አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚላኩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ቀጥለዋል

ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚላኩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ቀጥለዋል
ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚላኩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ቀጥለዋል

በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች ለሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚላኩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚላኩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ወደ አካባቢው የተላኩት ምግብ፣ አልሚ ምግብ፣ መድኃኒት፣ የግል ንፅሕና መጠበቂያ እንዲሁም የትምህርት እና የግብርና ቁሳቁስ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በተጨማሪም ነዳጅ እና ጥሬ ገንዘብ በመንግሥት በኩል እየቀረበ እንደሆነም አብራርተዋል።

እስከ ጥር 8፣ 2015 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 29 የውጭ ሀገራት አጋር አካላት እና መንግሥት 149 ሺህ 496 ነጥብ 33 ሜትሪክ ቶን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የዕርዳታ ቁሳቁሶች፤ 1 ሺህ 562 ነጥብ 76 ሜትሪክ ቶን መድኃኒቶች እና 4 ሺህ 154 ነጥብ 94 ሜትሪክ ቶን አልሚ ምግቦች ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል መላኩን ጠቁመዋል።

መንግሥት ዕርዳታዎችን እያደረሰ ያለው አጋር አካላት መሸፈን በማይችሉበት ቦታ ጭምር እየገባ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደበበ፤ ከቀረቡ ሰብዓዊ ድጋፎች ውስጥ 15 ሺህ 023 ነጥብ 25 ሜትሪክ ቶን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እንዲሁም አንድ ሚሊየን 113 ሺህ 953 ሊትር ነዳጅ በመንግሥት ማቅረብ መቻሉን ነው የተናገሩት።

እንደ አቶ ደበበ ገለፃ፤ መንግሥት በትግራይ ክልል ለሥራ ማስኬጃ የሚውል አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብርም በጥሬ ገንዘብ ወደ ሽሬና መቀሌ ልኳል። ገንዘቡ ከከተሞቹ ወደየአካባቢው የሚሰራጭ እና ለአገልግሎት እና ለሥራ ማስፈፀሚያ የሚውል ነው።

የሰብዓዊ ዕርዳታዎቹ በየብስ እና በአውሮፕላን እንደተጓጓዙ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በየብስ የተጓጓዙ ዕርዳታዎች 3 ሺህ 745 ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ማጓጓዝ እንደተቻለ ተናግረዋል። በተመሳሳይ በአውሮፕላን መድኃኒት እና ገንዘብ ለማጓጓዝ በአጠቃላይ 38 በረራዎች መደረጋቸውንም አክለዋል።

ድጋፉን በሰመራ አብአላ ኮሪደር፤ በኮምቦልቻ አላማጣ ኮሪደር እና በጎንደር ሁመራ ሽሬ እንዲሁም በጎንደር አዲአርቃይ ማይፀብሪ እና ዲማ እንዲጓጓዝ ተደርጓልም ብለዋል።
ምንጭ፣ አዲስ ዘመን ጥር 11 /2015

Related Post