አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

ኢትዮጵያ የታደገችዉ የሰዉ ልጆች አሻራ

ኢትዮጵያ የታደገችዉ የሰዉ ልጆች አሻራ
ኢትዮጵያ የታደገችዉ የሰዉ ልጆች አሻራ

በመኮንን ተሾመ ቶሌራ – መፅሐፈ ሔኖክ የሰዉ ልጆች በጥንት ዘመን ከፃፉአቸው መፃህፍት አንዱ ሲሆን የኖህ ቅድመ አያት በሆነዉ በሄኖክ በእብራይስጥ ቋንቋ እንደተፃፈ ይታመናል። በሔኖክ እንደተፃፈ የሚነገረዉ ይህ መጽሃፍ ከአለም ላይ ከ 2000 አመታት በላይ በእብራይስጥም ይሁን በሌሎች ቋንቋዎች የነበሩት ቅጂዎቹ በሙሉ ጠፍተዉ ወይም እነዲጠፉ ተደርገዉ ስለነበር የሰዉ ልጅ የዚህን ታላቅ ስራ ዱካዉን ማግኘት ሳይችል ቆይቶ ነበር።

ይሁንና ብርቱዎቹ የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶችና መነኮሳት በነበራቸዉ አለማቀፍ ግንኙነት መጽሃፉን ካለበት ቦታ በማምጣት ሙሉ በሙሉ በቁም ፅሁፍ (Calligraphy) በብራና ገልብጠዉት ስለነበር አለማች መልሳ ልታገኘዉ ችላለች። በዚህም መፅሐፈ ሔኖክን ጠብቃ በማቆየቷ ኢትዮጵያ ለመላዉ አለም ታላቅ ዉለታ ለመስራት ችላለች።

መፅሐፈ ሔኖክ በቅዱስ መፅሃፍ አዲስ ኪዳን ሦስት ቦታዎች ላይ ማለትም በሉቃስ 3:37 ፣ እብ 11:5 እንዲሁም ይሁዳ 1:14-15 ላይ የተጠቀሰ ታላቅ ክርስቲያናዊ የሃማኖት መፅሃፍ ነዉ። የክርስትና ሃይማኖት ታሪክንና ትርክቶችንም የተሟላ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለዉ መጽሃፍ እንደሆነ በበርካታ ምሁራን ይታመናል።

ይሁንና መፅሃፉ የአይሁድና የፕሮቴስታነት ሀይማኖቶችን ጨምሮ በበርካታ የሃይማኖት አባቶች ትኩረት ተነፍጎት ቀኖናዊ እንዳይሆን ተደርጎ ይልቁንም የኦሪት ዘመን መፃህፍ (deuterocanonical) ነዉ በሚል ከየቅዱስ መፅሃፍቶቻቸዉ ጥራዝ ዉስጥ እንዳይካተት አድርገዋል።

የተለያዩ ሀይማኖቶች በተለያዩ ጊዜአት በተደረጉ የሲኖዶስ ዉሳኔዎች መሰረት በየቅዱስ መፅሃፍቶቻቸዉ (sculptures) መካተት ያለባቸዉን መፃህፍት እነደወሰኑ ይታወቃል።
በዚሁ መሰረት የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን 73 ቀኖናዊ መፃህፍተን የምትቀበል ሲሆን አይሁዶች 24 መፃህፍት አላቸዉ እንዲሁም በቁጥራቸዉ እጅግ ብዙ የሆኑት የፕሮቴስታንት አብያተ-ክርስቲያናት ደሞ 66ቱን መፃህፍት ቀኖናዊ አድርገዉ ይጠቀማሉ። እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ ግን መፅሐፈ ሔኖክን በመፅሃፍ ቅዱሶታቸዉ አላካተቱም።

እንዳንዶች አሰተያየታቸዉን ሲሰጡ በአዲስ ኪዳን እዉቅና የተሰጠዉ የሔኖክ መፅሐፍ ቢያንስ በአይሁዶች ቀኖናዊ መፃህፍት እንኳን ተካቶ ቢሆን ኖሮ ለብዙ ዘመናት ጠፍቶ አየቀርም ነበር ይላሉ።

ይህን በተመለከተ ታላቁ የዘመናችን የጥንታዊ የግእዝ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ኃይሌ “አከራካሪ መጽሐፍ” ያሉትን መፅሐፈ ሔኖክን “ይህ መጽሐፍ ከየትኛዉም የሲኖዶስ ቅጂ ዉስጥ ተዘርዝሮ አይገኝም ፣ ከሰማኒያ አንዱ መጻሕፍተ ሕግ አንዱ አይደለም።” ሲሉ ገልፀዉታል።

ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ይህን ሲሉ የመጽሃፉ ሙሉ ቅጂ በግእዝ ቋንቋ ከኢትዮዽያ ከመገኘቱ በፊት ቀደም ብሎ እና የሃገራችን ሊቃዉንትም ከንጉስ ዘርዓያቆብ ዘመን ጀምሮ ክርክር አድርገዉ ከመወሰናቸዉ በፊት ይሁን አይሁን ግን ግልጽ አያደርጉም።

ምክንያቱም እሳቸዉ እነዳሉት መፅሐፈ ሔኖክ በአለም ዙሪያ አከራካሪ እና በቀኖናዊነት ቅቡልነት የሌለዉ ቢሆንም አሁን ላይ ግን መጽሃፉን ለምዕተ ዐመታት ጠብቃ ባቆየችዉ በኢትዮዽያና እንዲሁም በኤርትራ ሰማኒያ አንዱ መፃህፍት ተካቶ እናገኘዋለን።

መፅሃፉ አከራካሪ የሆነበት ምክንያት የመፅሃፉ ዋና ዋና ሀሳቦች በሌሎች ቅዱሳን መፃህፍት መገለፃቸዉና በሄሆክ ዘመን የፅህፈት ዘዴ ገና ባለመፈጠሩ እንዴት ሄኖክ መፅሃፉን ሊጽፍ ቻለ የሚል ጥያቄ ስላለ ነዉ (ጌታቸዉ 51፣2012)።

ፕሮፌሰር ጌታቸዉ “ከግእዝ ሥነ ጽሑፍ ጋር ብዙ አፍታ ቆይታ” በተሰኘዉ መፃህፋቸዉ (ጌታቸዉ 50፣2012) “ከጠፋበት ምክንያት አንዱ ሲኖዶስ ዉስጥ ባለመግባቱ [በሲኖዶሶች ባለመመረጡ] የሆናል፣ ለምን አልገባም ? የመፅሃፍ ቅዱስን መጠን የወሰኑ አባቶች ብዙ መፃህፍት አስቀርተዋል፣ ወንጌላቱም አራቱ ብቻ እንዲሆኑ የወሰኑት እነሱ ናቸዉ።”

መጽሃፉ በኢትዮዽያ ቀኖናዊ መፃህፍት ዉስጥ እንዲካተት ብዙ ክርክር እነደተደረገም ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ጽፈዋል። በተለይ ንጉስ ሀርዓያዕቆብ መፅሐፈ ሔኖክን የሚተቹትን ኢትዮዽያን ሊቃዉንትና የሲኖዶስ አባላት በሃሳብ ክፉኛ ይሞግታቸዉና በቁጭትም ይፅፍ እንደነበረ ይገልጻሉ።

“ሔኖክን የምትክድ ከሃዲ ሰዉ ሆይ – ስማ ፣ ኦሪትም የሄኖክን ክብር እንዲህ ስትል ትናገራለች፣ ‘ሔኖክ እግዚብሄርን አስደሰተዉ ፣ አልተገኘምም ፣ እግዚአብሄር ደብቆታልና።’ ” ሲል ፅፎ መፅሃፉ ከ81ዱ መፃህፍት ዝርዝር መግባት እንዳለበት መከራከሩን ጠቁመዋል። [“አልተገኘምም ፣ እግዚአብሄር ደብቆታልና” ያለዉ በመፅሀፍ ቅዱስ መሰረት ሄኖክ ከጥፋት ውሃ በፊት ያረገ የመጀመሪያው ሰው በመሆኑ ነዉ። ከጥፋት በኋላ ደሞ ኤልያስና እየሱስ ክርስቶስ ስጋቸውን ነፍሳቸውንና መንፈሳቸውን ይዘው ወደ ሰማይ ተነጥቀዋል ተብሎ ይታመናል፡፡]
በመፅሃፉ ዙሪያ ካለዉ ክርክር ባለፈም የመፃህፉ መገኘት ለሀይማኖት ታሪክ ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል።
[embedyt] https://www.youtube.com/watch?v=KIChceXNWE0[/embedyt]
ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ “The Ethiopian Orthodox Tawahidi Church” በተሰኘዉ መፅሃፋቸዉ የመፃህፉን ጠቀሜታ በተመለከተ ሲያብራሩም መፅሀፈ ሄኖክ ለግእዝ ስነ-ፅሁፍ ልክ ፑሽኪን ለሩሲያ ስነ-ፅሁፍ እና ሼክስፒር ደሞ ለእንግሊዝ ስነ-ፅሁፍ ያላቸዉን ያህል ክብደት እነዳለዉ ፅፈዋል። “For Ethiopic literature, the Book of Enoch is like Pushkin for Russian literature and Shakespeare for English literature.” (Ephraim I. PP 66:2013)

ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንዳሉት መፅሃፈ ሄኖክ በአለም ላይ ጠፍቶ ሙሉ ጥራዙ በግዕዝ ቋንቋ እንደመገኘቱ በቋንቋዉን ባህሪያትና አገላለፅ ምክንያት እና አሁን እንደ ሪጂናል ተደርጎ የሚጠቀሰዉ ግእዙ በመሆኑ ለሀገራችን የሚኖረዉ ጠቀሚታ ከፍ ያለ መሆኑ አይቀርም።

አሁን ላይ በተለያዩ አለማትና የሀገራችን ገዳማት የሚገኙት የመፀሃፉ ቅጂዎች የተፃፉመት መንገድና አቀራረብ (የምእራፍ አከፋፈል ፣ ቁጥር አሰጣጥ ፣ ጥረዛ ፣ ህዳግና ስዕል አሳሳል) ቅጂዎቹ እነደ ተገለበጡበት ዘመንና ፀሀፊዎች ይለያያሉ።

ቀደም ብሎም በ18ኛዉ ክ/ዘ የአባይን መነሻ ለማሰስ ወደ ኢትዮዽያ ከመጡ አሳሾች መካከል ጀምስ ብሩስ የተባለ ስኮትላንዳዊ ሁለት ቅጂዎችን ወደ አዉሮፓ ወሰዶ ስለነበር እና የመጽሀፉ አንዳንድ ብጥስጣሽ ብራና ቅጂዎች/ሙት ባሕር ብራናዎች(Dead Sea Scrolls) በአረማይክ ቋንቋ በ1950ዎቹ በመገኘታቸው ምክንያት መፅሀፈ ሄኖክ በአሁኑ ወቅት በመላዉ አለም ነሚገኙ አብዛኛዉ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለትምህርትና ለምርምር ስራ እየዋለ ይገኛል። በአማርኛ ቋንቋም በብዛት እየታተመና እየተሰራጨ ይገኛል።

በሀገራችን ባሉ ገዳማትም እንደማንኛዉም የግእዝ ቋንቋ መፃህፍት ከጥንት ጀምሮ በብዛት እየተባዛና እየተሰራጨ ቆይቷል። ይሁንና በየገዳማቱ የሚገኙ የግእዝ ቋንቋ መፃህፍት ብዙ ጊዜ የተፃፉበትን ዘመን እና ፀሃፊዉን ስለማይጠቅሱ ( አንዳንዴም የገለበጡት መፅሀፍ ላይ ስም መፃፍ ትህትናን ሰለማያሳይ) ትክክለኛ ዕድሜያቸዉን እና ፀሀፊዉን ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ የሚታዎቅ ነዉ።

ይሁንና ፕሮፌሰር ጌታቸዉ እንደሚት የየዘመናቱ የቁም ፅሁፍ አይነቶች ስለሚገመቱና ወይም ጸሀፊዉ በፅሁፉ መሃል በዘመኑ የነበረዉን ንጉስ ወይም ዻዻስ ጠቅሶ እንደሆነ እሱን በመፈለግ ዘመኑን ለመገመት ይቻላል።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰዉ ምንም እንኳን መፅሀፈ ሄኖክ አከራካሪ ቢሆንም በአጠቃላይ ለሰዉ ልጆች የሀይማኖት ጥናት የሚሆኑ በርካታ ጠቃሚ መልእክቶች እና ታሪኮች ያሉት እንደሆነ ምሁራን ይስማማሉ።

ከመፀሀፉ ቀደምት ቅጂዎች አንዱ ከሆነዉና በፈረንሳይ ብሄራዊ ሙዚዬም ከሚገኘዉ የአንቷን ዳባዲ (Antoine d’Abbadie) ቅጂ መረዳት እንደሚቻለዉ አንዳንዴ የምጽአት ቀን መፅሀፍ (apocalyptic) በመባል የሚታወቀዉ መፅሐፈ ሔኖክ አምስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት።

