የአፍሪካ የቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ኢንስቲትዩት የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ከአባል አገራቱ አምባሳደሮች እና ተወካዮች ጋር የቆዳው ዘርፍ በሚያስገኘው ጠቀሜታ ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥን ዓላማ ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት እንደተገለጸውም አፍሪካ ከፍተኛ የጥሬ ቆዳ ሃብት ባለቤት ብትሆንም በዓለም ገበያ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ያክል ገቢ አላገኘችም፡፡
ለዚህም ዘርፉ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ አለመረዳት፣ በጥራት አለማከናወንና እሴት ባለመጨመር ጥሬ ሃብቱን ብቻ ወደ ውጪ መላክ እንደ ዋነኛ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
የአፍሪካ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ኢንስቲትዩት የዋና ዳይሬክተሩ አማካሪ ፕሮፌሰር መኮንን ሃይለማርያም እንደገለጹት አፍሪካ ካላት የቆዳ ሃብት አንጻር እዚህ ግባ የሚባል ገቢ እያገኘች አይደለም፡፡ ለአብነትም በ2019 በቆዳ ዘርፍ በዓለም የተደረገው ግብይት 260 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ጠቁመው ከዚህ ውስጥ አፍሪካ ያገኘችው 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከአንድ በመቶ በታች ድርሻ ያለው ነው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ አገራትም ከዘርፉ የሚገኘውን ከፍተኛ ሃብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኢንስቲትዩቱ እሴት የሚጨምሩ ስልጠናዎችንና የገበያ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ስራዎችን እየተከናወነ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የውይይቱ ዋና ዓለማም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ለማሳሰብ ነውም ብለዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከኮሜሳ አባል አገራት በተጨማሪም ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ክፍት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር መኮንን ገለጻም አፍሪካ በዓመት ከውጪ አገራት 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው የቆዳ ውጤት ታስገባለች። ይህም አፍሪካ ያላት ከፍተኛ የቆዳ ሃብት ላይ እሴት ጨምራ ወደ ውጭ መላክ ሲገባት ለአህጉራዊ ፍጆታም በቂ የሆነ ምርት እያመረተች አለመሆኗን ያመላክታል ብለዋል፡፡
ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም የሚታዩ ማነቆዎችን መፍታት፣ ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ሃይል መምራትና አስፈላጊውን ግብዓት መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ሚልኬሳ ጃገማ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በቆዳ ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በቆዳው ዘርፍ የፖሊሲ ችግር፣ ለባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ያለማድረግና የእንስሳት ልማት ጤንነት ላይ በትኩረት ያለመስራት ችግር እንደሚስተዋል ገልጸዋል፡፡ እነኚህን ሁሉ ማነቆዎች በጥናት ለመፍታትና ኢትዮጵያን ወደ ቦታዋ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቆዳው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት አፍሪካ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እንድታገኝ አገራት በቅንጅት መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ የቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ኢንስቲትዩት በኮሜሳ ውስጥ ለታቀፉት አገራት ብቻ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ክፍት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ምንጭ – ኢዜአ