አርእስተ ዜና
Thu. Dec 26th, 2024

ስለህገ-ወጥ የዶላር ምንዛሪን ከፌዴራል ፖሊስ የተሰጠ መግለጫ

ስለህገ-ወጥ የዶላር ምንዛሪን ከፌዴራል ፖሊስ የተሰጠ መግለጫ

በሀገራችን ላይ የተለያዩ ሴራዎችን ሲያካሂድ የቆየው የአሸባሪው የህወሃት ጁንታ ቡድንና ተላላኪዎቹ ፊት ለፊት ከሚያካሂዱት ሀገር የማፍረስ ሴራ ጎን ለጎን በሀገሪቱ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠርና ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲማረር የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ መሆናቸው ተደርሶበታል፡፡

በዚህ መሰረት የሽብር ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረባቸው አመታት በዘረጋቸው ኔትዎርኮችና ቅጥረኞች አማካኝነት ከአዲስ አበባ ቶጎ ውጫሌን፣ ሞያሌን፣ መተማንና ሌሎች የመውጫ በሮችን በመጠቀም ኮንትሮባንድ ዝውውር ላይ በመሳተፍና ዶላርን በጥቁር ገበያ እየገዛ የዶላር እጥረት እንዲከሰት ከማድረግ ባሻገር በርካታ የጥፋት ተግባራትን ሲያካሄድ የቆየ መሆኑን ቀደም ሲል በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ስድስት ድርጅቶች ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ስለመሆኑ ባስተላለፍነው መረጃ ተደራሽ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል ጋር በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ለሽብር ቡድኑ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩ 117 የንግድ ድርጅቶች እና መኖሪያ ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የአሸባሪው ቡድን የፋይናንስ ምንጭ እንዲደርቅ የሚያደርጉ ተግባራትን አከናውኗል፡፡

ውድ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፡- የአሸባሪው ቡድን ከፍተኛ የገቢ ወይም የፋይናንስ ምንጭ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የዘረጋቸውን ኔትዎርኮች በመጠቀም ዶላርን በጥቁር ገበያ በውድ ዋጋ መሰብሰብ እና የሃዋላ አገልግሎትን መጠቀም እንደሆነና ከዚህ በሚያጋብሰው ገቢም የጦር መሳሪያ ግዥን በመፈፀም ለጥፋት ተልዕኮው እንደሚጠቀምበት ፌዴራል ፖሊስና የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል በሀገር ውስጥና በውጭ ሃገርም ባካሄዱት ረጅም ጊዜ የፈጀ ጥናትና በተደረገ ምርመራና ክትትል ደርሰውበታል፡፡

በጥናቱም ኔትዎርኮቹን የመለየት ስራ የተከናወነ ሲሆን በኔትዎርኮቹ ውስጥም፡-
1. አርዓያ (የዞማ የውበት ሳሎን ባለቤት) አሜሪካ የሚኖር
2. ሳሙኤል (ሳሚ ዶላር) አሜሪካ የሚኖር
3. ጣዕመ መርከብ አሜሪካ የሚኖር
4. ሄኖክ (ዲሲ)- አሜሪካ የሚኖር
5. ሃብቶም ዶላር (ፈረንሳይ የሚኖር)
6. ኤሊያስ (ዱባይ የሚኖር)

የተባሉት ግለሰቦች የሚገኙበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚልኩትን ዶላር አየር በአየር ግብይት በመፈፀም እንዲሁም ዶላሩን እዚያው ውጪ እንዲቀር በማድረግ ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ የፋይናንስና የሎጀስቲክ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባችኋል፡፡

በህገ-ወጥ መንገድ የአሜሪካን ዶላርን ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ እየተላላኩ ሀገራችን ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ በማድረግ ረገድ፡-
1. መንግስቱ ወርቁ (እስራኤል፣ ቴል አቪቭ የሚኖር)
2. አቪ ፈጠነ (እስራኤል የሚኖር )
3. አስቴር ባልትና (ፕሪቶሪያ የምትኖር )
4. እቴነሽ (ፕሬቶሪያ የምትኖር)
5. ዮናታን ትሬዲንግ ጂፒ (ጆሃንስበርግ የሚኖር)
6. ሄኖክ ባልትና (ጆሃንስበርግ የሚኖር)
7. እሙ (ደርባን የምትኖር)
8. መሐመድ ሼክ ጀማል እና ፋሚ ሼክ ጀማል (ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ)

ግለሰቦችና ድርጅቶች እጃቸው እንዳለበት በምርመራ ስለተረጋገጠ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ብሄራዊ ኢንተርፖል እነዚህን ግለሰቦችና ድርጅቶች ለህግ ለማቅረብ ስም ዝርዝራቸውን ለአለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ልኮ በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡

ስለዚህ ውድ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ይህ አሸባሪ ቡድን ለሽብር ድርጊቱ ማስፈፀሚያነት የሚጠቀመውን ገንዘብ የሚያገኘው በዚህ መንገድ መሆኑን በመገንዘብ ከዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ቡድን ጋር ባለመተባበር ሀገር ወዳድነታችሁን እንድታስመሰክሩ እንዲሁም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በዚህ ህገ-ወጥ ድርጊት ላይ የተሰማራችሁ ዜጎች ጉዳቱ ለመላው ሀገሪቱ ነውና ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Related Post