አርእስተ ዜና
Mon. Jan 27th, 2025

በእሳት መጫወት ቢበቃንስ?

በእሳት መጫወት ቢበቃንስ
በእሳት መጫወት ቢበቃንስ

በታምራት ሃይሉ – ትላንትና የተመለከትኩት ነገር መንፈሴን ሲረብሸው ነው የዋልኩት፤ በሩዋንዳ ሚዲያ ኮሚሽን ጋባዥነት ወደ ኪጋሊ ከመጣሁ ሰነበትሁ፤ ትላንትና የሩዋንዳ ጄኖሳይድ መታሰቢያ ሙዚየምን ለመመልከት ተገኝቼ ነበር።

ሩዋንዳውያን የዛሬ 28 አመት በዚህ ወር ተጀምሮ በርካቶችን ያሳጣቸውን ዘግናኝ ድርጊት በማሰብ ላይ ናቸው። ሙዚየሙ ከበሩ ጀምሮ የለቅሶ ቤት ድባብ ነው። ያለው፤ በጭፍጨፋው ካለቁት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ንፁሀን መሀከል የ258 ሺ ሰማዕታት ታሪክ ይዟል፤ ህጻን ወጣት ጎልማሳ ሽማግሌ ሴት ወንድ የተማረ ያልተማረው ወዘተ የሁሉንም ሰማዕታት ዘግናኝ ጭፍጨፋ በፎቶግራፍ በቪዲዮ በፅሁፍ ተደራጅቶ ይገኛል።

ባለሶስት ወለል የሆነው ሙዚየሙ በሁለተኛና በሶስተኛው ፎቅ ላይ ከዚህ በፊት በአይሁዳውያን ላይ የተፈፀመውን ፤ በቦስኒያ እንዲሁም በካምቦዲያ የተፈፀሙ ጄኖሳይዶችን ይዘክራል። ከሙዚየሙ ስወጣ በትኩስ ሬሳ ተሸክሜ እንደሚሄድ ሰው አይነት ስሜት ውስጥ ነው የወደቅሁት፤ ለምን ይሄ ሁሉ?

ዛሬ ከ28 አመታት በሃላም በመላ ሀገሪቱ ዜጎች ላይ ረብቦ የሚታየው ሀዘን መነሻው የሚዲያ ቅስቀሳ መሆኑን ቆም ብሎ ማሰብ ሚዲያ በማንኛውም አጋጣሚ በእጃቸው የገባ ሰዎች ሁሉ ሊያስቡበት ይገባል፤ ዛሬ በሀገራችን እዚህም እዚያም የሚታየው ብሄር ተኮርና ሀይማኖት ተኮር ግጭት የሩዋንዳን ጭፍጨፋ ሊያስንቅ ወደሚችል ጥፋት ሊከተን እንደሚችል መናገር በምንም መለኪያ ነብይነት አይደለም።

በንድፈ ሀሳብ ሳይሆን በተግባር ሀገራችን ወደዚያ መንገድ ጉዞ ለመጀመር እየቃተተች ነው። በእሳት መጫወት ሊበቃ ይገባል፤ ማንም ይህ ጉዳይ አይመለከተኝም ብሎ ቢመፃደቅ ራሱንና ልጆቹን ፤ህዝብና ሀገሩን ያጣል፤ ነገን የሚያስቀድሙ ዜጎች ሁሉ ዝምታቸውን ሊሰብሩ ይገባል። ከሚመጣው የሚረብሽ ነገር ይሰውረን፤

Related Post