አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

በአዲስ አበባ ባለ ኮከብ ሆቴሎች 35 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያጡ ነው

በአዲስ አበባ ባለ ኮከብ ሆቴሎች 35 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያጡ ነው
በአዲስ አበባ ባለ ኮከብ ሆቴሎች 35 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያጡ ነው

በአዲስ አበባ የኮከብ ደረጃ የተሰጣቸው ሆቴሎች በኮሮናቫይረስ ሳቢያ በወር በአማካይ እስከ 35 ሚሊዮን ዶላር እያጡ መሆኑን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር አስታወቀ።

ኮቪድ 19 የዓለም ወረርሸኝ በመሆን የተለያዩ አገራት የጤና ቀውስ ከመሆንም ባለፈ ኢኮኖሚያቸውን ክፉኛ እያዳከመ ይገኛል። ቫይረሱ ዓለም አቀፍ መፍትሄ እስካላገኘ ድርስ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ላይም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ መበርታቱ የማይቀር መሆኑ ይገመታል። በዚህም በኢትዮጵያ አሁን ላይ በተለይ የቱሪዝምና የመስተንግዶ ዘርፉ፣ ግብርናው፣ አምራች ኢንዱስትሪውና የውጪ ንግዱ ክፉኛ እየተጎዳ መሆኑን ጥናቶች እያመላከቱ ነው።

በኢትዮጵያ ”ወረርሽኙ ለስድስት ወራት የሚቆይ ከሆነ ደግሞ አገሪቷን 139 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ምርት መቀነስ ሊያጋጥማት ይችላል” ተብሏል። በኮሮና ወረርሽኝ ተፅእኖ በአዲስ አበባ በሚገኙ ታላላቅ ሆቴሎች ብቻ በወር በአማካይ እስከ 35 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያሳጣ መሆኑም ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ስር ካሉት 130 ሆቴሎች መካከል በ126ቱ ላይ የተደረገው የአጭር ጊዜ ጥናት ግኝትም ይህንኑ አረጋግጧል። የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ሰብሳቢና የጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ብስራት ÷በመዲናዋ ከባለ 2 እስከ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች ወቅታዊው የገበያ ሁኔታ የጥናቱ አካል መሆናቸውን ጠቁመው÷በዚህም በወር በአማካይ እስከ 35 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩ እየተባባሰ እንዳይሄድ በመንግስት የተወሰዱት እርምጃዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ቢኒያም የገጠሙንን ፈተናዎች በትብብር እናልፋቸዋለንም ነው ያሉት። የሃርመኒ ሆቴል ዋና ስራ አስኪያጅና የሆቴሎች አማካሪ አቶ ዜናዊ መስፍን በበኩላቸው÷ በወረርሽኙ ምክንያት የሆቴል ኢንዱስትሪው ክፉኛ እየተጎዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም በመንግስት የተደረጉት የእዳ ስረዛና የብድር ሁኔታን የማመቻቸት ስራዎች ጥሩ የመፍትሄ ርምጃዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የዘርፉ ማሽቆልቆል በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳርፈው ጫና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ፣ ወረርሽኙ እልባት ቢያገኝ እንኳ የቀደመው የውጪ ገቢ ይመለሳል የሚል የቅርብ ጊዜ ግምት የለም ብለዋል።

በመሆኑም ይህን ሊመልስ የሚችል ተብሎ የተቀመጠው፣ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የውጭ ኩባንያዎች መመለስን ተከትሎ ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል። የሆቴል አገልግሎት መቋረጥን ተከትሎ ሌሎች ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተቋማት የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የቱሪዝም ኢትዮጵያ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍጹም ካሳሁን ናቸው። ለዚህም እንደ ማገገሚያ በመንግስት በቅርቡ ተግባራዊ እያደረገ ያለው የማሻሻያ ርምጃ አበረታች ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል። (ምንጭ-ኤፍ.ቢ.ሲ)

Related Post