አርእስተ ዜና
Fri. Nov 22nd, 2024

ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ አገልግሎቶችን አስጀመረ

ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ አገልግሎቶችን አስጀመረ
ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ አገልግሎቶችን አስጀመረ

ኢትዮ ቴሌኮም የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በቴሌብር ለደንበኞቻቸው ለማቅረብ የሚያስችል የዲጂታል የፋይናንስ ገበያ እና የዲጂታል የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ አገልግሎቶችን በይፋ አስጀመረ።

ኢትዮ ቴሌኮም የፋይናንስ ዘርፉ ባንኮች፣ ማይክሮ ፋይናንስ፣ ኢንሹራንስ እና ሌሎችም በዘርፉ ያሉ ተቋማት የቴክኖሎጂ አቅምን ተጠቅመው የፋይናንስ አገልግሎታቸውን ተደራሽና አካታች ለማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ የሚያስችላቸውን የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ (Digital Financial Marketplace) ሶሉሽን አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ ተቋማት በርካታ የአክሲዮን ባለድርሻዎች ያሏቸው እንደመሆኑ የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ ሂደታቸውን ዲጂታል በማድረግ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የሚያስተዳድሩበት የዲጂታል አክሲዮን ገበያ (Digital Share Sell/Buy) ሶሉሽኖችን ይዞ ቀርቧል፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ገበያ / Digital Financial Marketplace/ የፋይናንስ ተቋማት የማይክሮ ፋይናንስ ማለትም የብድር፣ ቁጠባ እና ኢንሹራንስ አገልግሎቶቻቸውን ለደንበኞቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ በአንድ ፕላትፎርም (Unified Digital Financial Marketplace) በዲጂታል አማራጭ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ሶሉሽን ሲሆን ደንበኞች ካሉበት ሆነው የእጅ ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ አገልግሎቱ የደንበኞችን የብድር እንቅስቃሴ እና በወቅቱ የመመለስ ልምድን በማገናዘብ እና የሰው ሠራሽ አስተውሎትን (Artificial intelligence) በመጠቀም በሚሰራ የብድር ቀመር (credit score) መሰረት የሚከናወን በመሆኑ ያለምንም የንብረት መያዣ (Collateral) የብድር አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ነው።

ኩባንያችን ከዚህ ቀደም ከዳሽን ባንክ እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ በቀረጸው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ከ3.6 ሚሊዮን ደንበኞች በላይ በብድር አገልግሎት ተደራሽ ያደረገ ሲሆን በዛሬው ዕለት የቀረበው የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ ሶሉሽን ባንኮች ምንም አይነት የካፒታል ኢንቨስትመንት ማድረግ ሳይጠበቅባቸው ኢትዮ ቴሌኮም በገነባው ፕላትፎርም ተጠቅመው የፋይናንስ አገልግሎቶቻቸውን ከ40 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ የቴሌብር ደንበኞች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚችሉበት አገልግሎት ነው፡፡

ይህ የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ ባንኮች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ እንደሀገር በብሔራዊ ባንክ በተያዘው የብሔራዊ ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ላይ በ2025 70 በመቶ ዜጎች በፋይናንስ እንዲካተቱ ለማስቻል የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ በእጅጉ የሚያግዝ ይሆናል፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ አገልግሎት ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ሲሆን ባንኮች ይህንኑ እንዲያውቁ በማድረግ በአሁኑ ሰዓት ፕላትፎርሙን ለመጠቀም ከአሀዱ ባንክ፣ ከሲንቄ ባንክ፣ ከእናት ባንክ እና አዋሽ ባንክ ጋር ውይይት ተጠናቆ ከብሔራዊ ባንክ በሚያገኙት ይሁንታ መሰረት አገልግሎቱን በቅርቡ የሚጀምር ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችል ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም በዛሬው ዕለት ኩባንያችን ዘመናዊ የዲጂታል አክሲዮን የግዢና የመሸጫ (Digital Share Sell/Buy) ፕላትፎርም ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ፍቃድ የተሰጣቸው የቢዝነስ ተቋማት የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ ሂደታቸውን ዲጂታል በማድረግ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የሚያከናውኑበትና አክሲዮናቸውን ለማህበረሰቡ በስፋትና በቀላሉ ተደራሽ የሚያደርጉበትን እድል አመቻችቷል፡፡

የቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እጅግ አስተማማኝ፣ ቀላል፣ ፈጣንና ምቹ ግብይት ለማከናወን በተለይም የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ አገልግሎት አቅራቢንና ተጠቃሚን ለማገናኘት፣ ሥራ ፈጣሪነትንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታት እንዲሁም አጠቃላይ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በማፋጠን ረገድ ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ ኩባንያችን ከዚህ ቀደም ዘርፎችን በመለየት እንደ ስማርት ትምህርት፣ ስማርት ግብርና፣ ስማርት ውሃና ኤነርጂ የመሳሰሉትን ዲጂታል አገልግሎቶች በማምጣት ቀልጣፋ እና ውጤታማ እንዲሁም ሀገራችንን ተወዳዳሪ ለማድረግ በመስራት ባንኮች የራሳቸው ዳታ ሴንተር መገንባት ሳይጠበቅባቸው በዋና ተልዕኳቸው ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስችላቸውን የሞጁላርና የክላውድ ዳታ ሴንተር አገልግሎት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት በዛሬው ዕለት ያቀረብነውን የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ገበያን በመጠቀም የሀገራችንን የፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነትን በጋራ እንድናረጋግጥ እንዲሁም ወጪ ቆጣቢ የሆነው የዲጂታል አክሲዮን ግዢና ሽያጭ አገልግሎቶችን እንዲጠቀሙ እየጋበዝን በቀጣይም ኩባንያችን ዜጎች በቴሌብር አማካይነት በቀላሉ ሁለንተናዊ የላቀ ተሞክሮን ለማሻሻል፣ ሕይወትንና የአኗኗር ዘይቤን ለማቅለል፣ የቢዝነስ አጋሮቻችን የአገልግሎት አሰጣጥንና አሰራር ለማዘመን፣ ለቢዝነስ እንቅስቃሴዎቻቸው ምቹና አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ይሆናል፡፡

Related Post