በኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ228 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች የመድህን ሽፋን መግኘታቸውን የመድህን አስተዳደር ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ አስታወቁ።
ኤጄንሲው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የስራ አፈፃፀምና የ2013 ዓ.ም የመነሻ እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ መክሯል። ዋና ዳይሬክተሯ በምክክሩ ወቅት በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተካሄደው ንቅናቄ በአስቸኳይ የህክምና እርዳታ፣በፈንድ አሰባሰብና በመድህን ሽፋን ተደራሽነት የላቀ ውጤት ተመዘግቧል።
በዚህም ከ228 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች የመድህን ሽፋን መግኘታቸውን ጠቅሰው ከ90 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብ ከፈንድ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል። በተመሳሳይ በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ከ25ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት በ240 የሆስፒታሎች ማግኘታቸውን አመልክተዋል።
ኤጄንሲው ለህክምና እርዳታው ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ አገልግሎት ለሰጡ የጤና ተቋማት መክፈሉን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሯ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማብዛት ከጤና ቢሮዎችና ጤና ሚኒስቴር ጋር በትበብር እየሰራን ነው ብለዋል።
ኤጄንሲው የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እቅዱን በመከለስ ለ2013 የስራ ዘመን የተለጠጠ እቅድ አዘጋጅቶ ከባለደርሻ አካላት ግብዓት በማደበር ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት በሀገሪቱ የሚንቀሰቃሱ ከ900ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች የመድህን ሽፋን ለመስጠት መታቀዱን አመልክተው አዳዲስ ወደ ሀገር የሚገቡትን ጨምሮ ከ200ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ለመመዝገብ አቅደናል ብለዋል።
በተመሳሳይ የአስቸኳይ ህክምና አገለግሎት ተደራሽነት፣የተጎጂዎች የካሳ ክፍያ ማሻሻያ ጥናት ተጠናቆ ለመንግስት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው የሀገሪቱን ልማትና እድገት የሚመጥን አገለግሎት ለመዘርጋት እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት በአስቸኳይ ጊዜ ህክምና አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ጉድለቶች ለማስተካከል ፣የካሳ ክፍያ መጠን ለማሳደግ የሚያስችሉ ውጤታማ ስራ ለመስራት ማቀዳቸውን የተናገሩት ደግሞ በኤጄንሲው የእቅድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ መሰረት ገብረኪዳን ናቸው።
የደቡብ ክልል የመድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጄንሲ ኃላፊ አቶ አሻ አረጋ በበኩላቸው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል።
የመድህን ሽፋን ቁጥጥርና ክትትል ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ውጤታማ ስራ በማከናወን ከ16ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች በአዲስ በመመዝገብ አባል እንዲሆኑ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በተሽከርካሪ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ለሰጡ 72 የጤና ተቋማት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉንም አመልክተዋል።
(ምንጭ – ኢዜአ)