አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

በኢትዮጵያ፣ግብፅ እና ሱዳን ድርድር ኢትዮጵያ በለጠች? ወይንስ ተበለጠች

በኢትዮጵያ፣ግብፅ እና ሱዳን ድርድር ኢትዮጵያ በለጠች? ወይንስ ተበለጠች
በኢትዮጵያ፣ግብፅ እና ሱዳን ድርድር ኢትዮጵያ በለጠች? ወይንስ ተበለጠች

በመኩሪያ መካሻ- ኢትዮጵያ፣ግብፅ እና ሱዳን ዛሬ በመሪዎች ደረጃ ተነጋገሩ።በሁለት ሳምንታት ውስጥ የጋራ ሰነድ በባለሙያዎች እንዲዘጋጅ ተስማምተዋል።በእዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ በለጠች? ወይንስ ተበለጠች? (ጉዳያችን አጭር ልዩ ዘገባ)

በዛሬው ድርድር ኢትዮጵያ በሶስት ጉዳዮች በልጣለች፣ግብፅ አንድ ጊዜያዊ ድል አግኝታለች። ዓርብ ሰኔ 19፣2012 ዓም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ፣የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ እና የሱዳኑ ፕሬዝዳንት አብዱላህ ሃምዶክ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ፕሬዝዳንት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎዛ ሰብሳቢነት በቪድዮ ስብሰባ አድርገው ነበር። በስብሰባው ውጤት መሰረት ሶስቱም አገሮች በሕግ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ የስምምነት ሰነድ የሚያዘጋጅ የባለሙያዎች ኮሚቴ ለመመስረት ተስማምተዋል።

በእዚህ ስምምነት መሰረት ይህ ኮሚቴ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሰነዱን አዘጋጅቶ እንደሚያቀርብ ነው የተነገረው።የግብፅ እና የሱዳንን መንግሥታት በምንጭነት በመጥቀስ የዓለም ዜና አውታሮች ሮይተር፣ኤኤፍፒ፣ሳውዲ ፕሬስ፣ዴይሊ ኒውስ፣አሶሼትድ ፕረስ እና የግብፁ አልሃራም ጭምር ኢትዮጵያ ከስምምነቱ በፊት ውሃውን አትሞላም እያሉ ማምሻውን ፅፈዋል።በኢትዮጵያ በኩል ግን እንዲህ የሚል ቃል አልተገባም።

አሶሼትድ ፕሬስ ብቻ ኢትዮጵያ ከስምምነት በፊት ውሃ አልሞላም አለች የሚል አልፃፈም።አሶሼትድ ፕሬስ ከኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በትውተር ገፃቸው ላይ ”ጠቃሚ ውይይት አድርገናል” ካሉት ውጪ የተሰጠ መግለጫ አለመኖሩን ነው የገለጠው።የአሶሼትድ ፕሬስ ከሁሉ የተሻለ ዘገባ ነው ያቀረበው።ምክንያቱም ሌሎቹ የግብፅ እና የሱዳንን መንግሥታት እየጠቀሱ ነው የፃፉት እንጂ የኢትዮጵያን መግለጫ አላካተቱም።

እዚህ ላይ በዛሬው ስምምነት ላይ በሁለት ሳምንት ውስጥ ቴክኒካል ኮሚቴው ሰነድ ያዘጋጅ ማለት በሁለት ሳምንት ውስጥ ባዘጋጀው ሰነድ ስምምነት ካልተደረሰ የክረምቱ ውሃ እስኪያልፍ ውሃ አትሞላም ማለት ሊሆን አይችልም።በኢትዮጵያ በኩል ውሃው የሚተኛበትን ቦታ የመመንጠር ሥራ በእዚህ ሳምንት ተጀምሮ በአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ለማጠናቃቅ እየተሰራ መሆኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በእዚህ ሳምንት አስታውቀዋል።ይህ ማለት እነኝህ ሁለት ሳምንታት ውይይት ተደረገም አልተደረገ ኢትዮጵያ የዝግጅት ጊዜዋ ነው። የዛሬውን ድርድር ሂደት እና ትርፍ እና ኪሳራውን ለማስላት የግብፅ እና የኢትዮጵያ ዋና ግብ ምንድን ነበር? ብሎ መጠየቅ እና ምላሽ ማግኘት ያስፈልጋል።

