አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

ከ135000 በላይ አርሶ አደሮች በቴክኖሎጅ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለፀ

ከ135000 በላይ አርሶ አደሮች በቴክኖሎጅ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለፀ
ከ135000 በላይ አርሶ አደሮች በቴክኖሎጅ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለፀ

ከ135000 በላይ አርሶ አደሮች በቴክኖሎጅ ሽግግርና የተሻለ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለፀ።

ሶስተኛው የተቀተናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደገለፁት መንግስት የግብርና ዘርፉን በማዘመን እና ምርቶችን ላይ እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በማዋል ከውጭ የሚገባውን የምርት መጠን መሸፈን አስፈላጊ መሆኑን ገለጹ።

ምርት ወደ ውጭ በመላክ አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚጫዎተውን ሚና በላቀ ደረጃ ለማሳደግና የኢኮኖሚ ሽግግሩን የተሳካ ለማድረግ ሶስት የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል።

በሶስቱ ፓርኮች የምግብ ማቀነባበሪያ ከገነቡ 21 አልሚዎች መካከል 5ቱ ወደ ስራ በመግባት ምርታቸውን ወ ደውጭ እየላኩ መሆኑን ጠቅሰው 100 ተጨማሪ አልሚዎች በፓርኮች ውስጥ ስራ ለመጀመር ፍላጎት ያሳዩ በመሆኑ ከመንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም በፓርኮቹ በተፈጠረው የስራ ትስስር 135000 አርሶ አደሮች በቴክኖሎጅ ሽግግርና የተሻለ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና የአስር ዓመት የእድገት እቅድ ላይ በግልፅ እንደተመላከተው በግል ዘርፉ የሚመራ ኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል እየሰራ በመሆኑ በፓርኮች ውስጥ ለመሰማራትና መዋለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ያላቸውን ባለሀብቶች አስፈላጊውን ሁሉ ማበረታቻና ድጋፍ በማመቻቸት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በበኩላቸው ለሚቀጥሉት አራት አመታት በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚሰሩና ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው መንግስት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚ ለመለወጥ እየሰራ መሆኑ ትክክለኛ የለውጥ አቅጣጫ ላይ ስለመሆኑ አመላካች በመሆኑ የሚደነቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን በሚፈለገው መንገድና ጊዜ ለማሳካት ሰላምና መረጋጋት መስፈን የሚጫወተው ሚና ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት በቁርጠኝነት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአፍሪካ ልማት ባንክ ካንትሪ ማናጀር ዶ/ር አብዱል ካማራ የአፍሪካ ልማት ባንክ ለተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ስራ 50 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በአጋርነት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ባንኩ እንደዚህ አይነት የኢኮኖሚ ልማት ስራዎች ላይ የገባው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱ የሚያሳየው አፍሪካን ኢኮኖሚ ለመለወጥ አርሶ አደሩን መደገፍ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብለዋል፡፡

Related Post