አርእስተ ዜና
Thu. Dec 26th, 2024

ኢትዮ ቴሌኮም 5 በመቶ ድርሻ ለኢትዮጵያ ዜጎች ሊሸጥ ነዉ

የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ማሻሻያ ስራዎች ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ውይይት ተካሂዷል።

ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር እና ተጨማሪ የቴሌኮም ኮርፖሬሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የተወሰነው ውሳኔ ሂደት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ተገምግሟል። በውይይቱ ላይ ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል ሲዘዋወር 40 በመቶ ድርሻ ለአለም አቀፍ ኩባንያዎች እንደሚተላለፍ ተነግሯል።

5 በመቶ ድርሻ ደግሞ ለኢትዮጵያዊያን ዜጎች በአክስዮን ይሸጣል ነው የተባለው። ይህ 5 በመቶ አክስዮን በጥቂት ግለሰቦች የሚያዝ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ እንደ አቅሙ የሚሳተፍበት መሆኑ ተጠቁሟል።

ቀሪውን 55 በመቶ ድርሻ መንግስት እንደያዘው እንደሚቀጥልም ተነግሯል። በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርን ለማዘመን የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ በከፊል ከማስተላለፍ ባሻገር ለሁለት አዳዲስ ኦፕሬተሮች ፈቃድ እንደሚሸጥ ተገልጿል።

ሁለቱ አዳዲስ ኦፕሬተሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምና ልምድ ያላቸው እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን የሚያሸጋግሩ ይሆናሉ ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፈቃድ የመስጠትም ሆነ በከፊል የማዘዋወር ስራዎች ከሌብነት በፀዳ፣ ሙያዊ አካሄድን በተከተለ እና የምናስበውን ጥቅም ለሀገር ማስገኘት በሚችል መልኩ ይከናወናል ብለዋል።

ዘርፉን ሊብራላይዝድ የማድረግ ሂደቱ የፓሊሲ ግፊት የሌለበት እና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የቀረቡ መርሆች እና አቅጣጨዎች ላይ ተመስርቶ የሚሄድ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዲጂታል ልማትን ማጎልበት፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ተደራሽነትን እና ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ፣ ብቃት እና ጥራት ላይ ያተኮረ አለም-አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ መገንባት እና ከዘርፉ ከፍተኛ ሃብት አገሪቱ እንድታገኝ ማስቻል የሚሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በቴሌኮም ዘርፍ የማሻሻያ ሥራዎች ቁልፍ የፖሊሲ ዓላማዎች ተብለው ተቀምጠዋል።
(ምንጭ – ኤፍ.ቢ.ሲ)

Related Post