አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

በኦሮሚያ ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ የመስኖ ስንዴ ተሰበሰበ

በኦሮሚያ ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ የመስኖ ስንዴ ተሰበሰበ
በኦሮሚያ ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ የመስኖ ስንዴ ተሰበሰበ

በኦሮሚያ ክልል በመስኖ ስንዴ ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ ምርቱን ለመሰብሰብ የተቻለ ሲሆን 4.5 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ማገኘት መቻሉን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ወርቁ ገለጹ።

በክልሉ ከ355 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ስንዴ ልማት የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም ከ15 እስከ 17 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል በማለት የግብርና ሚኒስቴር ዘግቧል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ምርቱ ለመሰብሰብ በሰፋፊ ኩታ-ገጠም እርሻዎችን በዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ /ኮምባይነሮች/ እንዲሁም አነስተኛ የእርሻ ቦታዎችን በሰው ሃይል በመታገዝ የምርት አሰባሰብ ስራ የተጀመረ ሲሆን አሁን ባለው ወቅታዊ መረጃ መሰረትም በመስኖ ስንዴ ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ ምርቱን ለመሰብሰብ የተቻለ ሲሆን 4.5 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ማገኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊው አክለው እንደገለፁት በዘንድሮው ዓመት የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በማስቀጠል ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ስራ በመስራት በቀጣይ ዓመት የተሻለ ሥራ ለመስራት እቅድ መያዙን ገልፀዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የመስኖ ስንዴ ልማት ስራ በስፋት ከተሰራባቸው ዞኖች ውስጥ አንድኛው የምስራቅ ሸዋ ዞን ነው፡፡ በዚህም ዞን ውስጥ በ10 ወረዳዎች ከ65 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ስንዴ የተሸፈነ ሲሆን አሁን የተጀመረውን የምርት አሰባሰብ ስራን በመገምገም እስከ 3 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት የሚያስችል ተስፋ መገኘቱን የዞኑ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በመደበኛ የመስኖ ልማት ስራ 54 ሺህ ሄክታር መሬት በአትክልትና ፍራፍሬ የተሸፈነ ሲሆን አርሶ አደሩም ያመረተውን ምርት የገበያ ትስስር ችግር ሳይገጥመው እንዲሸጥ ኦሮ-ፍሬሽ የሚባል የግብይት ትስስር በመፍጠር አርሶ አደሩ በቀጥታ ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ ይዞ የሚወጣበት ዕድል መፍጠር እንደተቻለም ከዞኑ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሃገራችን ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት በሃገር ውስጥ ለመተካት የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት ይገባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለስንዴ ምርት ተስማሚ አፈርና ምቹ ስነ-ምህዳር ስላላት ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ትልቋ የስንዴ አምራች ሀገር ናት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስንዴ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለው ፋይዳና ከውጭ የሚገቡትን የግብርና ምርቶች በሃገር ውስጥ ለመተካት፣ ለአግሮ-ፕሮሰሲንግና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

በዘንድሮው የምርት ዘመን እንደ ሀገር በተያዘው እቅድ መሰረት በኦሮሚያ ክልል የመስኖ ስንዴ ልማት በሰፋት ከተሰራባቸው ክልሎች አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም የደረሱትን የመስኖ ስንዴ ለመሰብሰብ በዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ /ኮምባይነሮች/ በመታገዝ የምርት አሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

Related Post