በመጀመርያ የግብፅ ፍላጎት ምን ነበር?
ግብፅ ዋና ዓላማዋ በአደባባይ ያለው ፍላጎት ውሃውን ሳንነጋገር አይሞላ ነው።የውስጥ ዓላማዋ ግን የዓባይ ግድብ የምስራቅ አፍሪካ የፀጥታ ችግር ነው በሚል ከነአካቴው በረጅም ጊዜ እንዲጠፋ ማድረግ ነው።ለእዚህም ዋና መንገድ ጠራጊ ያደረገቸው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት እና የአረብ ሊግን ነበር።በሁለቱ ድርጅቶች በኩል ግድቡ የፀጥታ ችግር ነው የሚል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ በሂደት የኢትዮጵያን ዕድገት ለማይፈልጉ ኃይሎች ግድቡን አሳልፎ መስጠት ነበር።

የኢትዮጵያ ፍላጎት ምንድነው?
ኢትዮጵያ የግድቡ ውሃ ሙሌት በእዚህ ክረምት እንዳያልፍ ትፈልጋለች።ዋናው የረጅም ጊዜዋ ግብ ግን ግብፅም የግድቡን ወደ ሥራ መግባት አምና የምትቀበልበት አንድ ዓይነት ውል መግባት እና ያረጀውን የቅኝ ግዛት ውል እንድትጥል ነው።ከእዚህ ውጪ ኢትዮጵያ አንዴ ግድቡን ወደስራ ታስገባው እንጂ በአንድ ሺ መንገዶች ወደፊት ተፅኖ የመፍጠር መንገዶች አሏት።ግድቡን ጨርሳ ወደ ሥራ ማስገባቷ በራሱ ከግብፅ አልፎ መካከለኛው ምስራቅ ላይም እጇ ረዘመ ማለት ነው።ስለሆነም የኢትዮጵያ ዋና ግብ በምንም መንገድ ሄዶ ግድቡን ወደ ሥራ ማስገባት ነው።

ሁለቱም አገሮች ውጥረቱ እንዲበርድ የሚፈልጉባቸው ምክንያቶች ምንድናቸው?
ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ውጥረት ቢያንስ በአሁኑ ወቅት መርገብ እንዳለበት የምታስብበት ምክንያት በቱርክ የሚደገፈው የሊብያ ኃይል ሰሞኑን ትሪፖልን ዙርያ በግብፅ የሚደገፈውን ኃይል ከማፅዳቱ አንፃር ግብፅ ትልቅ የፀጥታ ስጋት ስለጋረጠባት እና ምጣኔ ሀብቷ ጀርባ የሆነው የቱሪዝም ንግዱ በኮሮና ወረርሽኝ ሳብያ ስለተዳከመ ከሊብያ እና ከኢትዮጵያ አንዱን መምረጥ የግድ የሚላት ጊዜ ላይ ነች።

ከቱርክ፣ኢራን እና ሩስያ ጋር በቀጥታ መጋጨት የማይፈልጉት ነገር ግን በሊብያ ጉዳይ ውስጥ በቀጥታ እንድትገባ ከጀርባ የሚገፋፏት የምዕራብ አገሮችም ፍላጎት ግብፅ በሊብያ ጉዳይ እንድትገባላቸው ነው።ስለሆነም ለግብፅ በአሁኑ ጊዜ የዓባይን ጉዳይ በአንድ ዓይነት ውል አስሮ ወደ ጊዜ የማይሰጠው የቅርብ አደጋ የሊብያው ጉዳይ ላይ ማተኮር የግድ አለባት።በእዚህ ሳምንት የግብፅ መገናኛ ብዙሃን እያወሩ ያሉት ሊብያውያን ግብፅ ጣልቃ እንድትገባ እየጠየቁ ነው የሚል ሰፊ ዘመቻ ላይ ነው የሰነበቱት።

ይህ የሚያሳየው ግብፅ ወደ ሊብያ መዝመቷ እንደማይቀር ነው።ስለሆነም የዓባይ ግድብ ጉዳይ አሁን መርገብ እንዳለበት ግብፅ ታስባለች።መርገብ ያለበት ግን ግብፅ የተሸነፈች መስላ በሕዝቧ ውስጥ ታይታ ሳይሆን የሆነ ”የማርያም መንገድ” ዓይነት ብታገኝ ማፈላለግ ላይ ነበረች።የዛሬው የመሪዎች ውይይት እንዳበቃ ኢትዮጵያ ውሃውን ሳንስማማ አትሞላም የሚለውን ዜና በማውራት ሕዝቧን ድል እንዳገኘች ለማውራት የመፍጠኗ ምስጢርም ይሄው ነው።

ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አሁን ሽግግር ላይ እንደመሆኗ መጠን ምንም ዓይነት ግጭት ውስጥ (አስገዳጅ ካልሆነ በቀር) መግባት አትፈልግም።ምክንያቱም ውስጣዊ መረጋጋት እና ምርጫ ገና ይጠብቃታል።በሚፈጠሩ ግጭቶች ደግሞ ቢያንስ የግድቡን ወደ ሥራ የመግባት ዕድል ስለሚያደናቅፍ በተቻለ መጠን ዘለቄታዊ ሂደቱ ላይ አተኩራለች።

በእዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ በለጠች? ወይንስ ተበለጠች?
በዛሬው ስምምነት ኢትዮጵያ ተበለጠች? ወይንስ በለጠች? የሚለውን ለመመልከት ግብፅ እና ኢትዮጵያ ምን ነበር የሚፈልጉት የሚለውን መመልከት ስለሚገባ ከላይ ይህንኑ አስመልክቶ በመጠኑ ለመግለጥ ተሞክሯል።ይህ በእንዲህ እያለ ግን ማወቅ ያለብን ጉዳይ ግብፅ በመጪው ሰኞ ሰኔ 29/2012 ዓም የሰርግ እና ምላሿ እንደሚሆን ጠብቃ ነበር።ይሄውም የተባበሩት መንግሥታት 15 የፀጥታው ምክርቤት አባላት ግብፅ እና ሱዳን በዓባይ ግድብ ዙርያ ያስገቡትን ደብዳቤ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ተይዞ ነበር።

በእዚህ ስብሰባ ምክር ቤቱ ቢያንስ ሁለቱ አገሮች እንዲወያዩ ኢትዮጵያም ውሃውን መሙላት ብታዘገይ ሊል እንደሚችል ይገመታል።ይህ ቢደረግላት ኖሮ ግን ግብፅ ይህንን ውሳኔ አንቀፅ እየጠቀሰች ለስህተቱ ምክንያት ኢትዮጵያ ነች በሚል በዲፕሎማሲው መንደር ለመለፈፍ ተዘጋጅታ ነበር።

ኢትዮጵያ ቀደም ብላም የግድቡ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት በኩል ድርድር ሊደረግበት እንደሚገባ ገልጣለች።ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በደቡብ አፍሪካ ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት ይህንን ሃሳብ ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት አቅርበው ነበር።በወቅቱ ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአሜሪካ ድርድር እያደርጉ ነበር።
ስለሆነም ኢትዮጵያ ከዛሬው ድርድር ሶስት ድሎች አግኝታለች።ግብፅ ደግሞ አንድ ጊዜያዊ ድል አግኝታለች።

ኢትዮጵያ ያገኘችው –
1) ድርድሩን ከአሜሪካ ጉያ ወጥቶ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲመጣ ማድረግ መቻሏ እና ግብፅም ወደ እዚሁ መድረክ እንድትመጣ ሆኗል።

2) ኢትዮጵያ በመጪው ሰኞ በፀጥታው ምክርቤት የውሃ መሙላቱ ጊዜ ቢረዝም የሚል ሃሳብ ከመሰጠቱ በፊት በአፍሪካ ህብረት በኩል በሁለት ሳምንት የቴክኒክ እና ባለሙያዎች ኮሚቴ እንዲመሰረት መስማማቷ ኢትዮጵያ ሁለት ጥቅም ታገኛለች፣አንዱ ሰኞ የፀጥታው ምክርቤት ሳይናገር ቀድማዋለች። የዛሬው ውይይት ውጤትም ለፀጥታው ምክር ቤት እንደሚላክ በዛሬው ውይይት ወቅት ለማወቅ ተችሏል።ሁለተኛ ውሃውን አልሞላም የሚል ቃል ሳትገባ በሁለት ሳምንታት ውስጥ የሚቀርብ ሰነድ ለማየት ተስማምታለች።

3) ኢትዮጵያ ደረቅ ዲፕሎማሲ የምትከተል ሳይሆን ለሰላማዊ መግባባት ምን ያህል ርቀት እንደምትሄድ ዛሬ አሳይታለች።ግብፅ በሰሞኑ ሂደቷ ኢትዮጵያ ውሃ መቼም የመሙላት መብት የላትም አይደለም ስትል የሰነበተው።በአደባባይ ያለችው ውሃው የሚሞላው በእንዲህ ጊዜ ይሁን የሚል ”ውሃ የማይዝ” የማዘናጋት ሂደት ነው የተከተለችው።ጉዳዩ ውጥረት በመፍጠሩም በሚል በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ አገሮችም ሆኑ የሩቅ ተመልካቾች አላስጨነቃቸው ማለት አይቻልም።

