አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ምዕራባዊያን ያፈኑት የሶማሊያ ሐቅ

ምዕራባዊያን ያፈኑት የሶማሊያ ሐቅ
ምዕራባዊያን ያፈኑት የሶማሊያ ሐቅ

በእስሌማን ዓባይ – የአፍሪካዊ ሶማሊያን በጎ ተስፋዎችና ያሏትን ፀጋዎችን እን BBC፣ FOX፣ CNN እና መሰል የፕሮፓጋንዳ ዜና አውታሮች ለአለም ሊያሳዩ አይመርጡም።

ፔንታጎን በ2023 መግቢያ ላይ ያወጣው አንድ ሪፖርት “..በአፍሪካ የሽብር ጥቃት በ 300 እጥፍ ጨመረ..” የሚል ነበር። እንደ ሪፖርቱ በፈረንጆች 2021 በሶማሊያ ከተሰነዘሩ ጥቃቶች 89 በመቶው አልሸባብ ያደረሰው እንደሆነና ለ534 ሰዎች ሞት ምክንያት ነው” ይላል።

በሌላ ሪፖርታቸው ከጥር 1 – 2022 እስከ ሰኔ 30 – 2022 ባለው ጊዜ 699 የሽብር ጥቃቶች በአፍሪካ ተመዝግበዋል ብለዋል። በዚህም በአፍሪካ 5,412 ሰዎች ሞተዋል” በማለት በተደጋጋሚ ትንተናዎች፣ ዘገባዎችና መንግስታዊ መግለጫም እየሰጡበት ነው የሚገኙት።

ቁጥሮች አይዋሹም..፤ ባለፈው የፈረንጅ አመት በልዕለ ሀያሏ የአሜሪካ ምድር በጥይት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ሥንት ነው? እነሱ አይነግሩህም። እውነታው ግን አሜሪካ ውስጥ በ 2022 ከ 44,000 ሺህ በላይ ዜጎች በጥይት (አብላጫው በሽጉጥ) ተመትተው ተገድለዋል፤ በሃያሏ ሀገረ አሜሪካ..።

በአፍሪካ 54 ሀገራት እንዳሉ እና የአህጉሪቷ አጠቃላይ ህዝብም ከ 1.4 ቢሊዮን በላይ ስለመሆኑ ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ2022 መረጃ ያስቀመጠው።

ቀጥሎ ነው እንግዲህ የተምታታው ነገር የሚገኘው። ሲያሻቸው Jungle እስከማለት በጠሯት 1.4 ቢሊዬን ህዝብ ያላት አህጉር በአምሳ አራቱ ሀገራቷ 5,412 ሞት በአመት ተመዘገበባት የሚለው ከበሮ ተደለቀበት፤ አህጉረ አፍሪካም እጅግ አደገኛ ምድር ናት ሰሉም ይገኛሉ።
ይሁንና 333 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሀገረ አሜሪካ፣ በኢንዱስትሪ ደረጃ ብጥብጥ እየደረሰባት 44,000 ሺህ ዜጎቿ በሽጉጥ ተመትተው ሲገደሉ የትኩረት አጀንዳቸው አይሆንም። በቀውስ አመላካች ካርታዎች ላይም አሜሪካ 0 ስጋት ተብላ exceptional ቀለም ይሰጣታል – ደህንነቷ ፍፁም የተጠበቀ መሬት ናት በማለት….።

የምዕራቡ ሚዲያ ሶማሊያን “ከራሷ ጋር ጦርነት ውስጥ ያለች ሀገር” ሌላ ጊዜ ደሞ “መንግስት አልባዋ ምድር” ብለው ነው የሚጠሯት። ይቺ ሶማሊያ በአመት 534 ሰዎች ተገደሉባት፤ በዚህም Horror ናት – ጦር ልከን እንድረስላት እያሉም ነው። ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ብንጎረጉር ተከታዩን ሐቅ እናገኛለን።

~ጀርመን ውስጥ በ 2020 የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 782 ነው፤
~አሜሪካ ውስጥ በ 2020 የተገደሉ ሰዎች 19,400 ሲህን ይህ እያደገ ቀጥሎ በ 2021 ላይ ይህ አሃዝ በ 30 በመቶ ጨመረ።
በ 2022 ደግሞ በአሜሪካ 647 የጦር መሳሪያ ጥቃት ጥቃት ተፈፅሞ 44 ሺህ ዜጎች በአሜሪካ ሞተዋል – The Gun Violence Archive” የተሰኘው በጦር መሳሪያ ጥቃትና ህልፈቶችን የሚሰንደው የምዕራባዊያን NGO በይፋ ያስቀመጠው መረጃ።

