አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

መንግስት እምነት ተኮር አለመግባባቶችን በሰላም እንዲፈታ ጥሪ ቀረበ

መንግስት እምነት ተኮር አለመግባባቶችን በሰላም እንዲፈታ ጥሪ ቀረበ
መንግስት እምነት ተኮር አለመግባባቶችን በሰላም እንዲፈታ ጥሪ ቀረበ

ከሐይማኖት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ግጭቶች ጉዳታቸው እጅግ የከፋ ነው። በተለያዩ ጊዜያት በመገናኛ ብዙሃን እንደተዘገበው በሃገራችን ሐይማኖትን መነሻ አድርገው በተቀሰቀሱ ግጭቶች የዕምነት ተቋማት በዋነኝነት ኢላማ ተደርገው ተጠቅተዋል፡፡

ግጭቶቹ በከረሩባቸው ቦታዎች ደግሞ ክቡሩ የሰው ልጅ ህይወት ጠፍቷል፣ የንግድ ተቋማት፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ጨምሮ የግለሰብ ቤቶች እና ተሸከርካሪዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በቅርቡ በጎንደር እና በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በሰውና በንብረት ላይ የደረሱ ጥፋቶችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሐያማኖትን መነሻ ያደረጉ አለመግባባቶች እንደ ሌሎቹ በህዝብ መካከል እንደሚከሰቱ ግጭቶች በተቋማት እና በግለሰቦች ላይ ጉዳት ከማድረስ አልፎ በሃገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳርፉት አሉታዊ ተፅኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

እምነት ተኮር ግጭቶች በወቅቱ በብልሃትና በጥንቃቄ ካልተያዙ መዘዛቸው የከፋ ነው፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ቀድሞ ለግጭቶቹ ምክንያት የሆኑ እና የሚሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ ለማውጣት እና ሳይረፍድ መፍትሄ ለመፈለግ በጉዳዮቹ ላይ በጥሞና እና በጥልቀት መስራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ደግሞ መንግሥት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የሐይማኖት ተቋማት እና ህዝቡ በንቃት ሊሳተፍ ይገባል፡፡

የሐይማኖት ነጻነት በአለምአቀፍ ደረጃ ለሰው ልጆች የተሰጠ መብት ነው፡፡ ይህ መብት እንዳይጣስ መንግስት ያሳስባል፤ ይከላከላል፣ ለተግባራዊነቱም አበክሮ ይሰራል፡፡ በምንም መልኩ በሃይማኖት የተነሳ ግጭት የአገር እና የህዝብን ሰላም የሚያደፈርስ እንዲሆን መፍቀድ የለበትም፡፡ ሁሉም ወገኖች እኩል የሚሳተፉበት፣ የተለያዩ ሰዎች ሃሳብ የሚስተናገድበት፣ ስለ ሰላም ፍቅር እና አንድነት የሚወራበትና የሚሰበክበት መድረክ በተከታታይ በማዘጋጀት መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ሊያደርግ ይገባል።

ሐይማኖት የሰላም፤ የፍቅር እና አብሮ የመኖር መርህ መፍለቂያ እንጂ የግጭትና የጥላቻ ምንጭ ሊሆን አይገባም፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትም የሐይማኖት ተቋማት ሐይማኖታዊ አስረተምህሮታቸውን መሰረት አድርገው በተለያዩ እምነት ተከታዮች መሃል እየተከሰቱ ያሉ ግጭትቶችን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት እና ሰላምን የመስበክ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው ውጤታማ ሥራ መስራታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በሐይማኖት ምክንያት በምንም መልኩ ለፀብ ሊዳርግ ይችላል ተብሎ የታመነበት ልዩነት ሲከሰት ህዝብ እንደ ህዝብ በቅንነት እና በግልፅነት ጥልቅ ውይይት ለማድረግ ቆርጦ መነሳት አለበት፡፡ ለመነጋገር ፈቃደኛ ያለመሆን እና በልብ ቂም ቋጥሮ ለበቀል መዘጋጀት የየትኛውም ሐይማኖት ሃሳብም፣ አስተምህሮትም አይደለም፡፡ የሐይማኖት አባቶች፣ መንግሥት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሃገሪቷ እየተከሰተ ያለውን ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ ፀብ ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት ዜጎችም የበኩላቸውን ድጋፍና ሚና በማበርከት ሰላማዊ ሃገር እንዲኖር በሚደረገው ጥረት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እንጠይቃለን።

እኛ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንደ አንድ የልማት አጋር ዋና ተግባራችን በዜጎች ላይ ሊደረስ የሚችልን ማንኛውንም አደጋ መከላከል እና መቀነስ ነው፡፡ ሰላም የእድገት እና የልማት መሰረት መሆኑን እናምናለን፡፡ ስለሆነም የሐይማኖት ተቋማት፣ ህዝብ፣ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጋራ በመሆን ለግጭቶች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን አውቆ ለመፍትሄው በሙሉ ልብ መስራት ይገባናል።

ዛሬ ችላ ብለን ያለፍነው ግጭት ነገ ምን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል በጽኑ ይታወቃል። ለሰላም እና ለፍቅር ጊዜያችንን፤ ዕውቀታችንን እና ልምዳችንን እንስጥ፣ እናካፍል፡፡ ይህንንም በማድረግ፣ በሃገራችን እየታየ ያለውን ሐይማኖታዊ መሰል ግጭት ከሚያስከትለው አደጋ ለመታደግ እንደሚቻል የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በፅኑ ያምናል። የሐይማኖት ተቋማት፣ መንግሥት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ እና ህዝቡ በሃገራችን ያለን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት በመተባበር በጋራ እንዲሰራ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአጽንኦት ጥሪውን ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በአንቀጽ 85 መሰረት የተቋቋመ ምክር ቤት ሲሆን በኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግበው ዕውቅና ያገኙትን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በሙሉ በመወከል በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ በአዋጁ ሃላፊነት ተሰጥቶታል። በአሁኑ ወቅትም ከ3600 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባላት ናቸው።

Related Post