ከሚቀጥለው ሐምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ በኦላይን እንዲሆን ለማድረግ የሪፎርም ስራ እየተከናወነ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
ይህ የተገለጸው በትናንትናው እለት ለ60 አመታት ያገለገለውን የንግድ ህግ በአዋጅ ቁጥር 1243/2013 በቀየሩን ተከትሎ ለሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር የንግድ ዘርፍ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በንግድ ህግ አዋጅና የበየነ መረብ ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በተሰጠበት ወቅት ነው።
የዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐሰን መሀመድ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት የሀገራችንን የንግድ ስርዓት ቀላል፣ ቀልጣፋና ፍትሐዊ በማድረግ አለማቀፋዊ ተቀባይነቱን ለማሻሻልና የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን በማቀላጠፍ ዘርፉ ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ በማሰብ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን፣ የኤክስፖርት ምርቶችን በመጠንና በገቢ ለማሳደግ፣ የምርቶችን አቅርቦት ጥራት ለማሻሻል፣ የንግድ አሰራር ስርዓታችንን ከአለማቀፋዊ ንግድ ህግጋት ጋር የተቀናጀ በማድረግ ሀገራችን በዓለም የንግድ ስርዓት ውስጥ ተገቢውን ስፍራ እንድታገኝ በማስቻል የገበያ መዳረሻዎቻችንን ለማስፋትና የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶት ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻ የሰልጠናው ተሳታፊ የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከስልጠናው የሚያገኙትን እውቀት ተግባር ላይ በማዋል ዘርፉን በማሻሻል የተሳለጠ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ዕውን መሆንና የንግድ ዘርፉ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተውን ጉልህ ድርሻ በማሳገድ ረገድ እየተሰሩ ላሉ ስራዎች ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