አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ሃገርን ከጠላት ለመከላከል ጥሪ ሲቀርብለት “አቤት” የሚል ወጣት ለምን አጣን?

ሃገርን ከጠላት ለመከላከል ጥሪ ሲቀርብለት "አቤት" የሚል ወጣት ለምን አጣን?
ሃገርን ከጠላት ለመከላከል ጥሪ ሲቀርብለት "አቤት" የሚል ወጣት ለምን አጣን?

በመላኩ ብርሃኑ – መቶ ሚሊዮን ያለፍን ታላቅ ህዝቦች ነን። 60 በመቶ ህዝባችን ጡንቻው የደደረ፣ ልቡ የጋመ፣ ጉልበቱ የጠነከረ አፍላ ወጣት ነው። ወታደር የሚሆን ወጣት ግን እያጣን ነው።ለምን?

እኛ ጋ ሲደርስ አለመታደል ሆኖ ይጣጣላል እንጂ ውለታና መስዋዕትነቱን አውቆና አበክሮ ቦታ ለሚሰጠው ህዝብና ሃገር ወታደርነት እጅግ ክቡር ሙያ ነው፣ አኩሪ ሙያ! እንኳን ወታደሩ ፣ ልጅ ልጆቹና ዘመድ አዝማዶቹ ደረታቸውን ነፍተው የሚኮሩበት ሙያ ነው።

ልጅ እያለን ስናድግ መሆን የምንፈልገውን ስንጠየቅ ቢያንስ ከመሃላችን ግማሻችን “ወታደር” ብለን እንመልስ ነበር። በኮባ ቅጠል ጠመንጃ እየሰራን ‘ጠላትና ኢትዮጵያ’ እያልን ተኩስ ስንጫወት ፣ ደግሞም ስናሸንፍ ዘንግ ላይ ያሰርነውን ጨርቅ እንደባንዲራ እያውለበለብን በክብር እየዘመርን ስንተክል ….ሃገርን ስለመውደድ፣ ከጠላት ስለመከላከል ፣ በመስዋዕትነት ስለመኩራት ፣ ስለጀግንነት እና ብሄራዊ ስሜት እያሰብን ስንዘምር ነው እኛ ያደግነው። ወታደርነት ከሁሉም ሙያ እኩል የብዙዎቻችን ራዕይ ሆኖ ኖሯል።

በተለይ ወታደር ለሃገሩ የሚከፍለው መስዋዕትነት ፣ በሶማሌ ጦርነት የፈጸመው ጀብዱ፣ የሻዕቢያን ሰራዊት ያሳድድበት የነበረ ጀግንነት፣ በትግራይ ተራሮች መሃል የተወሸቁ ወንበዴዎችን ይመታበት የነበረ ጠንካራ ክንድ እየተነገረው፣ የምስራቅ እና ሰሜን ጦር ሜዳ ውሎና ታሪኩ በሚገባ የተሰነደበትን “ድላችን ኤግዚቢሽን” እየጎበኘ ፣ ድምጻውያን በዘፈን ግጥሞቻቸው ሲያወድሱት እየሰማ ፣ የሃገር ፍቅር፣ የትግል እና የድል ዘፈኖችን አፍ መፍቻው አድርጎ ላደገ ለእኔ ትውልድ ወታደርነት ማለት ቁመናውን ሲያዩት ደም የሚያሞቅ፣ ዩኒፎርሙን ሲያዩት ልብ የሚያኮራ ፣ የጀግንነት ውሎና መስዋዕትነቱ ሲተረክ ሲሰማ አንገት ቀና የሚያደርግ ክቡር ሙያ ነበር።

ደርግ ጎረቤት ሃገራት በፍርሃት የሚርዱለት፣ የቀድሞ ጀግኖች አባቶቹን አደራ የተቀበለ እና ኢትዮጵያን “እናት ሃገሬ” ብሎ የሚጠራ ፣ ባንዲራዋን እያየ ሲዋጋ ደረቱን ለጥይት መስጠት የማያሳሳው የአየርም፣ የባህርም፣ የምድርም ምርጥ ኢትዮጵያዊ ወታደር መፍጠር ችሎ ነበር።

