትህ በፊት፣ አትሙት!” ነው መርሁ፡፡
(የዛሬ ፫ ዓመት የተፃፈ)
………
ዋርካ ሬዲዮ 104.1 ዛሬ ሃምሌ 8፣ 2014 የሙከራ ስርጭቱን ጀምሯል። በጥበቡ በለጠ
“ታላቅ ደስታ ነው። ታላቅም ዜና ነው። ምክንያቱም 105 የሚዲያ ባለሙያዎች በጋራ ሆነው፣ አክሲዮን መስርተው ያቋቋሙት ሬዲዮ ጣቢያ ነው። የሙያተኞች ሬዲዮ ጣቢያ። ዋርካ መጠለያ ነው። ዋርካ ሸንጎ መቀመጫ ነው። ዋርካ እርቀ ሰላም ማከናወኛ ስፍራ ነው። ዋርካ በጋራ ሰከን ብለው የሚነጋገሩበት ቦታ ነው። ዋርካ ብዙ መገለጫ አምዶች አሉት። እናም ፣ ዋርካ ሬዲዮ የኢትዮጵያዊያን የጋራ መጠለያ ሆኖ እንዲያገለግል ሙያተኞቹ ብርቱ ትግል ይጠበቅባቸዋል።
ይህን የሙያተኞችን ሕልም ዕውን እንዲሆን በርትታችሁ የሰራችሁ ሁሉ ፈጣሪ ውለታችሁን ይመልስ ዘንድ እመኛለሁ።”

Related Post