አርእስተ ዜና
Sat. Apr 20th, 2024

በቴሌኮም ማጭበርበር 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

Aug29,2020
በቴሌኮም ማጭበርበር 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በህገወጥ የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ከነመሳሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች በኢትዮ ቴሌኮም ሳተላይት ኔትወርክ በኩል ማለፍ ሲገባቸው፤ ህገወጥ የቴሎኮም መሳሪያዎችን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና ዓለምአቀፍ ጥሪዎችን በመጥለፍ በራሳቸው መስመሮች ለደንበኞች እያቀረቡ ህገወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ እንደነበር የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልከቷል፡፡

ሕገወጥ የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎችን በድብቅ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት፣ ግለሰቦቹ በሕገወጥ መንገድ በሚሰጡት አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮምን ከፍተኛ ጥቅም ለማሳጣት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አገልግሎቱ ከኢንፎርሜሽን መረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ጋር በቅንጅት ባደረገው ጥብቅ መረጃ ማሰባሰብ፣ ጥናትና ክትትል ከተለያዩ ሕገወጥ መሳሪያዎች ጋር ተጠርጣሪዎች እንዲያዙ መደረጉን ገልጿል።

ለዚህ ህገወጥ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 11 ጌትዌይ (ሲምቦክስ)፣ 26 ቲፕሊንክ፣ 1 ሺህ 339 ሲም ካርዶች፣ 20 ፍላሽ ዲሰክ፣ 11 ላፕቶፕ እና ሌሎች ህገወጥ የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ህገወጥ ድርጊቱ ኢትዮ ቴሌኮምን በአመት እስከ 137 ሚልዮን ብር እንደሚያሳጣው መግለጫው ጠቁሟል፡፡

ሕገወጥ የቴሌኮም መሣሪያዎችን በመጠቀም አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ 11 ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ለመያዝ በአዲስ አበባ በኮልፌ ቀራንዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ልደታ፣ ቦሌ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች በፌዴራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች አማካኝነት ኦፕሬሽኖች መካሄዳቸውንና በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን መግለጫው ጠቅሷል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከኢንፎርሜሽን መረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ጋር ከዚህ በፊት በቅንጅት ባደረጋቸው ተከታታይ ኦፕሬሽኖች ኢትዮ ቴሌኮምን ከፍተኛ ገቢ ሊያሳጡ የሚችሉ የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊቶችን ማስቀረቱን ገልጿል።

ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ሲመለከተ በየአካባቢው ለሚገኙ የመረጃና የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል።

(ምንጭ-ኢዜአ)

Related Post