አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

የሲሚንቶ ዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት ተገኝቶባቸዋል

የሲሚንቶ ዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት ተገኝቶባቸዋል
የሲሚንቶ ዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት ተገኝቶባቸዋል

በገበያ ላይ የተከሰተውን የሲሚንቶ እጥረት እና የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በሲሚንቶ ምርትና ግብይት ሂደቱ ላይ ውጤት ማሳየቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአቅርቦት ችግር ምክንያት በሙሉ አቅማቸው ባለማምረታቸው እና ነጋዴ ያልሆኑ አካላት በነጋዴ ስም በህገ-ወጥ መንገድ ምርቱን በመያዛቸው የሲሚንቶ ምርት እጥረትና ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል፡፡

የአቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከውጪ የሚያስመጡትን ጥሬ እቃ ከሀገር ውስጥ እንዲጠቀሙ በመደረጉ 20 በመቶ ብቻ ከሀገር ውስጥ ይጠቀሙት የነበረውን የድንጋይ ከሰል አሁን ከ60-100% ከሀገር ውስጥ ተጠቅመው እያመረቱ ይገኛሉ፡፡

ፋብሪካዎች የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን መጠቀማቸው የማምረት አቅማቸውን ከመጨመሩም በዘለለ ሀገራችን ያለባትን የውጪ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለልና የማምረቻ ዋጋቸውን በመቀነስ ሲሚንቶን ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ እንዲያቀርቡም ያስችላል፡፡

በተጨማሪም በሲሚንቶ ግብይት ውስጥ ያሉትን ህገ-ወጦች ከገበያው ስርዓት ውስጥ ለማሶጣት በቅርቡ በተዘረጋው አሰራር ህጉን ለማክበር ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴዎችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ብቻ ሲሚንቶ ከፋብሪካ ገዝተው እንዲያከፋፍሉ በመደረጉ የስርጭት ሂደቱ ጤናማ ሆኗል ያሉት ሚኒስትሩ የአቅርቦቱ ችግር እየተስተካከለ፣ ህግ የማስከበርና ግብይቱን በስርዓት የመምራቱ ስራ እየተሰራ ስለሆነ አሁን ያለው የሲሚንቶ ዋጋ በቀጣይ በእጅጉ ይቀንሳል ብለዋል፡፡

አቶ መላኩ አክለውም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በሲሚንቶ ላይም ሆነ በምግብ ሸቀጦች ላይ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የተሰሩ አቅርቦትን የማሻሻልና የቁጥጥር ስራዎች ውጤታማ ነበሩ ያሉ ሲሆን በቀጣይም አቅርቦቱን የማስተካከልና ህግ የማስከበር ስራዎችን ሳይነጣጠሉ ህብረተሰቡንና ነጋዴውን ባሳተፈ መልኩ በመስራት አሁን ያለውን የገበያ ሁኔታ ይበልጥ ለማረጋጋት ይሰራልም ብለዋል፡፡

(ምንጭ – የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት)፡

Related Post