አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

በወጪ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች የዉጪ ምንዛሪ ተጠቃሚነት ጨመረ

በወጪ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች የዉጪ ምንዛሪ ተጠቃሚነት ጨመረ
በወጪ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች የዉጪ ምንዛሪ ተጠቃሚነት ጨመረ

በሃቅ መልቲሚዲያ : ነሃሴ 5፤2015 – በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣዉን የዉጪ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች የሚያገኙትን የዉጪ ምንዛሪ መጠን የሚጨምር ደንብ ማውጣቱን ዛሬ አስታወቀ።

ዛሬ ነሃሴ 5፤2015 ይፋ የሆነው መመሪያ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ወደ ሃገር ዉስጥ ከሚያስገቡት የዉጪ ምንዛሪ ዉስጥ ግማሹን ወይም 50 በመቶዉን እንዲጠቀሙበት ይፈቅድላቸዋል። ይህን የገለጹት 10ኛው የብሄራዊ ባንክ ገዢ የሆኑት አቶ ማሞ ምህረቱ ናቸው። እንደ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጻ ከሆነ፤ አዲሱ ደንብ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ቀድሞ ይጠቀሙበት የነበረዉን የ30 ከመቶ የዉጪ ምንዛሪ ድርሻ ከፍ ያደርገዋል።

በዚህም መሰረት አንድ ነጋዴ ለምሳሌ የ10 ሚሊዮን ዶላር ቡና ወደ ዉጪ ሃገር ቢልክ፤ 5 ሚሊዮን ዶላሩ በቀጥታ ለመንግስት ጠቀመታ ወደ ብሄራዊ ባንክ ገብቶ ለላኪው በእለቱ የምንዛሪ ዋጋ የሚተላለፍ ይሆናል። ከተቀረው 5 ሚሊዮን ዶላር 1 ሚሊዮን ዶላር ላኪው አብሮት የሚሰራው ባንክ በተመሳሳይ መልኩ በእለቱ የምንዛሪ ዋጋ ሲጠቀምበት፤ የተቀረው 4 ሚሊዮን የዉጪ ምንዛሪ ግኝት የቡና ላኪው ለሚፈልገው አገልግሎት እንዲያዉለው አዲሱ መመሪያ ይፈቅዳል።

በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች በገቢ ንግድ የተሰማሩ እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ አዲሱ መመሪያ እነዚህ ነጋዴዎች ወደ ሃገር ዉስጥ የሚያስገቧቸው ሸቀጦች እንዲጨምሩ አስተዋጽዎ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶቹ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይም እንደመሰማራታቸው የሚያጋጥማቸዉን የጥሬ እቃና የመለዋወጫ መዘግየት በተወሰነ መልኩ ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጻ ከሆነ፤ አዲሱ ደንብ የብሄራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሃሴ 1፣2015 ተሰብስቦ ካወጣቸው የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች ዉስጥ አንዱ ነው። የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎቹም በሃገሪቱ እየጨመረ የሚገኘዉን የዋጋ ንረት ለመቀነስ ያለሙ መሆናቸዉን የባንኩ ገዢ ተናግረዋል።
https://www.youtube.com/watch?v=GEPUH2Zn4Pc

Related Post