አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

ኢትዮጵያዊው የዕፅዋት ሊቅ የ2022 ሊንያን ሜዳሊያ ተሸለሙ

ኢትዮጵያዊው የዕፅዋት ሊቅ የ2022 ሊንያን ሜዳሊያ ተሸለሙ
ኢትዮጵያዊው የዕፅዋት ሊቅ የ2022 ሊንያን ሜዳሊያ ተሸለሙ

በሄኖክ ስዩም – ኢትዮጵያዊው የዕፅዋት ሊቅ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው የ2022 ሊንያን ሜዳሊያ ተሸላሚ ኾኑ።

የሦስት ሺህ አመት ታሪክ አለን። የ50 አመት ዕድሜ ያለው ሽልማት የለንም። ባለውለታዎቻችን እንደ አትሌቶቻችን የዕውቅና ሜዳልያዎችን ከውጪ ይዘውልን የሚመጡ ናቸው። እንዲህ ካሉ የእኛ ሰዎች መካከል ጉምቱው የዕፅዋት ሊቅ ፕሮፌሰር ሰብስቤ አንዱ ናቸው።

ከዚህ ቀደም የእንግሊዝ የሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ ኪው (Royal Botanic Garden, Kew Medal ዓለም አቀፍ ሽልማትን ወስደዋል። እ.ኤ.አ በ2018 “ለምርምርና ለፈጠራ የላቀ አስተዋፅኦቸው የሮያል ሶሳይቲ አባል ኾነው የተመረጡበትን Foreign Member of the Royal Society (ForMemRS) ክብርን ተቀብለዋል።

እንደ ፈረንጆቹ በ2021 ለትሮፒካል ዕፅዋት ጥናት የላቀ ድርሻቸው Cuatrecasas Medal for Excellence in Tropical Botany ሜዳልያ ከአሜሪካው የስሚትሶኒያን የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ተሸልመዋል።

ዘንድሮ ደግሞ የሳይንስ ሊቃውንቱ ለተፈጥሮ ሳይንስ ዕድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦ የሚሸለሙትን የሊንያን ሜዳሊያ 2022 አሸናፊ ኾነዋል።

ፕሮፌሰር ሰብስቤ እጅግ የገዘፈ አበርክቶ ያላቸው የኤርትራ እና የኢትዮጵያን እፅዋት አጥንተው የሰነዱ የኢትዮጵያ ፍሎራ ፕሮጀክትን ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ ከ17 የአፍሪካና የአውሮፓ አገሮች የተወጣጡ የዕፀዋት ተመራማሪዎችን በመምራት ስኬታማ ስራ የሰሩ “Aloes and Other Lilies of Ethiopia and Eritrea”፣ “Aromatic Plants of Ethiopia”፣ “Atlas of the Potential Vegetation of Ethiopia”፣ “Ethiopian Orchids”፣ “Field Guide to Ethiopian Orchids” በተሰኙ የምርምር ሥራ መጻሕፍቶቻቸው የሚታወቁ ናቸው።

አንድ ቀን እንደ እሳቸው ያሉ መልካም ሰዎች የኢትዮጵያ ጂኦግራፊና ሳይንስ ሶሳይቲ ሽልማትን ዕውን ሲያደርጉ መሰል ባለውለታዎቻችንን ሜዳሊያ ለመሸለም ሌላው ዓለም አይቀድመንም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ለሙያ ጓዶቻቸው፣ ተማሪዎቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸውና ለሀገሬ ሰው ሁሉ ስለ ሽልማቱ እንኳን ደስ ያላችሁ ብያለሁ።

Related Post