ኢህአዴግ ሲመጣ ይህንን የልብ ኩራት መስበር፣ ልፍስፍስ ትውልድ መፍጠር አቅዶ ብዙ ለፋ። ሃገር ግድ የማይለው፣ ታሪክ የማይስበው፣ ባንዲራ ግዱ ያይደለ፣ ኢትዮጵያዊ ደሙ የቀዘቀዘ ትውልድ ለመፍጠር ብዙ ብዙ ሰራ። ድላችን ኤግዚቢሽንን አወደመ። የወታደሩን ታሪክና ቅርሶች በተነ። ወታደሩን ራሱን ከነቤተሰቡ፣ ከነቤቱ፣ ከነመከላከያ ተቋሙና ከክብር አልባሳቱ ጭምር አፈራርሶ አራገፈው።

ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብለው የተነሱባትን ጠላቶች አፈር አስግጦ ቀብሮና በላያቸው ላይ ባንዲራውን ተክሎ በውድ ህይወቱ መስዋዕትነት በአጥንቱ ስባሪ አጥሯን የገነባውን ወታደር አሳደደው። ደርግ ከነብዙ ድክመቱም ቢሆን “አብዮታዊ ሰራዊታችን” እያለ የሚያንቆለጳጰሰውን የሃገር መከላከያ ሰራዊት ኢህአዴግ ” የደርግ ወታደር” ብሎ አንገቱን አስደፋው። ወታደር የሚለውን እጅግ የተከበረ ስም ታጋይ በሚል ስም ቀየረው።ፕሮፌሽናሉን የወታደርነት ሙያ በጫካ ትግል ተዋናዮች ትርክት ትቢያ ውስጥ ቀላቀለው። እንኳን ወታደሩ ዘመድ አዝማዱ ሁሉ አጥንቱ ድረስ በሚዘልቅ ስድብና በተቀነባበረ ማዋረድ አንገቱን እንዲሰብር አደረገው።

“ንክኪ” እያለ እያሳደደ በገዛ ሃገሩ ወድቆ እንዳይነሳ አድርጎ በተነው። ለሃገሩ ህይወቱን የሰጠውን ፣ በስንት ጦር ሜዳ ጀብዱ የፈጸመውን ጀግና የውጊያ መሃንዲስ መንገድ ላይ ፎቶግራፉን አንጥፎ የሚለምን ስንኩል ነዳይ አደረገው። ወታደሩ የፈጠራቸው ልጆቹና ሚስቱ ተርበው ብዙ ቤት ተበተነ፣ ብዙዎች በአባቶቻቸው ወታደር መሆን ብቻ የደርግ ልጆች እየተባሉ ከማንኛውም ጥቅም ታግደው ሁለተኛ ዜጋ ሆኑ፣ ጎስቋላ ህይወት መሩ። ይህንን ያየ የኢትዮጵያ ወጣት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልቡን ከወታደርነት ምኞት፣ ፊቱን የወታደር ቤትን ከማየት ገለል አደረገ።

በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ግን ጉድለቱ አፍጥጦ መጣ። የምክር ቤቱ ተቃዋሚዎች ጦርነቱን ሲቃወሙ መለስ ዜናዊ ግን ተሳለቀ።” ወታደር አዋጡ ብለን የምንጠይቅ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፣ ያለን ሃይል ይበቃናል” አለ። ወታደር መሆን እንዳያስብ ተደቁሶ የኖረው ወጣት ግን ኢትዮጵያዊ ነውና የሃገሩ ክብር ሲደፈር ቁጭ ብሎ ማየት አላስቻለውም፣ ምክንያቱም ደሙ የኢትዮጵያዊ ነውና።

