አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

የታክስ ሕግ ተገዥነት

የታክስ ሕግ ተገዥነት
የታክስ ሕግ ተገዥነት

የታክስ ሕግ ተገዥነት ማለት መንግስታት የታክስ ገቢን ለመሰብሰብ ያወጡትን የታክስ ህጎችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን እና መርሆዎችን በፈቃደኝነት በማክበር የግብር እና ቀረጥ ግዴታዎችን በተገቢው ጊዜ እና መንገድ መወጣት ማለት ነው፡፡

እያንዳንዱ የታክስ አስተዳዳር ከግብር ከፋዮቹ የሚጠብቀው መሠረታዊ ግዴታዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም፡-
1. በግብር ከፋይነት መመዝገብ፣
2. ግብርን በወቅቱ እና በትክክል ማሳወቅ፣
3. በትክክል ሪፖርት ማድረግ ወይም ትክክለኛ ደጋፊ ማስረጃዎች ማቅረብ እና
4. ግብርን መክፈል ናቸው፡፡

1. በግብር ከፋይነት መመዝገብ፡- እያንዳንዱ በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኝ እና በግብር ከፋይነት መመዝገብ የሚጠበቅበት ግለሰብ እና ተቋም በሙሉ በራሱ ተነሳሽነት ወደ ታክስ መረቡ መምጣት እና በግብር ከፋይነት መመዝገብ ይገባዋል፡፡ መመዝገብ ለሚመለከተው የታክስ ዓይነት ሁሉ መመዝገብን ይጨምራል፡፡ ለአንዱ የታክስ ዓይነት ተመዝግቦ ለሌላው አለመመዝገብ የህግ ተገዥ አያሰኝም፡፡

በእኛ አገርም ያለው የግብር ከፋዮች ምዝገባ ሥርዓት የጣት አሻራ መስጠትን፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ማውጣትን እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ የሂሳብ መዝገብ መያዝን የሚያካትት በመሆኑ እያንዳንዱ ግብር ከፋይ እነዚህን ሥርዓቶች አሟልቶ በግብር ከፋይነት መመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡

2. ታክስ ማስታወቅ፡- በሌላ በኩል ከአንድ በግብር ከፋይነት የተመዘገበ ግብር ከፋይ የሚጠበቀው ሌላኛው ግዴታ የግብር ሰብሳቢው ተቋም ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ እና ባስቀመጠው ግብርን የማሳወቂያ መንገድ ተጠቅሞ ለግብር ሰብሳቢው ተቋም መክፈል የሚገባውን የታክስ መጠን ማሳወቅ ነው፡፡ ይህም ማለት ከነበረው የሽያጭ መጠን እና በህግ የተፈቀዱ ተቀናሽ ወጪዎች አንጻር እንዲሁም በህግ በተቀመጡ የታክስ ቀመሮች አንጻር ለገቢ ሰብሳቢው መክፈል የሚገባው የታክስ መጠን በራሱ አስልቶ ግብር ሰብሳቢው ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ እና ባዘጋጀው መንገድ ማሳወቅ ነው፡፡ ገቢዎች ሚኒስቴር እንደ ታክሶቹ ዓይነት የማሳወቂያ የጊዜ ሰሌዳ ያስቀመጠ ሲሆን በተቀመጠው አግባብ ማሳወቅ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ለየታክስ/ግብር አይነቱ የተለያየ ማስታወቂያ ቅጾች የተዘጋጁ በመሆኑ ቅጾቹን በአግባቡ ሞልቶ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮም ተቋሙ ግብር ከፋዮች በኤሌክትሮኒክስ መንገድ በቀጥታ ካሉበት ሆነው ግብራቸውን የሚያሳውቁበት ስርዓርአትንም ዘርግቷል፡፡

3. ሪፖርት ማድረግ፡- የሚጠበቅበትን የግብር መጠን ያሳወቀ ግብር ከፋይ ያሳወቀው የታክስ መጠን ትክክለኛ ስለመሆኑ በደጋፊነት ሊያስረዱለት የሚችሉ የተለያዩ ሪፖርቶችን ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህም ሪፖርቶች በዋናነት የገቢ መግለጫ /income statement/፣ የሂሳብ መዝገብ /balance sheet/፣ የገንዘብ ፍሰት /cash flow/ እና የመሳሰሉትን ያካትታሉ፡፡

4. ታክስ መክፈል፡- በአራተኛ ደረጃ ከአንድ ግብር ከፋይ የሚጠበቀው ግዴታ በራሱ ፈቃድ መክፈል ይገባኛል በማለት አምኖ ያሳወቀውን እንዲሁም በተለያዩ ሪፖርቶች ያረጋገጠውን የታክስ መጠን በግብር ሰብሳቢው ተቋም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መክፈል ነው፡፡ ይህም ማለት አመታዊ የሆኑትን በየዓመቱ በተቀመጠው ጊዜ፣ ወርሃዊ እና ሌሎቹንም በተቀመጠላቸው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት መክፈል ነው፡፡

በአጠቃላይ፤ የታክስ ህግ ተገዥነት ማለት እነዚህን እና ሌሎች ከታክስ ጋር የተገናኙ ግዴታዎችን በራስ ተነሳሽነት መወጣት ማለት ሲሆን ከገቢዎች ሚኒስቴር አንጻር የህግ ተገዥነት ማለት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዲያስፈጽም የተሰጡትን የጉምሩክ እና የታክስ ህጐችን፣ ደንቦችን እና መመሪያዎችን በፈቃደኝነት በማክበር፤ የግብር እና የታክስ ግዴታዎችንም መወጣት ማለት ነው፡፡

መረጃዎች በተንቀሳቃሽ ምስል
https://youtu.be/vr0dfqIrsro

Related Post