ወደታፈነው የሶማሊያ እውነት ስንመለስ
የሽብር ፕሮፓጋንዳ ስርጭትን የሚመግቡ ሚዲያዎችን በሕግ እቀጣለሁ ያለው የሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መንግስት ነው። በዚህም የሶማሊያ ሚዲያዎችና ዜጎች በአጠቃላይ ከአልሸባብ ጋር የተያያዙ የፕሮፓጋንዳ ዘገባዎችንና የሽብር ተግባራቸውን፤ አስተሳሰባቸውን ጨምሮ የሚያሰራጩትን እንቀጣለን ስትል ይፋ አድርጋለች – በማስታወቂያ ሚኒስትሯ አብዲራህማን ዩሱፍ በኩል።

ሌላው ብሩህ እውነታ፣ ከወራት በኋላ ሶማሊያ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ EAC አባልነቷን ታረጋግጣለች የሚለው ብስራት ሲሆን፤ ጉዳዩ ለምዕራቡ ሚዲያ መርዶ ቢሆንም በሞቃዲሾ ግን እየሰራችበት ነው። [5] የ EAEC ህብረቱ አንድ የጋራ መገበያያ ገንዘብ የሚኖረው ሲሆን በወርቅ እንደሚሆን ነው አሁን ላይ የተያዘው አቋም። ይህ ደሞ ከሀገራቱ ተዘርፎ ይሸሽ የነበረውን ምንዛሪ የሚያስቀር ይሆናል። በ 2024 መጀመሪያ ላይም መገበያያ ገንዘቡ ይዘጋጃል ተብሏል።
አፍሪካን የአረብ ባሕረ-ገብ መሬት የሚያገናኘው የሶማሊያ ረጅም የህንድ ውቅያኖስ-ቀይ ባሕር መስመር ለአዲሱ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ አባላትም ሆነ ለሶማሊያ ከፍተኛ ምጣኔ ሐብታዊ ጥቅም የሚያስገኝ ነው።

ከአፍሪካ በ “ILLICIT CAPITAL FLIGHT” (ከ 2000-2015) ባለው ጊዜ ውስጥ 836 ቢሊዮን ዶላር ሸሽቶ መውጣቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ በቅርብ በወጣ ጥናት ደግሞ ወደ አፍሪካ በዬአመቱ 162 ቢሊዮን ዶላር እየገባ በተመሳሳይ አመት በህገ ወጥ የሚሸሸው ደግሞ 203 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ይገልፃል።

አፍሪካዊያንን በዘር እየፈረጁ በስልታዊ ዘዴ ማዋረድ የምዕራባዊያን ተግባር ሆኖ ነው።
“ነጭነት” እንደ እውነት እንደ ደግነት እና እንደ ቅዱስ… ጥቁርነት ደግሞ እንደ አረመኔ እንደ ውሸት እና ክፋት እንደሆነ ለማስመሰል ይሰራሉ።
በአፍሪካ የሀገረ ቻይና ኤምባሲዎች በኢንቨስትመንት ስፔሻሊስቶችና ሳይንቲስቶች ተሞልተው፣ የምዕራባዊያኑ ግን በፕሮፓጋንዲስቶች፣ በሴረኛ የሕግ ወጥመዶች፣ በ ThinkTank፤ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶቻቸውና በአጭበርባሪዎች የታጨቁ ናቸው።

በፕሮፓጋንዳ የተሰላቹ አፍሪካዊያን እምቢ ማለት የጀመሩ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካዊት ዶ/ር ናሌዲ ፓንዶር በሀገራቸው የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭን ከቀናት በፊት በተቀበሉበት ወቅት ምዕራባውያኑን በድፍረት ያስጠነቀቁትም ለዚሁ ነው። “ተከፋፈሉ፣ ተነጣጠሉ የሚሉንን አንቀበልም፣ ከማን ጋር ግንኙነት እንደሚኖረን የመወሰን መብቱ አለን” ነበር ያሉት።

የአልበርት አንስታይን አንድ አባባል ለምዕራባዊያን በጣም የተገባች ናት፤ – “እብደት ማለት አንድን ነገር በተመሳሳይ ዘዴ ደግሞ ደጋግሞ በመስራት የተለየ ውጤት መጠበቅ ነው።” ብሎ ነበር።

Related Post