አርእስተ ዜና
Mon. Jan 27th, 2025

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ሊያደርግ ነው

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ሊያደርግ ነው
ቢጂአይ-ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ሊያደርግ ነው

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ በአሰራሩ፣ በማምረት ሂደቱ እና በስርጭት ሞዴሉ ላይ ወሳኝ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ሊያደርግ መሆኑን ገለፀ።

ኢንቨስትመንቱ የኩባንያውን ፋብሪካዎች የማምረት አቅም መጨመር እና እንዲሁም ታሪካዊውን የአዲስ አበባ ፋብሪካ ሰበታና ማይጨው ወደሚገኙት ሁለቱ የቢራ ፋብሪካዎቹ ማዛወርን ያካትታል። የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚ/ር ሄርቬ ሚልሃድ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲናገሩ

“ይህ ኢንቨስትመንት ኩባንያችንን የበለጠ ተወዳዳሪ ለማድረግና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶቹን ለውድ ደንበኞቹ ለማቅረብ ከምንሰራቸው ዋና ዋና ፕሮጀክቶች አንዱ ነው” ብለዋል። የቢጂአይ-ኢትዮጵያ ስትራቴጅካዊ ለውጥ መተግበር ያስፈለገው ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከተፈጠረው የገበያ ለውጥ፣
በኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚታየው አጠቃላይ ተወዳዳሪነት ጋር እርምጃውን ለማስተካከል፣ እንዲሁም የኩባንያውን እድገት ለማፋጠንና ጠቅላላ አመለካከቱን ለማሻሻል ነው።

ሚልሃድ “ድርጅታችን በኢትዮጵያና በገበያዋ ከፍተኛ አቅም እንዳለ እናምናለን” ብሏል። “ኢትዮጵያ እያደገችና እየተለወጠች ስትሄድ የገበያውን ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አሰራር ለመዘርጋት ተዘጋጅተን ወደ ተግባር ገብተናል” በማለት አክለዋል። የፕሮጀክቶቹ ትግበራ በኩባንያው አሠራርና በገበያው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ይታመናል።

“ራዕያችን በሚቀጥሉት አመታት የማምረት አቅማችንን በእጥፍ በማሳደግ በዓመት ወደ 10 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ለማድረስ ነው” ሲሉ ሚልሃድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም “ይህን ትልቅ አላማ ለማሳካት በሰራተኞቻችን፣ በምርቶቻችን፣ በደንበኞቻችንና በምንኖርበት
ማህበረሰብ ላይ ኢንቨስት እናደርጋለን” ያሉ ሲሆን “በመካሄድ ላይ ካሉት ዋና ዋና ተግባራት አንዱ በማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የማምረት አቅሙን ማሳደግ ነው” ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

“በውሃ አቅርቦት ውስንነትና የሎጂስቲክስ ተግዳሮቶች ምክንያት በአዲስ አበባ መሓል ከተማ የሚገኘውን ታዋቂውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካችንን ለማዛወር የተገደድን ቢሆንም ይኸው ችግር ራሱ የሌሎች ፋብሪካዎቻችንን የማምረት አቅም ለማሳደግ እድል ፈጥሮልናል” ሲሉም ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

በተጨማሪ “ቢጂአይ-ኢትዮጵያ ድርጅታዊ መዋቅሩን በማደስ ተመራጭ አሰሪ ድርጅት ለመሆን እየሰራ ይገኛል” ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል። ቢጂአይ-ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባሉት ሰባት ፋብሪካዎቹ ለ3,500 ቋሚ ሰራተኞች እና 2,000 ጊዜያዊ ሰራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን የለውጡ ግብም በእያንዳንዱ የስራ ክፍል ውስጥ ያሉትን አስፈላጊ ክህሎቶች እና ሂደቶችን በመለየት የተግባር ልህቀትን በመላ ኩባንያው ማምጣት ነው።

“የስራ ሚና መደራረብን በመቀነስ፣ አሰራራችን በማዘመንና በማሻሻል ሰራተኞቻችንን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ለመዘርጋት በቁርጠኝነት እየሰራን ነው” ብለዋል ዋና ስራ አስኪያጁ። ለዚህ አንዱ መገለጫው ኩባንያው ከጊዜያቸው በፊት ቀድመው ጡረታ የወጡና እድሚያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ
የኩባንያው ጉምቱ ሰራተኞች እንዳገለገሉባቸው ዓመታት መጠን እስከ 48 ወራት የሚጠጋ ደሞዝ በመክፈል በክብር ለማሰናበት የፈጠረላቸውን እድል መጥቀስ ይቻላል።

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ ለመተግበር ካቀዳቸው የኢንቨስትመንትና የሰው ሃይል አስተዳደር ማሻሻያ ስራዎች ባሻገር የምርት ስርጭቱን ለማዘመን አዲስ ስትራቴጂ በመቅረፅ ወደ ተግባር ገብቷል። በምርት ስርጭት ላይ የሚተገበረው ፕሮጀክት የሽያጭ አሰራራችን በማዘመን የሽያጭ ሰራተኞችንና ወኪሎቻችን ወደ ደንበኞች የበለጠ ቀርበው እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመ ነው። ቢጂአይ-ኢትዮጵያ በዓመት ከ7.4 ቢሊዮን ብር በላይ ታክስ በመክፈል በኢንዱስትሪው የፕላቲኒየም ግብር ከፋይ ነው። ቢጂአይ-ኢትዮጵያ ለውድ ደንበኞቹ፣ ለሰራተኞቹ፣ ለሽያጭ ወኪሎቹና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ተጠቃሚነትን
ለማምጣት በኃላፊነት ስሜት የንግድ ስራውን የሚያከናውን ድርጅት ነው።

የቢጂአይ-ኢትዮጵያ እናት ኩባንያ የሆነው ካስቴል ግሩፕ ለኢትዮጵያ ገበያ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች አምርቶ ማቅረብ ከጀመረ ከ25 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ገበያውን ለማልማት ባለው ቁርጠኝነት የስራ እድል በመፍጠርና የኢኮኖሚ እድገት በማምጣት በህብረተሰቡ ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ ለማሳደር አስችሎታል።

ቢጂአይ ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ የግል ድርጅቶች ትልቁ ግብር ከፋይ ድርጅት ሲሆን የሜታ አቦ ፋብሪካን (ሰበታ) ጨምሮ የተለያዩ ፋብሪካዎችን በመግዛትና የምርት አቅማቸውን በማሳደግ እድገት እያስመዘገበ ይገኛል። በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች ማለትም በማይጨው (ራያ)፣ በኮምቦልቻ፣ በሀዋሳ፣ በዘቢዳር እና በዝዋይ የሚገኙት ፋብሪካዎቻችን ተደራሽነቱን አፍተውለታል።

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ፣ ካስቴል ቢራ፣ ሜታ ቢራና ድራፍት ከማምረቱም በተጨማሪ እንደ አካሺያ፣ ሪፍት ቫሊ የመሳሰሉ የወይን ምርቶችን ያመርታል። ኩባንያው 3,500 ቋሚ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን ለአስርት አመታት ለማህበረሰባችን ድጋፍ በማድረግ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

Related Post