ስለሆነም ኢትዮጵያ በዛሬው ድርድር የሁለት ሳምንታት ለጋራ ሰነድ ማዘጋጃ ጊዜ መስጠቷ ምን ያህል ጉዳዩ በሰላም እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላት ያሳየችበት ዕድል ፈጥሯል።ውጥረቱንም አላልታዋለች።ለግብፅ የሚሻላት ግን ውጥረቱ ማየሉ እና የፀጥታው ምክር ቤት ያሉ ወዳጆቿም ጉዳዩ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ችግር ነው ብለው ለማሳመን ጥሩ ምክንያት እንዲያገኙ ነበር።አሁን በሁለት ሳምንት መላላቱ ግን የፀጥታው ምክር ቤትም ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት ተይዟል በሚል በመጪው ሰኞ ስብሰባውን ሊሰርዘው የሚችልበት አጋጣሚ ሁሉ ሊኖር ይችላል።

ግብፅ ያገኘችው ጊዚያዊ ድል
ግብፅ በዛሬው ድርድር ያገኘችው ድል ጊዜያዊ የሁለት ሳምንታት የፕሮፓጋንዳ ድል ነው።ይሄውም ውሃውን ሳንስማማ እንዳትሞሉ ብለን ነበር።ይሄው ይህንን አስፈፅመን መጣን በሚል ለህዝባቸው መንገር ነው።ቀደም ብሎ እንደተገለጠው ኢትዮጵያ ውሃውን ሳንስማማ ላለመሙላት ተስማማሁ የሚል ቃል አልሰጠችም።በሁለት ሳምንት ውስጥ አንድ ሰነድ ተዘጋጅቶ ሶስቱም ሀገሮች ሊስማሙበት ነው ቀጠሮ የተሰጠው።ኢትዮጵያም የግድቡን የስራ ሂደት አላቆመችም።ውሃው የሚተኛበት ቦታ ምንጠራም በአንድ ወር ውስጥ ለምፈፀም በእዚህ ሳምንት ስራው ተጀምሯል።

ኢትዮጵያ የማታልፈው ቀይ መስመር
ኢትዮጵያ በዛሬው ስብሰባ ላይ የሁለት ሳምንታት ጊዜ ለአንድ የጋራ ሰነድ ማዘጋጃ ጊዜ ትስጥ እንጂ ከሁለት ሳምንታት በኃላ በሚዘጋጀው ሰነድ ላይ ካልተስማማች ውሃውን የመሙላቱን ተግባር ፈፅማ ልታቆም አይገባትም።ምክንያቱም ይህ ክረምት ውሃው በታቀደው መሰረት ካልተሞላ በአንድ ዓመት ውስጥ ብዙ ነገሮች ሊቀያየሩ ይችላሉ።ስለሆነም ዘንድሮ ውሃውን አለመሙላት ኢትዮጵያ ልትዘለው የማትችለው ቀይ መስመር ነው።በመሆኑም ውሃውን የመሙላት ጉዳይ ለድርድር ሊቀርብ የሚችል አይደለም።

ለማጠቃለል፣የግድቡ ጉዳይ በሰላም ሁሉንም አገሮች በተለይ የኢትዮጵያን የራሷን የውሃ ሀብት የመጠቀም ሉዓላዊ እና የማይገሰስ መብቷን አስከብሮ ስምምነት ላይ ቢደረስ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአካባቢው የቀጠናው ሀገሮች መልካም ዜና ነው።በመሆኑም ”ዊን ዊን” ድርድር እንዲሆን የሁሉም ምኞት ነው።ይህ ስምምነት ከተፈረመ እስከመቼውም ሰላም ይሆናል ማለት ግን አይደለም።ምክንያቱም ግብፅ የስልት ለውጥ አድርጋ የረጅም ጊዜ ዕቅድ አታወጣም ብሎ መናገር አይቻልም።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ኃይል መመንጨት ከጀመረ በኃላ ያላት አቅም ስለሚደረጅ የመደራደር አቅሟ በዚያው መጠን ስለሚያድግ ኢትዮጵያ አሁንም ተጠቃሚ ትሆናለች። በመጨረሻም የማኅበራዊ ሚድያው መንግስት በሚያደርገው የድርድር ውጣ ውረድ ላይ ከውስጥ ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ሳያውቅ እና የመንግስትን ስልታዊ አካሄድ ሳይረዳ በስሜት በመሄድ ለሕዝብ የተሳሳተ መረጃ እንዳያደርስ መጠንቀቅ አለበት።

Related Post