አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

የወባ ማጥፋት ፕሮግራም የአፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ

የወባ ማጥፋት ፕሮግራም የአፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ
የወባ ማጥፋት ፕሮግራም የአፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ

የወባ ማጥፋት ፕሮግራም የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወር የአፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው።

የወባ በሽታ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ዋነኛ የጤናና የማህበራዊ ዕድገት ችግር ሲሆን ዕድሜም ሆነ ፆታ ሳይለይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ በሀገራችን የወባ በሽታ የሚከሰተው በአብዛኛው ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር ድረስ ዋናውን የክረምት ዝናብ ተከትሎ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት መረጃ መሠረት የስርጭት መጠኑ ከባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ በግምገማው መድረክ ተገልጿል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት እስከ ህዳር መጨረሻ ያለው ሪፖርት እንደሚያሳየውም 6,330,753 ለሚሆኑ የወባ ህሙማን ተጠርጣሪዎች ምርመራ ተደርጎ፤ በወባ በሽታ መያዛቸው ለተረጋገጠ 1,330,888 ሰዎች የህክምና አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን ይሄም ትኩሳት ኖሮባቸው ምርመራ ካደረጉ ሰዎች መካከል 21% ወባ ተገኝቶባቸዋል፡፡

የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይዎት ሰለሞን የዚህ የግማሽ ዓመት ግምገማ ዋና ዓላማ በግማሽ ዓመቱ ታቅዶ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት አፈፃፀምን በመገምገም ለወባ በሽታ መጨመር አስተዋፅኦ ያደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶችን በመለየት ለቀጣይ የመስተካከያ አቅጣጫዎች ለማስቀምጥ ያለመ መሆኑ ገልጸዋል፡፡

የወባ በሽታን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር በግማሽ ዓመቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የህብረተሰቡን ግንዛቤን ለመጨመር የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ስፖቶች ተዘጋጅቶ መተላለፉ፣ ከ449 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች እና ከ6435 በላይ ቀበሌዎች ከፍተኛና መካከለኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው የወባ ሳምንት ንቅናቄ ማድረግ፤ 19,753,405 አጎበር ተገዝቶ ወደ አገር ዉስጥ እንዲገባ ክትትል የተደረገ ሲሆን የመጀመሪያው 8,367,000 አጎበር ለክልሎች ተሰራጭቷል።

1,207,897 ቤቶችን ለመርጨት ታቅዶ 96% ቤቶችን መርጨት መቻሉን እንዲሁም ለወባ ማጥፋት በተመረጡ ወረዳዎች በማህበረሰብ ደረጃ በሚከናወነው ህሙማንን ተከተሎ በሚሰራ 12,724 Case and foci investigation and response ስራዎች መሰራቱን አቶ ጉዲሳ አሰፋ የወባ ማጥፋት ፕሮግራም አስተባባሪ ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም የወባ ስርጭትን ለመግታት የየክልሉን ተጨባጭ ሁኔት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለወባ በሽታ ማንስራራት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን በጥናት መለየትና አስፈላጊዉን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን በተለየ ሁኔታ መስራት እንደሚያስፈልግ ዶ/ር መሳይ ሀይሉ የኢትዮጵያ ህብረተሰቡ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡

በዚህ ግምገማ ላይ ሁሉም ክልሎች፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰቡ ጤና ኢንስቲትዩት፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና መስራያ ቤትና ቅርንጫፎች እና አገር ድርጅቶች ተወካዮች እየተሳተፉ ነዉ።

Related Post