አርእስተ ዜና
Mon. Jan 27th, 2025

መሪ ሆኖ ጠርጣራና ምክር አለመስማት ዳፋው ብዙ ነው

መሪ ሆኖ ጠርጣራና ምክር አለመስማት ዳፋው ብዙ ነው

በመኩሪያ መካሻ – አልጋ ወራሽ ተፈሪ፣ በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት በዘዴና በስልት ሥልጣናቸውን ካደላደሉ በኋላ የፖለቲካው ወንበር ላይ ያለተቃውሞ አልተቀመጡም። በየአቅጣጫው የተቃውሞ እሳት ይነሳባቸው ጀመር። የአልጋ ወራሽ ተፈሪ ስልታዊ ፖለቲካዊ አካሄድ ያስፈራቸው ወግ አጥባቂ ቡድኖች እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም።

በተለይ ከውጭ አገር ዜጎች ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መፍጠራቸው የፖለቲካ ሥልጣን ክንዳቸውን ለማጠናከር ረድቷቸዋል። በአንጻሩ ደግሞ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል። በአፍቃሬ ፈረንጅነት፣ በካቶሊክነት፣ አገር በመሸጥና አልፎም ተርፎም “ተፈሪ እና የሸዋ ተከታዮቹ የውሻ ሥጋ ይበላሉ” እስከሚል ክስ ወረደባቸው።



ተፈሪ ግን ይህንን ክስ እንዲህ በዋዛ አልተመለከቱትም። ሰላማዊ ውይይት ወይም ድርድር ሳይሆን የፈረጠመውን ጡንቻቸውን ማሳየት አስፈለጋቸው። በአማፂው የንግስት ዘውዲቱ ባለቤት በራስ ጉግሳ ወሌ ላይ የአውሮፕላን ቦምብ በማዝነብ ፀጥ ለጥ አደረጓቸው።

ኃይልና ጉልበት የፖለቲካው መነጋገሪያ ሆነ። የባለቤቷ በዚህ ሁኔታ መውደቅ ያስደነገጣት ንግሥት ዘውዲቱም ልቧ ቆሞ እስከ ወዲያኛው አሸለበች። ተፈሪ ንጉሥ ከተባሉ በኋላ የጋዜጦች የመፃፍ ነፃነት እንኳ ኮስሶ ከ1921 በኋላ ወደ አወዳሽነት ዞሩ። እነሆ እስካሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ጋዜጦች በአዝማሪነታቸው ቀጥለዋል። ይህም እንዲሁ በድንገት የመጣ ሳይሆን ነባሩ ፖለቲካዊ ባህላችን ያሳደረውን ተፅዕኖ ያሳያል።

የራስ ተፈሪ ፖለቲካዊ ብልጥነት እንዲህ በቀላሉ እንደማይታይ ብርሃኑ ድንቄ ሲጽፍ፣ “ራስ ተፈሪ ሰው አያምኑም፤ በቀላሉ የሰው ምክር አይከተሉም። ወሬ ከማንም ሰው መስማት ይፈልጋሉ። እንደሚቀናቸው ካላመኑ በቀር አንድ ነገርን ለመጀመር ያመነታሉ። በሴትና በመጠጥ አይታለሉም” ብሏል።

የአጼ ኃይለሥላሴ ፍፁማዊና መለኮታዊ አገዛዝ ያስገኘው አዲስ ነገር በ1923 ዓ.ም የመጀመሪያውን፣ በ1948 ዓ.ም ደግሞ የተሻሻለውን ሕገ-መንግሥት ማምጣቱ ነው። ሕገ-መንግሥቱ በንጉሡና በመሳፍንቱ መካከል ያለውን የሥልጣን ሚዛን የሚደነግግ ሲሆን፣ ባህሩ ዘውዴ እንደሚለው “የህዝቡን መብትና ግዴታዎች የሚገልጹ አንዳንድ አንቀፆች የገቡትም እንዲህ አይነት አንቀፆች የሌሉትን ሕገ- መንግሥት ሰው ፊት ማቅረብ ስለማይቻል ይመስላል” ሲል ለይስሙላ እንደቀረበ አትቷል።

“ተፈሪ ንጉሥ ከተባሉ በኋላ የጋዜጦች የመፃፍ ነፃነት እንኳ ኮስሶ ከ1921 በኋላ ወደ አወዳሽነት ዞሩ። እነሆ እስካሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ጋዜጦች (ሚዲያ) በአዝማሪነታቸው ቀጥለዋል”



ለይስሙላነቱ እንዲሁ የተፈጠረ አልነበረም። የዚያን ወቅት የፖለቲካ ባህል አስተሳሰብ ስንኩል መብት እንዲሰጥ ሆኖ በመታሰቡ ሕገ-መንግስቱን ሽባ ያደረገ ነበር። የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት መሳፍንት እና መኳንንት ሲሆኑ፣ እነሱም በቀጥታ በንጉሠ-ነገሥቱ የሚሰየሙ ናቸው። የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላቱ ደግሞ ለይስሙላ በህዝቡ የሚመረጡ የመሬት ከበርቴዎች ነበሩ።

እኔ እንኳ በልጅነቴ የማውቃቸውና ለሊሙ አውራጃ እንደራሴነት የተወዳደሩት ራቢያ አብዱልቃድር የባላባት (ቆሮ) ልጅ ነበሩ። ዴሞክራሲ ላልተማረውና ተራው ህዝብ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ቦታ አልነበረውም ተብሎ ይታሰባልና ላልሰለጠነ ህዝብ አይበጀውም በሚል ቦታ አላገኘም። ይህም የኋላ ኋላ ዳፋው ለንጉሱ ውርደትና ውድቀት በር ከፈተ።

Related Post