በነገራችን ላይ አንቷን ዳባዲ (Antoine d’Abbadie) ፣ እ᎐አ᎐አ ከ1830ቹ እስከ 1870ቹ 234 ያህል የግእዝና ያማርኛ መፃህፍት ላይ ጥናትና ምርምር ያደረገ እንዲሁም መዝገበ ቃላትን ያሳተመዉ እና ኢትዮጵያንና ቋንቋዎቹዋን (ግእዝንና አማርኛን) አቀላጥፎ የሚናገር በመሁኑ የዘርዓያቆብን “ሐተታ ዘርዓያቆብ” የተሰኘዉን መፃህፍ ፅፎ ሊሆን ይችላል እያሉ አንዳንድ የዉጭ ፀሃፊዎች እኛ ኢትዮጵያን እንደ “ ሐተታ ዘርዓያቆብ ያለ ጥልቀ መልእክት ያለዉ ፍልስፍና በዚያ ዘመን መፃፍ እንደማንችል በመፃፍ የሀገራችንን ክብር ለመንካት ከሚሞክሩበት ሁኔታ ጋርም ይያያዛል።

የመፅሐፈ ሔኖክ አምስቱ ዋና ዋና ክፍሎቸም የሚከተሉት ናቸዉ፡
1. መጽሀፈ ትጉኃን (The Book of the Watchers , 1 Enoch 1–36)
2. መጽሀፈ ምሳሌ (The Book of Parables of Enoch, 1 Enoch 37–71)
3. የሰማይ ብርሃናት መመለስን የተመለከተ (The Astronomical Book , 1 Enoch 72–82) (also called the Book of the Heavenly Luminaries or Book of Luminaries)
4. የሄኖክን ህልሞች የተመለከተ ክፍል (The Book of Dream Visions , 1 Enoch 83–90) (also called the Book of Dreams)
5. ሔኖክ መልእክት (The Epistle of Enoch , 1 Enoch 91–108)

ትንሹ ዘፍጥረት (The Little Genesis) በመባል በሚታወቀዉ መፅሀፈ ሄኖክ የመጀመሪያዉ ክፍሉ በሆነዉ መጽሀፈ ትጉኃን ሄኖክያያቸዉን ራዕዮች ይዘረዝራል ። በወቅቱ የነበሩ ሰዎች በአመጻቸው ጽናት ከቃየል ልጆች ጋራ አብረው እንዲዋሀዱ ከደብረ ቅዱስ በወረዱበት ጊዜ ሄኖክ እንደ ገሠጻቸው ይላል። የከለሱት ልጆቻቸውም በቁመት አብልጠው ረጃጅሞች እንደተባሉ እነዚህም አባቶቻቸውንና ምድሪቱን እንደ በደሉ ይናገራል።

በዘፍጥረት የተገለፀዉን የግዙፎቹን ሰዎች (የኔፍሊኖችን) እና ከነሱ ጋር ስለተወዳጁት ሴቶችና ሌሎችንም ታሪኮች ይተርካል።ይህንንም “በእማንቱ መዋእልተ ወልዳ ሎሙ አዋልድ ሠናይት ወላሕያት። ወርእዩ ኪያሆን መላእክት ዉሉድ ሰማያት ወፈተዉዎን ወይቤሉ በበይናቲሆሙ ንዑ ንኀረይ ለነ አንስተ እምዉሉደ ሰብእ ወንለድ ለነ ዉሉደ።”ሲል በግእዙ ፅፎታል።
“ በእነዚህ ወራት መልከ መልካሞችና ደመግቡዎች ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸዉ። የሰማይ ልጆች መላእክትም እነርሱን አይተዉ ወደዷችዉ።” እንደማለት ሲሆን መላእክቱም ከሴቶቹ ልጆችም እንዉለድ ብለዉ ወለዱ ልጆቻቸዉል ከሰዉ ቅርፅ የተለዩ በጣም ግዙፎች ሆኑ ፣ አምላክ እስከሚያጠፋቸወም ድረስ ብዙ ጠፋትና ሀጥያትም አደረሱ።

በተጨማሪም ሄኖክ ወደ ሰማያት ተወስዶ የሰማይ ቦታዎችን ያሳዩታል። ከዚህ በላይ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ብዙ ይነበያል፤ ያኔ ጻድቃን ሺ ልጆችን ይወልዳሉና በሰላም በደስታ እንደሚኖሩ የሚል ትንቢት ነው። በዚህ መሠረት የመሢህ፣ የሙታን ትንሣኤ እና የዕለተ ምፅአት ትንቢቶች መጀመርያ ከሄኖክ ወይም ከአዳም ዘመን ጀምሮ ይገልፃል።
መፅሃፉ በሌሎቹ ክፍሎችም ስለ ተለያዩ ምሳሌዎች ፣ ስለ ሰማይ ብርሃናት መመለስ ፣ስለ ሄኖክ ህልሞች እና መልእክቶች ጥልቀት ባለዉ ፍልስፍና ስለሚያቀርብ ለተለያዩ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም ተሪክን ለመቀመር ጠቃሚ መሁኑ ይታመንበታል።

Related Post