አርእስተ ዜና
Thu. Dec 26th, 2024

ምክር ቤቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫው እንዲካሄድ ወሰነ

ምክር ቤቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫው እንዲካሄድ ወሰነ
ምክር ቤቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫው እንዲካሄድ ወሰነ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ አስቸኳይ ስብሰባው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተራዝሞ የነበረው 6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የመከላከል ስራውን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በ2013 በጀት አመት ማካሄድ ይቻላል በሚል የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ህብርተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባስቀመጡት ምክረ- ሀሳብ መሠረት ቫይረሱን በመከላከል ምርጫውን ማከናወን እንደሚቻል ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የዳሰሳ ጥናት አድርጎ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረቡ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም መደረጉን ያስታወሱት ወ/ሮ አበባ ካሉት ትንበያዎች አንጻር ወረርሽኙ ረዘም ላለ ጊዜ አብሮን ሊቆይ የሚችል በመሆኑ ይህንኑ ግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ስነ-ምግባር ደንብና መመሪያ በማዘጋጀት ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን የጤና ሚኒስቴር ባቀረበው ሪፖርት ማረጋገጥ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ማህበረሰቡ በቫይረሱ ዙሪያ ያለውን ግንዘቤ በማስፋትና መዘናጋት እንዳይፈጠር ሰፊ የንቅናቄ ስራዎችን በመስራት ምርጫውን ማካሄድ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡ ከቫይረሱ ጋር ሆነው ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ምርጫ ያከናዎኑ ሃገራት ለአብነት ከውጭ ፈረንሳይና እስራዔል፤ ከአፍሪካ ደግሞ ጊኒ፣ ቡሩንዲ፣ ማሊና ዝምባብዌ ምርጫ ማካሄድ እንደቻሉ የምክር ቤቱ አባል አወቀ አጥናፉ /ዶ/ር/ በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

ወ/ሮ አበባ በበኩላቸው በቫይረሱ ላይ ጥብቅ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እንደሚሰራ ገልጸው ፣ ምርጫ ቦርድም ከዛሬ ጀምሮ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባት የሚያስችለው ሁኔታ መኖሩን ነው የገለጹት፡፡ የውሳኔ ሃሳቡም የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 16/2013 ሆኖ በአንድ ተቃውሞ በ8 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

ምክር ቤቱ መስከረም 8/2013 ባካሄድው 5ኛ ዙር 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥና ቀጣይ እርምጃዎች የቀረበውን ሪፖርትና ምክር ሃሳብ በዋናነት ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱ ይታወሳል፡፡

Related Post