አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

ኮቪድ 19 በምርጫ ሥራዎች ላይ አዳዲስ መመዘኛዎች ሊያስተዋውቅ ይችላል

ኮቪድ 19 በምርጫ ሥራዎች ላይ አዳዲስ መመዘኛዎች ሊያስተዋውቅ ይችላል
ኮቪድ 19 በምርጫ ሥራዎች ላይ አዳዲስ መመዘኛዎች ሊያስተዋውቅ ይችላል

ከኮቪድ 19 በኋላ ያሉት ሁኔታዎች በምርጫ ሥራዎች ላይ አዳዲስ እርምጃዎችንና መመዘኛዎችን ማስገደድን ሊያስተዋውቅ እንደሚችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡

የፌዴራል የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ከጤና ሚኒስቴር እና ከምርጫ ቦርድ የሚቀርበውን የባለሙያዎች ማብራሪያ ትናንት በሸራተን አዲስ ሆቴል አዳምጧል፡፡ በውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በሰጡት ማብራሪያ፤ የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታና ቦርዱ ለወደፊት ሊከተላቸው የሚችላቸው የምርጫ አፈጻጸም አቅጣ ጫዎችን በተመለከተ ወረርሽኙና ምርጫን የሚያገናኙ የአሰራር አማራጮችን በተከታታይ እየመረመረ ይገኛል::

ቦርዱ የወደፊት የምርጫ ሁኔታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በሚያይበት ወቅት ከኮቪድ 19 እና ከምርጫ ሥራዎች ጋር የተያያዙ አደጋዎች፣ ተጽእኖዎችና ምላሾችን መለየት ላይ የሚያተኩሩ ግምቶችን ወስዷል፡፡ በዚህም የአካል ደኅንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ከአልኮል የተሰሩ የእጅ ማጽጃዎች፣ የጸረ ተውሳክ ርጭት ማድረግን ጨምሮ የልዩ ልዩ እርምጃዎች አፈጻጸምን አስመልክቶ የምርጫ ህግ ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያዎችን እስከማድረግ አዳዲስ እርምጃዎችና መመዘኛዎች ሊተገበሩ ይችላሉ፡፡

እንደ አቶ ውብሸት ገለጻ፤ ግምቶቹን መነሻ አድርጎ ተግዳሮቶቹ በምርጫ አፈጻጸም ላይ የሚኖራቸው ተጽእኖዎችን በሁለት የቢሆን የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጧል:: የመጀመሪያው የምርጫ ቦርድ የቢሆን የጊዜ ሰሌዳ (ሴናሪዮ) የምርጫ ሂደቱ 10 ወራት እንደሚወስድ አስቀምጧል። ለዚህም ምርጫውን ለማስፈጸም 40ሚሊዮን 985ሺ ዶላር ተጨማሪ በጀት ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው የቢሆን የጊዜ ሰሌዳ ደግሞ የምርጫው ሂደት ሶስት ተጨማሪ ወራት ወስዶ በ13 ወራት እንደሚጠናቀቅ ተመላክቷል፡፡

አጠቃላይ የጊዜ ሰሌዳ በመራዘሙ ምክንያት ቦርዱ ለተጨማሪ ወጪዎች እንደሚዳረግ የገለጹት አቶ ውብሸት፤ በመጀመሪያው የቢሆን አማራጭ ተጨማሪ ወጪዎች በአብዛኛው ከተሻሻለው የመራጮች ትምህርትና አቅርቦት ሥራዎች ጋር የሚያያዙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ተቋማዊ ሥራን በተሟላ ሁኔታ ለመጀመር ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ፤ ምርጫውን ለመደገፍ የሚሳተፉ አካላትን ሙሉ ትኩረት ለማግኘትም የምርጫ ሥራን ቀዳሚ አጀንዳ ለማድረግ 60 ቀናት እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሰሌዳ መሠረት የመራጮችና እጩ ምዝገባ እንዲሁም የመራጮች ተሳትፎ በስጋት እንዳይገታ ተጨማሪ ትምህርት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዙ የማከማቻ ገንዘብ ወጪ እንዲሁም የመራጮች ትምህርት ተጨማሪ ይዘቶች ስለሚኖሩት ቀንና ገንዘብ እንደሚያስፈልግ አቶ ውብሸት ጠቅሰዋል፡፡ በምርጫ ወቅት ፓርቲዎች ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው፤ በዚህም ምክንያት የምረጡኝ ቅስቀሳ 102 ቀናትን እንደሚፈጅም ተናግረዋል፡፡በሁለተኛው የቢሆን አማራጭም ቢሆን ከፍተኛ ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

ምርጫው ከተራዘመ ጊዜ በኋላ የመራጮች ምዝገባን ወደ ዲጂታል መረጃ ለመቀየር የሚያስችልና ለድምጽ መስጫ ቀን ዝግጅት የሚሆን “ዳታ ቤዝ” ግንባታ፤ ለማካሄድ መዝገባዎችን ለማጠናቀቅ ሰነድ ያስገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሰነድ ማጣራትና ውሳኔ መስጠት፤ የተጨማሪ መጋዘን ዝግጅት፤ ለድምጽ መስጫ ቀን አገልግሎት የሚውሉ ግዥዎችን ማከናወን፤ (የምስጢር ድምጽ መስጫ ሳጥን፣ የምልክት ቀለሞች፣ የጽህፈት መሳሪያዎች) እንዲሁም የሚዲያ ክትትል እቃዎች ግዥ ተጠናቅቆ ወደ አገር በመግባት ላይ እንደሚገኝም አቶ ውብሸት ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2012

Related Post