ነገር ግን በአሳዛኝ ሁኔታ ሆን ተብሎ የጥይት እራት እንዲሆን ተደረገ። የኢትዮጵያን ወታደር ደም የላሰው ጅብ ገና ምላሱ ሳይደርቅ ኢህአዴግ “ጦርነቱን አሸነፍን” ብሎ መርዶ መቀመጥ የነበረበትን ህዝብ በልጆቹ ደም ላይ አደባባይ አስወጥቶ አስጨፈረው። እነዚያ የኢትዮጵያ ብርቅ ልጆች ግን የበረሃ ሲሳይ ሆነው ወደቤታቸው አልተመለሱም።

እነሆ ዛሬ ላይ ደረስንና የዚያ ሁሉ ወታደር ህይወት በአንድ ክልል ውስጥ የተገበረባት ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶቿ በግራና ቀኝ ሲነሱ የምትመክትበት ክንድ የሳሳ መስሎ ቢሰማት ዜጎቿን ለወታደርነት ጠራች። ወጣቱ ግን ለዘመናት በወታደርና ወታደርነት ላይ የተሰራው ግፍ እና 27 ዓመት ሙሉ ወታደሩን አስመልክቶ በየሰዉ ዐዕምሮ የተጫነው የስነልቦና መርግ ተጽዕኖ ፈጥሮበት ያንን ክባድ ጥሶ መውጣት አልቻለም።

እስኪደክመው ሳይሆን እስኪሞት ለመስራት ቃሉን ሰጥቶ በዱር በገደሉ የሚማስነው ወታደር እነሆ ዛሬም የቀድሞውን ትርክት ለማስቀጠል በሚደረግ ትግል ስሙና ምግባሩ በየአደባባይ እንዲህ ሲዋረድ ወጣቱ እያየ ነው። በገዛ ሃገሩ ሞቶ እያኖረ ውለታው የሚዘነጋ፣ ቆስሎ እያዳነ ስሙ የሚጠለሽ መለዮ ለባሽ እያየ ወጣቱ ወታደር መሆንን ባይመኝ ምን ይገርማል!!

አሁን ኢትዮጵያ ከእንቅልፏ ነቅታለች። ጥቅሙን ለሚያጣጥል ፣ ውለታውን ለሚያኮስስ ተግባር የኢትዮጵያ ወታደር ከዚህ በላይ እንዲዋረድ መፍቀድ አይገባም። እስካሁን ለተሰጠው አደራ የከፈለውን የህይወት ምላሽ በክብር ዘክሮ እረፍት መስጠት ያስፈልጋል። ነገ ወታደር እንዲሆን የሚፈለገውን ወጣት ኢትዮጵያዊ ግን የዚህ አይነት ረብ የለሽ ሚሽን በዚህች ሃገር ዳግም እንደማይኖር ፣ ቢሞትም ዳር ድንበሩን ከውጭ ወራሪዎች የመጠበቅ ታሪካዊ ሃላፊነቱን ሲወጣ በክብር እንጂ በሃገሩ ዜጎች እንዲህ ተዋርዶ እንደማይሆን አረጋግጦ ዛሬም እንደጥንቱ ለሃገሩ ክብር እንዲቆም በክብር መጥራት ያስፈልጋል።

በተራ የጋዜጣ ማስታወቂያ አይደለም! በክብር መጥራት!!
ግብጽና ሱዳን ከራሳችን ከወጣው ጠላት ጋር ተደምረው ሊበሏት ያሰፈሰፉባት ኢትዮጵያችን አደጋ አንዣቦባታልና መንግስት ህዝቡን በተለይም ወጣቱን ያለፈውን ረስቶ እንደአባቶቹ በክብር ለሃገሩ ዘብ እንዲቆም መጥራት አለበት። ወታደር አጣሁ ብሎ ሪፖርት ማቅረብ ሃገርን ‘ይሄኔ ነው መግጠም’ ለሚል ፈሪ ጠላት ጥቃት ማመቻቸት ነው።

ቀልድ አይደለም !! መንግስት ያስብበት!! ሃገር ያለጠንካራ መከላከያ ሃይል ለደቂቃ እንቅልፍ ተኝታ ማደር የለባትም!!

Related Post